FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, November 29, 2012

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የተጠበቁ የስልጣን መሸጋሸጎችን አደረጉ


ህዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ይፋ ባደረጉት ሹመት 2 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን እና ሁለት ሚኒስትሮችን ብቻ በመሾም አቶ መለስ የመሰረቱትን ካቢኔ ይዘው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።  አስቀድሞ እንደተጠበቀው የኦህዴዱ አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማእረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒሰትር በመሆን የአቶ ጁነዲን ሳዶን ቦታ ተክተዋል። የህወሀቱ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ደግሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ በመሆን ቀደም ብለው በያዙት የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጣን  ላይ እንዲቆዩ ተደርጓል።
አዲስ ሹመት የተሰጠው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ሲሆን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ አድሀኖም  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በእርሳቸው ቦታ ደግሞ ዶ/ር ከሰተ ብርሀን አድማሱ የጤና  ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምኦን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፣ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ብርሀነ ሀይሉ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሶፍያን አህመድ፣ የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ማንያዘዋል፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደሴ ደለቀ፣ የትራንስፖርት ሚኒሰትሩ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የኮሚኒኬሽን ሚኒሰትሩ አቶ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ ፣ የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ፣ የማእድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ፣ የትምህርት ሚኒሰትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒሰትሩ አቶ አብዱላጢፍ አብዱል አህመድ ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አማን አብዱልከድር፣ የሴቶች ፣ ልጆችና ወጣቶች ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ባሉበት ስልጣን እንዲቀጥሉ ተደርጓል። አቶ መለስ ባባረሩዋቸው የንግድና እንዱስትሪ ሚኒስትር ቦታ አቶ ሀይለማርያም ሚኒሰትር ዲኤታ የነበሩትን የብአዴኑን አቶ ከበደ ጫኔን ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል።
አቶ ሀይለማርያም ለካቢኔዎቹ አስተባባሪዎች ሁለት ጠቅላይ ሚኒሰትሮችን ከመሾም በስተቀር 98 በመቶ የሚሆነውን የአቶ መለስን ካቢኔ ሳይነኩ መቀጠሉን መርጠዋል። ኢሳት በሰሞኑ ዘገባው በአቶ ጁነዲን ቦታ አዲስ ሹመት ከመኖር በስተቀር መሰረታዊ የሚባል የካቢኔ ለውጥ እንደማይኖር ዘግቦ ነበር።
በዛሬው ሹመት ህወሃት የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቁልፍ ቦታዎችን አግኝቷል፡፡
ሹመቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለይም በኦህዴድ እና በህወሃት በተገቢው ሁኔታ አልተወከሉም የሚሉ ቅሬታዎችን
ለማርገብ የታሰበ ሳይሆን እንደማይቀር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በካቢኔው ውስጥ አለመካተታቸው አስገራሚ ሆኗል።
ሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መስከረም 25 ቀን 2003 ኣ.ም በሰጡት ሹመት በመንግስት ሥልጣን ላይ
ለረዥም ጊዜ የቆዩትን ባለስልጣናት በመተካካት ስም ዞር ማድረግ ችለዋል፡፡ከነዚህ ባለስልጣናት መካከል ምክትል
ጠ/ሚኒስትር የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ፣የአቅም ግንባታ ሚ/ር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ፣የንግድና ኢንዱስትሪ
ሚ/ር አቶ ግርማ ብሩ፣የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አምባሳደር መሐመድ ድሪር፣የስራና ከተማ ልማት ሚ/ር የነበሩት
ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣የውሃ ሃብት ሚ/ሩ አቶ አስፋው ዲንጋሞ፣የሴቶች ጉዳይ ሚ/ር ወ/ሮ ሙፍረሂት ከሚል፣የሰራተኛና
ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የነበሩት አቶ ሐሰን አብደላ የሚገኙበት እንደነበር ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment