ከመጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ማቆም አድማ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት በርሃብ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል እየተወሰዱ እንደሆነ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፁ፡፡
የትምህርት ጥራት መጓደል፣ የአስተዳደራዊ ችግሮችና በምግብ ጥራት መጓደል ምክንያት ጥያቄያቸውን ለኮሌጁ አስተዳደር ቢያቀርቡም ምላሽ በማጣታቸው የትምህርት ማቆም አድማ ለማድረግ የተገደዱት ቅድስት ስላሴ መንፈሰሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት በርሀብ ተጎድተው ራሳቸውን በመሳት በመጀመራቸው በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል መወሰድ መጀመራቸውን ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡
ፍኖተ ነፃነት ጋዜጠኛም በቅድስት ስላሴና በየሆስፒታሎቹ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው አባ እያሱ ሰብስቤ የተባሉ ተማሪ በየካቲት 12 ሆስፒታል እንዲሁም ደቀመዝሙር በኃይሉ ሰፊ ምኒሊክ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ መሆኑን አረጋጧል፡፡ አመሻሹ ላይም ገ/እግዚያብሄር የተባሉ ተማሪ በአምቡላንስ ከኮሌጁ ተወስደዋል፡፡ ተማሪዎቹ በደል አድርሰውብናል ከሚሉዋቸው የኮሌጁ ሀላፊዎች ውስጥ መምህር ፍስሀፂዮን ደሞዝ አካዳሚክ ዲን እና መምህር ዘላለም ረድዔት የቀን ተማሪዎች አስተባባሪ በዋነኝነት ተጠቅሰዋል፡፡
ደረሰ ስለተባለው ችግር ለማጣራት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሀፊ ብፁዕ አቡነ ህዝቅኤል በኮሌጁ ጉዳይ ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ተናግረው የነበረ ቢሆንም ተሰብሳቢ ባለመሟላቱ ስባሰባው እንዳልተደረገ ለፍኖተ ነፃነት የደረሱ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment