የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከትናንት በስቲያ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ኪዱ ገብረሥላሴ በተባለ የታክሲ ተሳፋሪና በረዳቱ መካከል በተፈጠረ የ1.35ብር አለመግባባት ምክንያት ረዳቱ በጥይት ተመታ።
እንደ ሪፖርተር ዘገባ ድርጊቱ የተፈጸመው ቦሌ መድኃኔዓለም
ከሚገኘው ካልዲስ ካፌ ፊት ለፊት ሲሆን፣ ተጠርጣሪው አቶ ኪዱ ገብረ ሥላሴ ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
ነጋ ንጉሡ የተባለው የታክሲው ረዳትም፤ ሃያት ሆስፒታል ለሕክምና ተወስዷል፡፡
የታክሲው አሽከርካሪ አቶ ጌትዬ ቆንጥር እንደገለጹት፣ ተሳፋሪው ሽጉጡን ሊተኩስ የቻለው የአገልግሎት ማብቂያ ቦታቸው ላይ ሲደርሱ “ውረድ አልወርድም” በሚል ክርክር ነው፡፡
ሾፌሩ አክለውም፦“ታክሲያችን አገልግሎት የሚሰጠው ከመርካቶ እስከ ቴሌ መድኃኔዓለም
ድረስ ነው፡፡ በዚያ ቀንም ተሳፋሪዎችን ከካዛንቺስ ጭነን ወደ ቴሌ መድኃኔዓለም ለማድረስ እየተጓዝን ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ቴሌ መድኃኔዓለም
ስንደርስ ለሁሉም ተሳፋሪዎች እንዲወርዱ ስንናገር፣ ሁለቱ ግን ለመውረድ ፈቃደኛ አልሆኑም፤” ብለዋል፡፡
እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤ከካዛንቺስ- ቴሌ መድኃኔዓለም
ድረስና ከካዛንቺስ- ቦሌ ድልድይ ድረስ ታክሲዎች የሚያስከፍሉት ታሪፍ በተመሳሳይ 2.70 ብር ነው፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪው አቶ ኪዱ መሄድ የምፈልገው ቦሌ ድልድይ ነው በማለት ከሾፌሩና ከረዳቱ ጋር አምባጓሮ ቢፈጥርም፣ ሾፌሩም ሆኑ ረዳቱ ከዚህ በላይ መሄድ እንደማይችሉና ቢሄዱም በሕግ እንደሚጠየቁ ለተጠርጣሪው ይናገራሉ፡፡
በሁለቱም ንግግር የተበሳጨው ተጠርጣሪ ግን ምላሹ ከታክሲ መውረድ ሳይሆን በጎኑ የሰደረውን ሽጉጥ በማውጣት በሾፌሩ ላይ ማነጣጠር ነበር፡፡
ጋዜጣው እንዳለው ይህን የተመለከተው ረዳትም ሽጉጡን ከተጠርጣሪው ለማስጣል ትግል ይገጥማል ።በዚህም መካከል ተቀባብሎ ከነበረው ሽጉጥ የተተኮሰች ጥይት የረዳቱ የግራ ጎን ውስጥ ተቀርቅራለች፡፡
ረዳቱም ከተጠርጣሪው አቶ ኪዱ ሽጉጡን ታግሎ በመቀበል በቦታው ለነበረው የካልዲስ ጥበቃ እንደሰጠው ጉዳዩን የሚመረምሩት ኮንስታብል አዱኛ ገልጸዋል፡፡
ከዚያም ፖሊስ ወዲያው በአካባቢው ደርሶ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎታል፡፡
ተጠርጣሪው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ የቀን ሠራተኛ ሲሆን፣ በነፍስ ማጥፋት ሙከራ ክስ ተመስርቶበታል። ተጠርጣሪው ኪዱ ገብረሥላሴ
የያዘው መሣሪያም ፈቃድ ያለው እንደሆነ በፖሊስ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ዜናውን ባነበቡት ሁሉ ዘንድ አቶ ኪዱ ገብረሥላሴ
ከባለዘመነኞቹና ከአድራጊ ፈጣሪዎቹ ሹመኞች አንዱ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አሳድሯል።
ታክሲ ውስጥ በተፈጠረ ተራ ንትርክ
የእለት ጉርሱን ለማግኘት የሚለፋን ደሀ ረዳት በሽጉጥ መምታት ጥጋብና እብሪት ካልሆነ በስተቀር ምን ሊባል ይችላል? ብለዋል በጉዳዩ ላይ በፌስቡክ አስተያየታቸውን የሰጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን።
የታክሲ ረዳቱ ነጋ በሃያት ሆስፒታል ሕክምናውን እየተከታተለ ሲሆን፣ በሰውነቱ ውስጥ ያለውን ጥይት ለማውጣት ኦፕራሲዮን ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment