የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በምርጫው ከተሸነፉ ዳግም ምርጫ እንዲደረግ አለያም የጥምር መንግስት እንዲቋቋም እንደሚጠይቁ የኬንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ አስጠነቀቁ።
እስካሁን የተደረጉት የድምጽ ቆጠራዎች በምርጫው የጆሞ ኬንያታ ልጅ ኡሁሩ ኬንያታ እየመራ እና የ ኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንቱ ራይላ ኦዲንጋ በሁለተኝነት እየተከተሉ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ይህንኑ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ለመጭበርበሩ እና በድምጽ ቆጠራው ሂደት ስርቆት ለመፈጸሙ በቂ ማስረጃዎች አሉን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውና በዲሞክራሲያዊነቱ በጎ አስተያየቶች
እየጎረፉለት ያለው የዘንድሮ የኬንያ ምርጫ ወደ መጨረሻው ላይ ችግር እንዳይፈጠር ስጋቶች ብቅ እያሉ ቢሆንም፤ እንደባለፈው ምርጫ ጊዜ ደም አፋሳሽ ችግር የሚከሰትበት መንገድ ግን እጅጉን የጠበበ እንደሆነ ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት።
ኦዲንጋ አቤቱታ ቢያቀርቡም ለደጋፊዎቻቸው የተቃውሞ ጥሪ እንደማያደርጉ
አረጋግጠዋል። የአገሪቱ ዋነኛ የምርጫ አስፈፃሚ አካል ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ኦዲንጋን ቅሬታ ውድቅ አድርጎታል። የምርጫ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር አህመድ ይስሀቅ ሀሰን፤ የምርጫ ውጤቱ እንዲጭበረበር የሚያደርግ ምንም ዓይነት ክፍተት የለም ነው ያሉት።
ቀደም ሲልም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች በጽሁፍ የቀረበ ምንም አይነት አቤቱታ እንዳልነበር የምርጫ ኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊ ሊሊያኔ ማሂሪ ዛጃ መናገራቸው ይታወሳል።
ይሁንና የኤክትሮኒክ ድምጽ መቁጠሪያው ከተበላሸ በሁዋላ የድምጽ ቆጠራ ሂደቱ እጅጉን መዘግዬቱን ቢቢሲ ጠቁሟል። በአሁኑ ጊዜ የምርጫ ኮሞሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ ከዲፕሎማቶች ጋር ስብሰባ ተቀምጧል።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2007-2008 በተካሄደው የኬንያ ምርጫ ሚስተር ራይላ ኦዲንጋ የድምጽ ቆጠራ ሂደቱ በፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ ደጋፊዎች እንደተጭበረበረ መናገራቸውን ተከትሎ በተነሳው አመጽ ከ 1000 በላይ ኬንያውያን መሞታቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment