FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, March 9, 2013

የአማራ ክልል ባለስልጣናት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ለተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ” ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ገለጹ


የካቲት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:- ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው በአማራ ክለል ዋና ከተማ ባህርዳር የደረሱ የአማራ ተወላጆች የክልሉ ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲሰጡዋቸው ቢጠይቁም ፣ ባለስልጣናቱ ጉዳዩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ጉዳይ በመሆኑ እንደማያገባቸው መግለጻቸውን ተፈናቃዮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ምንም መፍትሄ ያላገኙት ተፈናቃዮች፣ ሀብት ንብረታቸውን አስረክበው ለጎዳና ተዳዳሪነት መዳረጋቸውን  ተናግረዋል።
በትናንትናው እለት ከ5 ሺ ያላነሱ የአማራ ተወላጆች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲወጡ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል። ከሶስት ሳምንት በፊት ደግሞ በሶማሊ ክልል በጅጅጋና አጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ንብረታቸውን እየተቀሙ ክልሉን እንዲለቁ መታዘዛቸውን ነዋሪዎችን በማናገር መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከደቡብ ክልላዊ መንግስት ቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በመፈናቀል ላይ ያሉ ዜጎች ልጆቻቸውን በጉዲፈቻ የሚወስድላቸው አካል እንደሚፈልጉ  ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ማስታወቃቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
"በአማርኛ ተናጋሪነታችን ሠርተን የመኖር ልጆቻችንን የማሳደግ ህልውና ያጣን ነን፡፡" የሚሉት እነዚህ ዜጎች “በተደጋጋሚ ጥቃት እየተሰነዘረብን ነው፤ ከ20 ዓመት በላይ ከኖርንበት መሬት ተፈናቅለናል፡፡ ከአውሬ ጋር እየታገልን ያለማነውን መሬት ተነጥቀናል፡፡ እነሱ የሚሉን እናንተ አማራ ስለሆናችሁ በዚህ ክልል መኖር አትችሉም፡፡ ወደ ክልላችሁ ሂዱ ይሉናል፡፡ አማራ ክልልን እንኳን ሰርተን የምንበላበት መሬት ቀርቶ ጎጆ ቀልሰን የምንኖርበት ቦታ ሊሰጡን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡” ሲሉ ቅሬታቸውን መግለጻቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
ተፈናቃዮቹም "በቀበሌና በወረዳ ደረጃ የሚፈጸሙብንን ወንጀሎች ለዞንና ለክልል ብናመለክት እኛን ወንጀለኛ አድርገው ጥፋተኞቹን ያበረታታሉ፡፡ በፌዴራል ደረጃ ያሉ ባለስልጣናትም አንድም የሚሰጡት መፍትሄ የለም፡፡ ከላይ እስከ ታች ያሉት በጠቅላላው የሚሰሩት ወንጀል ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ መፍትሄ እናገኛለን ብለን አንጠብቅም፡፡" ሲሉ ተስፋ መቁረጣቸውን ተናግረዋል።
ተፈናቃዮች “ቤት የሌለው መቆሚያና ማረፊያ የሌለው ሰው ቤተሰብ መስርቶ ልጅ ማሳደግ ንብረት ማፍራት አይችልም፡፡ እኛ ከእንግዲህ እንደሆንን እንሆናለን፡፡ ልጆቻችን ግን ማደግ አለባቸው፡፡ በማያውቁት ነገር ሊሰቃዩ አይገባም፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር ጉዲፈቻ የሚያሳድጉ ድርጅቶች እንዲወስዱልን እንፈልጋለን፡፡" በማለት ተማጽነዋል።
ሟቹ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የነደፉት በዘር ላይ የተመሰረተ አስተዳደር አላማ ፣ የኢትዮጵያን የዘመናት አንድነት በመሸርሸር ለአገዛዙ እድሜ ለማራዘም መሆኑን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ መለስ በበኩላቸው ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉት አርሶአደሮች በህገወጥ መንገድ ወደ ክልሉ ሄደው መሬት የወረሩ ናቸው በማለት ፖሊሲያቸውን ከትችት ለመከላከል መሞከራቸው ይታወቃል።
ምን እንኳ የዘር ፖለቲካው ዋና መሪ የነበሩት አቶ መለስ ከዚህ አለም ቢለዩም፣ የእርሳቸውን አገዛዝ የተከተለው የአቶ ሀይለማርያም መንግስት ተመሳሳይ ፖሊሲ እያስፈጸመ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment