ቀን፤ 21/03/2013
ለርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትና ወዳጆች፤ እንዲሁም በUK እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ሁሉ።
የተቀበሉትን የክህነት ኃላፊነት ጠብቀው በንጽሕና በመቆም እግዚአብሔርንና ሰውን ከማገልገል ይልቅ ሥጋዊ ጥቅምን አስቀድመው የተነሱ ጥቂት የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በምእመኑ መካከል ጸብና ጥላቻ ቀስቅሰው ሁከት እንዲሰፍን በማድረግ ባለፈው ሳምንት ለንደን ወደ ሚገኘው የኢህአዲግ መንግሥት ኤምባሲ በመሄድ ቤተ ክርስቲያንን ያህል ነገር እንደ ግል ንብረት ለማስረከብ እንፈልጋለን በማለት ከጠየቁ በኋላ ከዛ በማስከተል ቤተ ክርስቲያኗን የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በመባል በኢህአዲግ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ለንደን ላይ ለተቋቋመው አካል አሳልፎ በመስጠት የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደርና ንብረት ለማስረከብ በድርድር ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት (ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH DIOCESE OF NORTH WEST EUROPE) በሚል መጠሪያ የተቋቋመው ከ11 November 2011ጀምሮ ሲሆን በቻሪቲ ቁጥር 1144634 መሠረት በቻሪቲ ኮሚሽን ተመዝግቦ የሚገኝ ነው።
የዚህ ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ተብሎ የተቋቋመ ሀገር ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቢ አዕላፍ ተወልደ ገብሩ ሲሆኑ፤ የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ደግሞ አቡነ እንጦስ የተባሉ አባ ጳውሎስ በህይወት ሳሉ በጎሳና በመንደር ልጅነት መርጠው ጵጵስና በመሾም ወደ ለንደን የላኳቸው ናቸው። በዚሁ ሃገረ ስብከት ውስጥ በትረስቲነት (Trustees) ሆነው የተዋቀሩት ደግሞ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2005 ዓ/ም ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን ጥለው በመሄድ ሌላ ቤተ ክርስቲያናትን የመሠረቱ ሰዎች ናቸው።
ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለንደን ላይ ከተመሠረተች 40 ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን በዚህ ረጅም የስደት ታሪኳ ወቅት ካለፈው ከደርግ መንግሥትም ሆነ አሁን ካለው የኢህአዲግ መንግሥት ጋር ሳትወግን በልጆቿ ጥረትና ተጋድሎ ከማንኛቸውም የመንግሥትና የፓለቲካ ተጽዕኖ ራሷን ነጻ በማድረግ ሁሉም በእኩልነት የሚያመልክባት ቤተ ክርስቲያን ሆና ኖራለች።
በዚህ የፓለቲካ ወገንተኝነት በሌለው አቋሟም ቤተ ክርስቲያኗ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ዙሪያ ለሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሁሉ ነጻና ፍትሐዊ የሆነ መሥመርን በመከተል ከክርስትና ሃይማኖትና ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅን የእውነት ተግባራት ስታከናውን ቆይታለች።
ዛሬ በሕይወት ያሉና በህይወት የማይገኙ አባላቶቿ ካህናትና ምእመናን ላለፉት 40 ዓመታት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ድካምም በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኗ በእግዚአብሔር ተራዳኢነት ለከፍተኛ የእድገት ደረጃ የበቃች ከመሆኗም በላይ ወደፊትም ከማንኛቸውም የመንግሥትና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በመሆን የበለጠ በማደግና በመስፋት ለስደተኛው ሕዝብና በስደት ላይ ለሚፈጠረው ትውልድ የምትተላለፍ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ፤ ሃብትና ቅርስ ሆና የምትኖር ነች።
ይህንን የመሰለውን የቤተ ክርስቲያኗን ያለፈ ታሪክና የወደፊት ራዕይ በማፍረስ በአሁኑ ወቅት አስተዳደሯንም ሆነ ሃብትና ንብረቷን ዛሬን ኖሮ ነገ በሚያልፍ የኢህአዲግ መንግሥት የእጅ አዙር ቁጥጥርና ተጽዕኖ ሥር ለማዋል የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪና ተከታዮቻቸው በመፈጸም ላይ ያሉት የክህደት ሥራ ቤተ ክርስቲያኗን ለዚህ ያበቋት አባላቷም ሆኑ ደጋፊዎቿና መላው በስደት ዓላም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚታገሱትና የሚቀበሉት አይሆንም።
በዚህ መሠረት ይህችን በሕዝብ ጥረትና ድካም ደርጅታ በእግዚአብሔር ተራዳኢነት ለከፍተኛ የእድገት ደረጃ የበቃች ቤተ ክርስቲያንን ያለ ሕዝብ ፍቃድ፤ እውቅናና ይሁንታ በስውር በመደራደር ለሌላ አካል አሳልፎ በመሸጥ መሾሚያና መሸለሚያ ለማድረግ መሞከር አጠቃላይ ስደተኛውን ኢትዮጵያዊ ከማዋረድ አልፎ በቁመናው እንደ መግደል ስለሚቆጠር የቤተ ክርስቲያኗ አባላት፤ የማርያም ወዳጆችና በአጠቃላይ በስደት ዓለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተሰነዘረበትን ጥቃት በመረዳት የተንኮሉን ገመድ በመበጣጠስ ሴራውን አክሽፎ ከእግዚአብሔር በታች የቤተ ክርስቲያኗ ባለቤት፤ አዛዥና ወሳኝ ሕዝብ ብቻ መሆኑን በተግባር የማረጋገጥ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለበት።
በዚህ መሠረት የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት፤ ወዳጆችና በUKና በመላው ዓለም የምትገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሕግን ተከትሎ በመሄድ ቤተ ክርስቲያኗን ለማዳን የሚደረገው ጥረት ገንዘብ፤ ጊዜና አቅምን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት አስተባባሪ ኮሚቴው በሚያወጣው መርሃ ግብርና ጥሪ መሠረት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ እንድታደርጉ በቅድስት ማርያም ስም ጥሪአችንን እናስተላልፋለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
http://www.goolgule.com/london-debretsion-church-press-release/
No comments:
Post a Comment