FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, March 2, 2013

እኛ የኢህአዴግን ጠመንጃ እንፈራለን፤ ኢህአዴግ ደግሞ 97 ላይ የመጣበትን የህዝብ ጎርፍ ይፈራል


ያለማመንታት ፕ/ር መረራ ‹‹ፖለቲከኛ ናቸው›› ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞአቸውም እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁርነታቸውና እንደፖለቲከኛነታቸው በሚያደርጉት ተሳትፎአቸው ይታወቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ደግሞ በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ በግልፅነታቸውና በቀልድ እያዋዙ ተናጋሪነታቸው ነው የሚታወቁት፡፡ በፖለቲካ የተሳትፎ ህይወታቸው የሚጀምረው አምቦ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ እያሉ ነበር፡፡ የንጉሱን አገዛዝ ለመጣል ከተንቀሳቀሱት አፍላ ወጣቶችም አንዱ ናቸው፡ ፡
imagesበወቅቱ የ66ቱ አብዮት እውን ቢሆንም አብዮቱ ብዙዎቹን ሲበላ እሳቸው ‹‹በዕድል›› በሚሉት ከበርካታ የሞት አጋጣሚዎች አምልጠዋል፡ ፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ሆነው ግን ከደርግ ጨካኝ የብረት መዳፍ አላመለጡም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ያለክስ በፖለቲካ እስረኝነት አሳልፈዋል፡፡ ባለፈው ዓመት አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ‹‹እርስዎ በግልዎ መታሰርን ይፈራሉ?›› ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹መታሰር… እእእ… ለመታሰር አልፈልግም፡፡ በደርግ ጊዜ ወደ ሰባት ዓመታት ስለታሰርኩኝ፤ እስር ምን እንደሆነ ስለማወቅ እስር መፍራት አለብኝ፡፡ ፍርሃቴ ግን ገደብ አለው›› ሲሉ ነበር የመለሱት፡፡ የ7 ዓመት እስራታቸው ደግሞ ዛሬ በብዙዎች ዘንድ ለሚታወቁበት በግልፅና በቀልድ እያዋዙ ተናጋሪነታቸው የህይወት ለውጥ ምክንያት እንደሆናቸው ነው ለኢትዮ-ቻናል የገለፁት፡፡ ‹‹የማክረር ፖለቲካን›› ያኔ ነው የተውኩት በማለት፡፡

ኢህአዴግ በ1983 አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄን ለማሳካት ፓርቲ አቋቁመው በሀገር ውስጥ ፖለቲካውን ትግል ተቀላቅለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ልዩ ሁነት የነበረው በ97 ምርጫ በትውልድ ሀገራቸው ተወዳድረው በማሸነፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመግባት የነበራቸው የ5 ዓመታት የፓርላማ ቆይታ ከአሁኑ ጋር ሲያነፃፅሩት በአንፃራዊነት የአሁኑ ‹‹ፓርላማው ፓርላማ አይመስልም›› ይላሉ፡፡ በሀገር ውስጥ የሚካሄደው ህዝባዊ ምርጫዎችን በተመለከተ ግን ‹‹ኢህአዴግ በምርጫ ጨዋታው ሜዳ ተጫዋችም፤ ዳኛም ነው የሆነበት›› ሲሉ ይተቹታል፡ ፡ አሁን ያለውን የምርጫ ሂደትንም ቢሆን የሚመለከቱትና ያላቸው አስተያየት ‹‹ነፃ›› እና ‹‹ፍትሃዊ›› አይደለም የሚልም ቢሆንም ዘወትር የሚጠቅሷት የጆሴፍ ሲታሊን አነጋገር መዋስን ይመርጣሉ፡፡ ‹‹ህዝብ ድምፅ ይሰጣል፤ እኛ እንቆጥራለን›› (People vote, we count) ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ከፖለቲካ ህይወታቸው ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲኤንኤን፣ ቢቢሲና ሬዲዮ ፍሬንች ኢንተርናሽናል፣ ጀርመን ሬዲዮ፣ ቪኦኤ፣ አልጀዚራ፣… እና ከሌሎችም ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ስላለው የፖለቲካ ሂደት ደግሞ ከኢትዮ- ቻናል ጋር ሠፊ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ!!
ኢትዮ-ቻናል፡- እንደመንደርደሪያ ጥያቄ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር ‹‹ጠቧል ወይም አልጠበበም?›› የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ፤ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል? ከ97 ምርጫ ወዲህ እስከአሁን ያለውን የፖለቲካ ሁነቶችን አብረው ቢያዩት?
ፕ/ር መረራ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው! እስከ 97 ድረስ በኢትዮጵያ ብዙ ነገሮች ይለኩ የነበረው በ66 አብዬት ነው፡፡ ከ97 በኋላ ደግም መለኪያው የ97 ምርጫ ሆኗል፡፡
በእኔ ግምት እጅግ በጣም አደገኛ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ነው የመጣው፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ለማንም በማይሆንበት ደረጃ የጠበበ ይመስላል፡፡ መንግስትም ቢሆን ‹‹ጨዋታው ዴሞክራሲ ነው›› ካለና በተወሰነም ደረጃ ለዚያ መንገድ እስከከፈተ ድረስ
የጨዋታውን ህጐች ማክበር አለበት፡፡ ስለዚህ፤ ሁልግዜ የምታወራውና የምትሰራው ጨርሶ የማይገናኝ ከሆነ ‹‹ይደግፉኛል›› የምትላቸውንም ሰዎች የውሸት ጨዋታ ነው የምታጫውተው ማለት ነው፡፡ በመጨረሻው ላይ ግን ጨዋታው ይጠፋባቸዋል፡፡… (ሣቅ)…
አሁን ሁልግዜ ‹‹ምርጫ›› ይባላል፤ ምርጫ ግን የለም፡፡ በቅርጫ ደረጃ እንኳን የለም፡፡ ቅርጫ ቢያንስ በአቅምህ ትወስዳለህ፡፡ ብዙ ግዜ ‹‹ልማት›› ተብሎ የሚወራውም በሁለት ነገር ችግር አለው፡፡
አንደኛው፤ ‹‹ዳታውን ማነው የሚጋግረው?›› የሚል ጥያቄ አለ፡፡ በቅርብ ግዜ 11 በመቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 8 በመቶ ገደማ ዝቅ አደረጉ፡፡ ብዙ ሰዎችን ጠይቄያለሁ፣ ዳታውን የሚሰበስበው (Survey data) የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡ እነ አይ.ኤም.ኤፍ (IMF)፣… ወዘተ ሌሎችም ለናሙና (Sample) ወረዳዎችን ወስደው ትንሽ ማስተካከያ አድርገው ወይ ከፍ፤ ወይ ዝቅ ያደርጋሉ እንጂ ለራሳቸው ሠፊ ዳታ የሚሰበስብላቸው የለም፡፡ ለምሳሌ፤ መንግስት ራሱ ዳታዎችን ከየት ነው የሚያመጣው? የውሸት ዳታ ነው? አይታወቅም፡፡
ሌላው ደግሞ በዚህ የሚከብረው ማነው? በሚገኘው ገንዘብ አሊያም አለ በሚባለው ዕድገት ማነው ተጠቃሚው? እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉትን ህንፃዎችን ዞረህ ብታያቸው ማነው የሚገነባቸው?
ለምሳሌ፤ ከቆሻሻ መጣያ ሰብስቦ የሚበላ አለ፡፡ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት አንድ ግዜ ብቻ መብላትም አለ፡፡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የከበሩ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት ከሚፈለገውም በላይ ከብሮ… ለመኖር የቻለም አለ፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ጥቂቶች ብቻ ናቸው እየከበሩ ያሉት እያሉኝ ነው?
ፕ/ር መረራ፡- አዎ! አከባበራቸው ምንጩ ከየት ነው? ወደ መንግስት ተጠግቶ ነው የከበረው?… ይሄም ራሱ ጥርጣሬ ነው፡፡ ስለዚህ፤ አንድም የዳታ ጥያቄ አለ፡፡ የሚባለው ዕድገት በእውነትም አለ ወይ? ሌላው ደግሞ ወደላይ የሚያድገውና ወደታች የሚወርደው ማነው? ‹አለ› የሚባለው የሀገር ሀብትስ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እየተከፋፈለ ነው? ወይስ አንዱ እንደፈለገ በሀብት ባህር የሚዋኝበት፤ አንዳንዱ ደግሞ የሚበላው አጥቶ በሀገሩም፤ በምንም ላይ ተስፋ የሚያጣበት ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው?
ኢትዮ-ቻናል፡- የዘንድሮው የ2005 የአካባቢ ምርጫ መድረክን ጨምሮ ወደ 28 ያህል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውድድሩ ወጥተዋል፤ በአጠቃላይ ‹‹ተስፋ አስቆራጭ ነው›› እያሉ ነው፡፡ ይሁንና፤ ከውድድሩ በተስፋ መቁረጥ ከመውጣት ቢያንስ በጠባቡ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶች በመቋቋም የህዝብን ምርጫና ፍላጐት ማራመድ አይቻልም ነበር?
ፕ/ር መረራ፡- እኛም ‹‹የትኛው ይሻላል›› የሚለውን ነገር ብዙ ተከራክረንበታል፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ተከራክራችሁማ አቆማችሁ? እዚህ ላይ ህዝቡን ያለአማራጭ መተውስ አይሆንም ወይ ውሳኔአችሁ?
ፕ/ር መረራ፡- እሱንም ጭምር ነው የተከራከርንበት፡፡ በአጠቃላይ ትልቁ ችግራችን 97 ምርጫ ‹‹ቅርጫ›› ነበር የሚመስለው፡፡ የተፈለገውን ያህል የህዝብ ድምፅ ቢሰረቅም፤ ቢሰረዝም ግን ምርጫ ይመስል ነበር፡ ፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ባልታየ መንገድ ምርጫ የሚመስሉ ነገሮች ነበሩ፡ ፡ ከዚያ በኋላ ያለፈው የ2002 ምርጫ ታይቷል፡፡ ኢህአዴግ ያንን ዝም ብሎ የመውሰዱ ጥያቄ ሳይሆን እስከ ምርጫ 97 ድረስ ኢህአዴግ ‹‹ፈሪሃ እግዚአብሔር›› እንኳን ባይኖረው ‹‹ፈሪሃ ፈረንጅ›› ነበረው፡ ፡ ነውር የሚባልም ነገር ትንሽ ነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ነውር ተወ፡፡
ያ በሆነበት ሁኔታ ዓይንህ እያየ፣ ህዝቡን ደግሞ የምርጫ ስርቆትን ማለማመድ ውስጥም መግባት ሆነብን፡፡ ለምሳሌ፤ ዓይንህ እያየ ድምፅህ ተሰርቆ፣ ተዘርፎ ሲሄድ ዝም ካልክ፤ ነገም ያ ጨዋታ ይቀጥላል፡፡
ስለዚህ፤ ዝም ብለን ህዝቡን ይዘን ብንሄድ፤ ያው እንግዲህ የሚጐዳውን ታውቃለህ? 2002 ምርጫም ቢሆን እኔ የተመረጥኩበት ቦታ ሰው ተገድሏል፡፡ ጊንጪም ላይ ተገድሏል፡፡ እዚያው አካባቢ አንድ ወጣት እንደውም ነውር በሆነ መንገድ ኢህአዴግ ገድሎ ‹‹የራሴ አባል ነው›› ብሎ በሞተ ሰው ስም የመታወቂያ ወረቀት ሁሉ ሰርቶ ነበር፡ ፡ የሚገርመው ልጁ የእኛ አባል ነው፡፡ አባቱ ለቪኦኤም፣ ለአሜሪካ፣ ለእንግሊዝ፣ ለዲፕሎማቶች መጥቶ ቃል ሰጥቷል፡፡ ‹‹ልጁ የነ መረራ ነው፤ የተገደለው በሚሊሺያ ነው›› የሚል ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን ‹‹የእኛ አባል ነው፤ በካንሰር ነው የሞተው›› ብሎ ነበር፤ በሚዲያ ሲያቀርብ የነበረው፡፡ ልጁ ወደ 23 ዓመቱ አካባቢ ነው፡፡ የታሰረ፣ የተደበደበ ብዙ ሰው አለ፡፡ ይሄ ሁሉ ‹‹ምርጫ አለ›› ብለህ፤ ህዝቡን ይዘህ መግባቱ ራሱ አንዳንድ ሰዎች የሚሉትን ሳይሆን ተቃራኒውን የማምጣት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ የራሺያ መሪ የነበረው ጆሴፍ ስታሊን ብዙ ግዜ የሚለው (You vote, we count) ‹‹እናንተ ትመርጣላችሁ፤ እኛ እንቆጥራለን›› ነው፡፡ ሁልግዜ ጨዋታው እንደዚያ ከሆነ መቆሚያ የለውም፡፡ እሱ ነው ያሰጋን፡፡
እኛ በምርጫ ቦርድ የአሰፋ ብሩ ዘመንን እንደ ‹‹ወርቃማ ዘመን›› ነው የምናየው፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ቢሮ ሲዘጋብን፣ ሰው ሲታሰርብን፣… አንዳንድ ነገር በዚያን ግዜ ታደርግ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ግን ምንም ነገር የለም፡፡
ለምሳሌ፤ 2002 ምርጫ ላይ ‹‹ማስረጃ የላችሁም›› አሉን፡፡ ከሁሉም በላይ ከአርሲ፣ ከአምቦ መስመር፣… ምርጫ ለመሰረቁ በጣታቸው አርሶአደሮች ድምፃቸውን ለእኛ የፈረሙበትና የምርጫ ቦርድ ማህተም ያለበት የድምፅ መስጫ ወረቀት ሁሉ ተሰብስቦ አስገብተናል፡፡ ያንን እያየ ‹‹ማስረጃ የላችሁም›› የሚለን ከሆነ፣ ምንድነው የሚቀረው? ስለዚህ፤ ትንሽም ቢሆን ‹‹እግዚአብሔር ምን ይለኛል?››፣ የሚል ዳኛ ካልሆነ ምን ለማድረግ ፍርድ ቤት ትሄዳለህ? ጨዋታው እኰ እሱ ነው፡፡ የኳስ ሜዳ ጨዋታ ላይ ዳኛውን ይዞ የገባ ቡድን፤ በፈለገበት ግዜ ቀይ ካርድ እያሳየ፣ ሲፈልግ ፊሺካ እየነፋ፣ ሲፈልግ ያልገባውን ‹‹ገባ›› ቢልም እኰ ምንም መከላከያ የለም፡፡ ኢህአዴግ ዳኛም፣ ተጨዋችም ነው የሆነው፡፡ እሱን ጨዋታ በሆነ መንገድ እንዲቆም ካልተደረገ በስተቀር አሁን ባለበት መንገድ መግፋቱ ችግር አለው፡፡
ስለዚህ፤ ምኑም፣ ምኑም በሌለበት ሁኔታ ዝም ብለህ ገብተህ ህዝቡንም፤ ራስህንም እያወቅክ የተዛባ ጨዋታ ዘላለም መጫወቱ ምንድነው ጥቅሙ? የሚለው ጥያቄ አለ፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ገፍተው ከነጭራሹ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲውን ለምን አትተውም›› የሚሉ አሉ፡፡ ‹‹ለኢህአዴግ ሽፋን ሆናችሁ›› ብለው፤ የሚነግሩን አሉ፡፡ በውጭ ብዙ ጠንካራ ክስ የሚቀርብብን በዚያ ነው፡፡ ‹‹ኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊ ለማስመስል ነው እንጂ ምንድነው እስቲ አሳዩን?›› ሲሉን፤ የምናሳየው የለም፡፡
በ 97 ላይ ከነበረው 172 መቀመጫ፤ በ2002 ወደ አንድ ነው የወረድነው፡ ፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ጨዋታውን ለራሱም፤ ለእኛም በማይሆን መንገድ እየገፋው ስለሆነ ሁለታችንም፤ ኢህአዴግም፤ እኛም ቁጭ ብለን ለማወቅ የምንችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በዚህኛው ምርጫ ላይ ለፖለቲካ ትርፍም እንኳን የማትጫወትበት ጨዋታ ስለሆነ መተው እንጂ ክርክሩ ነበር፡፡ አንተ በምትለውም መንገድ የተከራከሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- የ97 ምርጫ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምርጫ ሂደት ያበላሸና እናንተ ተቃዋሚዎችም ያበላሻችሁበት እንዲሁም ኢህአዴግ ግትር እንዲሆን ሊገፋፋ የቻለበትን ሁኔታ ፈጥራችኋል፡፡ ምክንያቱ ተቃዋሚዎች እናንተ ናችሁ ነው የሚባለው?
ፕ/ር መረራ፡- በአጠቃላይ ኢህአዴግ እስከ 97 ምርጫ ድረስ ‹‹በዱላም እያስፈራራሁ፤ ምንም እያደረኩኝ ኢትዮጵያን እገዛለሁ›› የሚል እምነት ነበረው፡፡ በተለይ፤ አርሶ አደሩ በዚያ ዓይነት ፍጥነት ይከዳኛል የሚል ግምት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ፤ የኢህአዴግ ጨዋታ ያ ነበር፡፡ በዚያ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በሚመስል ነገር ከዚያ በኋላ መጫወት እንደማይችል ተረድቶታል፡፡ ትንሽም ቢሆን በር ከተከፈተ (flood gate) የሚሉት ፈረንጆች፤ ጐርፉ ትንሽ ቀዳዳ ካገኘ ጐርፉ ይዞህ ይሄዳል፡፡ ያ ጐርፍ ይፈጠራል ብሎ ኢህአዴግ አልገመተም ነበር፡፡ ስለዚህ ጐርፍ ተፈጠረ፡ ፡ ያንን ጐርፍ ለማቆም እንኳን ባይሆን በተወሰነ ደረጃ ቀውስ ውስጥ ከመግባት አንዳንድ የራሱን ማስተካከያ ማድረግ ነበረበት፡፡ ኢህአዴግ ዋናው ትልቁ ስህተቱ ሥልጣን ለመካፈልም፤ ከሥልጣን ለመውረድም አልተዘጋጀም፡፡ ለሁለቱም ካልተዘጋጀህ ደግሞ ምርጫ ውስጥ የምትገባበት ምክንያት የለም፡፡ ዝም ብሎ ድሮ ኢትዮጵያ በተገዛችበት መንገድ መግዛት እንጂ ቢያንስ፣ ቢያንስ ሥልጣን ለመካፈል ከመጣብህ ወይም ካልሆነ ደግሞ ምርጫ ብለህ ከገባህ ሥልጣን እስከመልቀቅ ካልተዘጋጀህ ለፈረንጅ ጨዋታ ብለህ እዚያ ውስጥ መግባት ኢህአዴግ አልነበረበትም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መሆኑን አሸናፊ ቢኖር ሥልጣን ለማስረከብም ዝግጁ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ ይሄን አይስማሙበትም?
አብዬታዊ ዴሞክራሲን እናውቀዋለን፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ‹‹ፓርቲና መንግሥት አንድ ነው›› ይላል፡፡ የሥልጣን ክፍፍልን አይቀበልም፡፡ ያው በኋላ ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ብሎ የለጠፈበትን ቅፅል ለጥፎ መግዛት ይቻላል፡፡ ገባህ! ያንን ከማድረግ በዚህ የምርጫ ጨዋታ ውስጥ ገብቶ ቢያንስ፣ ቢያንስ ለመልቀቅም፤ ሥልጣን ለመካፈልም ካልተዘጋጀ ለምን ህዝቡንም፤ ሀገሪቷንም፤ ማንንም እዚያ ችግር ውስጥ እንደከተተ፣ ያ ሁሉ ህይወት እንዲጠፋ እንዳደረገ አላውቅም! ምርጫ ብለህ የሌለ ጨዋታ መጫወት አራዳነትም አይደለም፤ ምንምም አይደለም፡፡ ውሎ አድሮ ኢህአዴግን ይጐዳዋል፤ አሁንም ጐድቶታል፡፡ ቢያንስ ብዙ ግዜ ፈረንጆች የሚሉት Managed transformation or transition የሚል ነገር አላቸው፡፡ ራስህ እየተቆጣጠርክ ለውጦችን ማምጣት ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን ራሱም እየተቆጣጠረ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ የተወሰነ አንድ፣ ሁለት እርምጃ ወደፊት መጥቶ ብዙ እርምጃዎችን ወደኋላ ነው የተመለሰው፡፡ የሀገሪቷንም ፖለቲካ እንደዚያ ነው የመለሰው፡፡ ስለዚህ፤ የኢህአዴግ ትልቁ ስህተት እሱ ነው፡፡
ምርጫ 97 የአብዬታዊ ዴሞክራሲው ውስንነቱና የትም እንደማያደርስ የታየበትና የተፈተነበት ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን ያንን አውቆ ወደፊት ከመሄድ ብዙ እርምጃዎችን ወደኋላ መመለስን መርጧል፡፡
በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ሁለት ስህተት ነው የተሰራው፡፡ አንደኛው፤ መጀመሪያውኑ ሁለት የተቃዋሚዎች ቡድን ምርጫ ውስጥ መግባት አልነበረባቸውም፡፡ ስህተቱ ከዚያ ነው የሚጀምረው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ሁለት የተቃዋሚ ቡድኖች ሲሉኝ፤ እነማናቸው?
ፕ/ር መረራ፡- ማለት የዚያን ግዜ ቅንጅትን የፈጠሩ ኃይሎች ብዙዎቹ ከህብረት ነው የወጡት፡፡ መላ ኢትዮጵያም፤ ኢዴፓም ከህብረት ነው የወጣው፡፡ ስለዚህ፤ ለተወሰኑት ጥቃቅን ነገሮች ትርፍ ይገኙበታል ብሎ፣ የዚያን ግዜ የሁለት የተቃዋሚዎች ቡድን መፍጠር በኋላ ለተከተለው በአንድ አቅጣጫ እንዳናስብ ነው ያደረገን፡፡ ያ የሁለት ቡድኖች መፈጠር ሁላችንም ተሰብስበን እስር ቤት እንዳንገባ፣ ወይም ሁላችንም ተሰብስበን ፓርላማ እንዳንገባ ልዩነት ፈጥሯል፡፡
ሌላው፤ በተለያየ ደረጃ ህብረት በፍጥነት ሁኔታውን አይቶ ‹‹ብሔራዊ አንድነት መንግሥት›› ን ከምርጫ በኋላ አምጥቶታል፡፡ ከምርጫ በፊት ግን ኢህአዴግ ተሸንፎ ‹‹ሥልጣን አለቅም›› ካለ ምንድነው የምናደርገው? የሚለው ላይ ለክፉ ቀን የሚሆን ምንም ነገር አልተዘጋጀንም፤ አልተነጋገርንበትም፡፡ ያ ገጠመን፡፡ እውነታው መጣ፡፡ እውነታው ሲመጣ ‹‹ምን እናድርግ?›› የሚለው ነገር መጣ፡፡ እንደራደራለን? ተደራድረን ምን እናገኛለን? እንዴት ነው የምናመጣው? ስለዚህ ለተለያየ መልስ የሰጠነው ለዚያ ነው፡፡
አሁን ለምሳሌ እኔን ብትጠይቀኝ ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድን ‹‹አልቀይርም›› ብሎ የሙጢኝ ያለው፣ ለእሱ የመጠባበቂያ ካርድ (Reserved card) ነው፡፡ የመጨረሻው ቢመጣ ይህችን ካርድ መጠቀሚያ ትሆናለች፤ የተሸነፈውን ‹‹ኢህአዴግ አሸንፏል›› ብሎ ሊያውጅለት ይችላል፡፡ እሷን ይዞ ነው ጨዋታው ውስጥ የገባው፡፡ እሷን ባይዝ ኖሮ ጨዋታው ሌላ ይሆናል፡፡ ስለዚህ፤ ኢህአዴግ ሥልጣን ላለመልቀቅ መዘጋጀቱን በዚያ ነው የሚያሳየው፡፡ ከህብረት ጋር ባደረገው ድርድር ትዝ ይለኛል፡፡ ስንደራደር እሷ ላይ ‹‹እታረዳለሁ!›› አለ፡፡ ‹‹የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ላይ አትምጡብኝ›› አለ፡፡
ሥልጣን እንደማይለቅ በግልፅ ነው ምልክት የሰጠን፡፡ ስለዚህ፤ እኔ እንደአቅሚቲ ብዙ መቀመጫዎችን ለማግኘት እንጂ ኢህአዴግ ግን እንደማይወርድ አውቄያለሁ፡፡ ክርክሩም ላይ ትዝ ይለኛል፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ‹‹ኢህአዴግ ይወርዳል›› ሲል ‹‹አትቀልድ! ኢህአዴግ አይወርድልህም፤ ምርጫ ቦርድን ‹ዳኛ› ይዞ ነው ጨዋታ ውስጥ የገባው›› ማለቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ስለዚህ፤ ተቃዋሚው ኢህአዴግ ተሸንፎ ‹‹አለቅም›› ካለ፤ ‹‹ምን አደርጋለሁ?›› የሚለው ላይ፣ በተለይ በሁለቱ ካምፖች መካከል ስምምነት አልነበረም፡፡ እኛ ሰሜን አሜሪካ ሄደን ብሔራዊ አንድነት መንግሥት የሚመስል ነገር ከማስተዋወቅ ውጭ ከዚያ በኋላ ላሉት ጥያቄዎች በግልፅ የተነጋገርነው ምንም ነገር የለም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- እናሸንፋለን ብላችሁ አልተማመናችሁም ማለት ነው?
ፕ/ር መረራ፡- ቆይ!… ኢህአዴግ ምን መሰለህ? በዚያን ግዜ ይቅርና በ1992 ምርጫ ላይም ትዝ ይለኛል፤ ክርክሩ ላይ የተናገርኩት ‹‹ሌሎቹ ቦታዎች አይደለም፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ከአንድ መቀመጫ በላይ ካገኘ ኢህአዴግ ዘላለም እንዲገዛን እፈርማለሁ›› ብዬ ነበር፡፡ በ97 ያ ጐርፍ ተፈጥሮ ይቅርና ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ኢህአዴግ በገባበት ጨዋታ ኦሮሚያ፣ አማራ ይሸነፋል፡፡ አዲስ አበባም የመሸነፍ ዕድል ነበረው፡፡ ስለዚህ፤ በራሱ የኢህአዴግ ጨዋታ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ከመጣ የትም አያደርሰውም፡፡ ገባህ! ምክንያቱም የብሔሮች Support base በጣም ጠባብ ነው፡፡ ኢህአዴግ የብሔሮች ጨዋታ ነው የተጫወተው፡፡ በፈረንጆች Comparative advantage እንደሚባለው፤ ወደሌሎች ነው የሚሄደው፡፡
ለምሳሌ፤ ልክ የሽግግሩ መንግሥት ግዜ እኰ ኦነግና ኦህዴድን ስታወዳድር ምን አድርጐ ነው ኦህዴድ ኦነግን የሚያሸንፈው? ምንም የለም! ማለት እንግዲህ ኦሮሚያን ሊያጣ ነው፡፡ ምን አድርጐ ነው አማራን አካባቢ ይዞ ኢህአዴግ የሚያሸንፈው? እንዲህ ዓይነቶች ይመጡበታል፡፡ ችግሩ የኢህአዴግ ጨዋታ ራሱን በራሱ የሚወድቅበት (Self defeat) ጨዋታ ውስጥ ነው የገባው፡፡ 97 ይቅርና በ92 ምርጫ እንዳውም ኢህአዴግ እኔ ካልኩት በላይ ነው የመጣበት፡፡ የዚያን ግዜ እንኳን ‹‹አንዳንድ እንደ ተ/ ኃይማኖት አካባቢ አንድ፣ ሁለት መቀመጫ ያገኛል›› ነው ያልኩት፡፡ እና፤ የዚያን ግዜ እንኳን ኢህአዴግ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚሸነፍ አውቅ ነበር፡፡ በሽግግሩም ወቅት ከኦነግ ጋር በተጣላበት ግዜ ለምሳሌም ቢሆን ኦሮሚያን ኦነግ ያለምንም ጭንቀት ጠርጎ ለመውሰድ ይችል ነበር፡ ፡ ኢህአዴግ ጠመንጃውን ከጨዋታው ካወጣ ማለቴ ነው፡፡
በአብዛኛው አማራ አካባቢም ይሸነፋል፡፡ የዚያን ጊዜ የመሸነፍ እድሉ ጥያቄ ውስጥ አይደለም የነበረው፡፡ ጥያቄው ‹‹ኢህአዴግ ጨዋታውን እንዴት ያዛባል?›› ‹‹ምን ያህል ያዛባል?›› ነው፡፡
ኢህአዴግ በ97 እውነት የሚመስል ጨዋታ ውስጥ ገባ፤ በፈረንጁም ግፊት ማለት ነው፡፡
እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት ድረስ ኢህአዴግ ትላልቅ ናቸው የሚባሉት ባለስልጣኖች ሁሉም ለክርክር መጥተዋል፡፡ ክርክሩን ግን አልቻሉበትም፡፡ የለመዱት፤ እዚያ ካድሬዎች ጋር የሚያወሩት አለ አይደል? መልሶ የማይጠይቅ ካድሬን፣ ዲስኩር ስታደርግ ትውላለህ፤ መልስ ግን አይጠይቅህም፡፡ ‹‹እነዚህን ድንቅ ስራዎች ሰርቼያለሁ›› ብለህ ትሄዳለህ፡፡ አፍን ሞልቶ መናገር ከሚፈልግ ተቃዋሚ ጋርና ከሚችል ተቃዋሚ ጋር ስትወዳደር ግን ጨዋታው ይለወጣል፡፡ ለኢህአዴግ ጨዋታው ተለወጠበት፡፡ ያንን አልቻለም፡፡
ኢህአዴግ በተለይ አርሶ አደሩን በዚያም፤ በዚህም ተብትቦ ይዟል፡፡ በዚያ ፍጥነት አርሶ አደሩ ‹‹ይክዳል›› የሚል እምነት አልነበረውም፡፡ ‹‹እኔ ትዝ ይለኛል ቀን- ቀን የኢህአዴግ ካድሬዎች እየዞሩ ‹‹እንግዲህ ንባችሁን፣ ማራችሁን እንዳትረሱ!›› ይሏቸዋል፡፡ አርሶ አደሩ ደግሞ ቀን- ቀን ከኢህአዴግ ካድሬ ጋር ‹‹ማራችን፣ ንባችን!›› ይላል፡፡ ሌሊት፣ ሌሊት ደግሞ የእኛን ልጆች ‹‹በርቱ! ዘንድሮ ንብ ወደ ዝንብነት የሚለወጥበት ዘመን ነው›› እያሉ፤ ራሳቸው የእኛን ልጆች ሲያበረታቱ ነው የሚያድሩት፡ ፡ እንዲህ አይነት ጨዋታም በቀላሉ ይመጣብኛል የሚል ግምት አልነበረውም ‹‹ተቃዋሚ ከተማ ውስጥ ወይም አውሮፓና አሜሪካ ነው የሚጮኸው እንጂ አርሶ አደሩ ውስጥ አይደለም›› የሚል እምነት ነበረው፡፡ ምክንያቱም፤ አርሶ አደሩ ተማሪውን፣ አስተማሪውን፣… ይሰማል፡፡ በተለይ፤ ያ ክርክር ብዙ ቦታ ያጋጠመኝ ገበሬዎች ብዙ ስቧቸው ሬዲዮ ይዘው ነበር የሚዞሩትና የሚያርሱት፡፡
እና ለማለት የፈለኩት ምንድነው? ኢህአዴግ የነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ጨዋታ መጫወት የሚችልበት አቋም አልነበረውም፡፡ ከዚያ በኋላ ጨዋታው የሚቀጥልበትም መንገድ የለውም፡፡ ኢህአዴግ የነበረው ምርጫ ፈረንጆች እንደሚሉት managed transition ራሱ ለውጡን እየተቆጣጠረ ከለውጡ የተወሰነውን ዋስትና ሊያገኝ ይችል ነበረ፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ያለበት መንግስት (coalition government) አቋቁሞ እዚያ ውስጥ ሚናውን፣ በተለይ ሰራዊት እስካላቸው ድረስ የበላይነት አላቸው፡፡ ላቲን አሜሪካ ኒኳራጓ እንደዚያ ነው ያደረጉት፡፡ የሠራዊቱ መዋቅርና አንዳንድ ነገር እንዳይለወጥ ካደረጉ በኋላ ሌላውን ሲሸነፉ ለቀቁ፡፡ ተመልሰውም አሸነፉ፡፡ የተዛባ ጨዋታ ሌላው እንዳይገፋቸው ሠራዊቱን ቢያንስ፣ ቢያንስ እዚያ አካባቢ የተወሰነ ነገር ይዞ ብዙ ነገሮችን ይሰሩ ነበር፡፡ ለራሳቸውም፤ ለሀገራቸውም የሚጠቅም፡፡ አለበለዚያ ግን ‹‹ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ›› እያልክ፣ ዘላለም ደግሞ የጠመንጃ ጨዋታ እየተጫወትክ ውሎ አድሮ ይይዝኃል፡፡ ኢህአዴግም የመጣበት እሱ ነው ማለቴ ነው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- አሁን በሁሉም ነገር ላይ ኢህአዴግ ነው ተቃዋሚዎችን እየፈራ ያለው ወይስ ተቃዋሚዎች ናቸው ኢህአዴግን እየፈሩ ያሉት?
ፕ/ር መራራ፡- ሁለቱም ሊሆን ይችላል፡፡ ለተቃዋሚውም ኢህአዴግ ከጨዋታው ውስጥ ጠመንጃውን ካላወጣ ጨዋታውን መቀጠሉ አዳጋች ሆኖበታል፡፡ ሁልጊዜ ተቃዋሚው አካባቢ የሚታየው የኢህአዴግ ጠመንጃ እና የኢህአዴግ ሁከት እንጂ የኢህአዴግ የህዝብ ድጋፍ አይደለም፡፡ እሱ ግልፅ ነው፡፡ በዚያ ብታጣ ምንም ችግር የለውም፡፡ ህዝቡ ኢህአዴግን ደግፎ ኢህአዴግን ከመረጠ የዴሞክራሲ ጨዋታ ያ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹የሚቀጥለውን ጨዋታ እጫወታለሁ›› ትላለህ እንጂ ሌላ ነገር ውስጥ የምንገባበት ብዙ ነገር የለውም፡፡
ስለዚህ ተቋዋሚውም ኢህአዴግ ከጨዋታው ውስጥ ጠመንጃውን ካላወጣ ሁልጊዜ ምርጫ ውስጥ በገባህበት ጊዜ እኛ እንደጦርነት እኮ ነው የምናየው፡፡ ለምን እዋሻለሁ! ምክንያቱም፤ ሰው ይታሰርብሃል፣ ይደበደባል፣ ቤቱ ይፈርስበታል፣… መዓት ችግሮች ነው የሚደርሱበት፡፡ መለስተኛ ጦርነት ውስጥ ነው የምንገባው፡፡
እኛ፤ የኢህአዴግን ጠመንጃ መፍራት አለብን፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ያለጠመንጃው መጫወት አይችልም፡፡ ‹‹የጥፋት ኃይሎች ናቸው፤ ኢንተርሃሞይ›› ሲል ነበር 97 ክርክር ላይ፡፡ አንድ ሰው ያልገደለ ተቃዋሚን ‹‹ኢንተርሃሞይ›› ብለህ መክሰሱ ምንድነው ትርጉሙ? ለኢንተርሃሞይ ኢህአዴግ ነው ወይስ እኛ ነን የምንቀርበው? ስለዚህ ለኢንተርሃሞይ የሚቀርበው በየትኛው ኢህአዴግ ነበር፡፡ የፖለቲካ የውሃ ልኩን ለመጠበቅ ተቃዋሚውን መክሰስ ውስጥ ነው የገባው፡፡
እኛ የኢህአዴግን ጠመንጃ እንፈራለን፡፡ ኢህአዴግ 97 ላይ የወጣበት የህዝብ ጎርፍ ሊመጣበት ይችላል፤ ስለዚህ ያንን ይፈራል፡፡ ሁለታችን የየራሳችን ፍራቻ አለን ማለቴ ነው፡፡
ለምሳሌ፤ አሁን እኔ ሙሉ በሙሉ እዚህ አልነበርኩም፡፡ ለቅሶ ነበር አይደል? ቴሌቪዥንን በደንብ በቅርበት ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ የሚጮሁት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጩኸት እንጂ እምባ የለባቸውም፡፡ አሁን እኔን ያንን ገምት ብትለኝ፤ በትክክልም ለፍቅር የሚያለቅስ አለ፤ በፍርሃት የሚያለቅስ አለ፤ ለሆዱ የሚያለቅስ አለ፡፡ ለእኔ ሶስት ዓይነት ናቸው፡፡ አሁንም ኢህአዴግ ያንን መለየቱን አቅቶታል፡፡ አንዳንዶቹ ሊለዩ ይችላሉ፣ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ለማታለል ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ያ ግምገማ ነው እኔ ያለኝ፡፡
ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ምድር በሙሉ ለቅሶ በለቅሶ ሆኗል የሚባለው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውርስ (legacy) ይቀጥላል የሚባለውን፣ አንተ ‹‹ለምን ወጣችሁ?›› የምትለው ምርጫ ላይ እኔ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር፤ እንዲያውም ወርም አልፈልግም፤ በሁለት ሳምንት ለተቃዋሚ በሚዲያ መንቀሳቀስ ቢለቀቅ፣ ኢህአዴግ እርግጠኛ ነኝ ምናልባት አፋር፣ ጋምቤላ፣ አንዳንድ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር ‹‹ኢህአዴግ ነኝ›› የሚልባቸው ቦታዎች ትግራይ ጭምር ይሸነፋል፡፡ በእኔ ግምት ማለት ነው፡፡
ብዙ ነገር በስሏል፡፡ 97ን አውቃለሁ፤ ከበሮ መምታት ነው፡፡ ካድሬዎችን በየመስመሩ አሰማርተህ ከበሮ ብትደበድብ በሁለት ሳምንት ስራ ኢህአዴግ አንዳንድ ቦታዎች በዝረራ ይሸነፋል፡፡ ለምሳሌ፤ ኦሮሚያ ከአንድ ሳምንት ስራ በላይ የሚፈጅ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት አማራ አካባቢ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሁለት፣ ሶስት ሳምንት ሊፈጅብህ ይችላል፡፡ ሶማሌ አካባቢማ ከአንድ ሳምንት ስራ በላይም የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ደቡብ ወር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ሁለት ቀን በቂ ነው፡፡ በእኔ ግምት ማለቴ ነው፡፡ እና ኦሮሚያን ካሸነፍኩ ደግሞ ወይ አማራ፤ ወይ ደቡብን ከጨመርክ ይበቃናል፡፡ የግድ ሁሉንም ኢትዮጵያ፣ ትግራይን ጨምሮ ማሸነፍ የለብህም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- በትክክለኛ ምርጫ ኢህአዴግን አሁን ማሸነፍ ይቻላል ነው የሚሉት? አቅማችሁ ይሄንን መሸከም ይችላል?
አትጠራጠር ኢህአዴግ በሁለት ሳምንት ስራ ‹‹ይሸነፋል›› ነው የምለው፡ ፡ ይሄንን ኢህአዴግም የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ምድር ለቅሶ በለቅሶ የሆነው በሁለት ሳምንት ስራ በትክክል የዚያን ተቃራኒ የመፍጠር ሁኔታ ይኖራል፡፡ ልክ ቅንጅቶች 97 ላይ የፈጠሩት የለም? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው ‹‹ምርጫን ለማሸነፍ የግድ መስረቅ አያስፈልግም›› ብለው ነበር፡፡ በማግስቱ የተፈጠረው ለዚያ ሊሆን የሚገባ መልስ ነበር ለጠ/ሚ/ሩ የሰጠው፡፡ ኢህአዴግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን እንዲቀበል ለማድረግ ካልቻለ የትም አይደርስም፡፡ እኛም የትም አንደርስም፡፡ ኢህአዴግ የግድ ተደራድሮም፤ ምንም ብሎ ወደ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲመጣ ኢህአዴግን መግፋት ካልቻልን ጨዋታው የትም አይደርስም፡፡
ይልቁንስ፤ በመጨረሻ ላይ እኔ ስጋቴን ልንገርህ፡፡ ዩጎዝላቪያ የፈረሰችው፣ ነፍሷን ይማርና የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት የፈረሰችው በሁለት ነገር ነው፡፡ ‹‹የውሸት ምርጫ›› እና ‹‹የውሸት ፌዴራሊዝም›› ነው ሁለቱንም ያፈረሳቸው፡፡ ዴሞክራሲን ተወው፡፡ እኔ ኢትዮጵያም በውሸት ምርጫና በውሸት ፌዴራሊዝም እንዳትፈርስ ስጋት አለኝ፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ብዙውን ጊዜ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ የፖለቲካ ዕድገቱ ቆሟል ትላላችሁ ወይም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ራሱን ገድቧል ስትሉ ምን ለማለት ፈልጋችሁ ነው?
ፕ/ር መራራ፡- ኢህአዴግ መቆም የጀመረው በ83 በሽግግሩ ማግስት ላይ ነው፡፡ የሽግግሩ መንግስት ላይ የግል ሰርግ ነው ያደረገው፡፡ የፈለገውን ጋበዘ፤ የፈለገውን ተወ፡፡ በሀገር ደረጃ ማሰብ ያቃተው በዚያ ላይ ነው፡ ፡ እራሱን ከሠርጉ ወደ መንግስትነት ለወጠ፡፡ ምክንያቱም፤ ኢህአዴግ ያገኘውን (very impressive) አመርቂ የሆነ ወታደራዊ ድሉን ወደ ፖለቲካ ድል መለወጥ አልቻለም፡፡ አቃተው፡፡ በዚያ ነው የሚጀምረው፡ ፡ 83 ላይ ግማሽ ሚሊዮን ሰራዊት የሚባለውን የደርግ ሠራዊት አሸንፎ ኢትዮጵያን ሲይዝ በጣም አመርቂ የሆነ ወታደራዊ ድል አግኝቷል፡ ፡ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ በራሱም ምክንያት በሌሎችም ተቃውሞ ተሳክቶለታል ወደ ፖለቲካ ድል ግን መለወጥ አልቻለም፡፡ በዚያ ነው የሚጀምረው፡፡
እድገቱን ምናልባት የጨረሰው ደግሞ ህወሐት ለሁለት ሲከፈል፣ የኢህአዴግ ብሬይን ለሁለት ነው የተከፈለው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ለመኖር ነው የሰራው፡፡ አንድ ጊዜ ኪራይ ሰብሳቢ፤ አንድ ጊዜ ‹‹ቦናባርቲዝም›› ፣ አንድ ጊዜ ‹‹ልማታዊ መንግስት››፣ የሚሉ ቅፅሎች እየተጨማመሩ፣ መሬት ላይ ባለው እውነታ ላይ ምንም ነገሮች ሳይቀየሩ ማለት ነው፡፡
ኪራይ ሰባብሳቢነት ከተቃዋሚ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› ማለት የመንግስት ስልጣን ይዘህ ወይም ተጠግተህ ያለአግባብ ስልጣንን ከመጠቀም ነው የሚመጣው እንጂ ባዶ እጅ የሆነን ተቃዋሚ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ ነው›› ብትል ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ይልቁንስ ኪራይ ሰብሳቢነት የት ነው የተገኘው? ኢህአዴግ ቤት ነው፡፡ እውነታው ሲመጣ ገንዘቦቹ ውሃ ማከማቻና… ምናምን ውስጥ የተገኙት ኢህአዴግ ቤት ነው፡፡
ኢህአዴግ ትናንሽ ዓሣዎችን ሲያስር እናያለን፡፡ ትላልቆቹ በሙስና መዋኘታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የኢህአዴግ ብሬይን እንኳን ለሁለት ተከፍሎ አንድ ሆኖም ብዙ ማድረግ ያልቻለ ብሬይን ነው ለሁለት የተከፈለው፡፡ ስለዚህ ወደፊትም መሄድ፤ ወደኋላም መመለስ ያቃተው በዚያ ላይ ነው፡፡ ወደ ፊት ለመሄድ 97 ላይ ተሞከረ፡፡ እሱም የበለጠ አደናገጣቸው፡፡ እንደገና ተመልሶ በር ዘግቶ ነው ፖለቲካ መሥራት የጀመረው፡፡ እሱ እንግዲህ ሁላችንም የት እንደሚያደርስ አናውቅም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- በኢትዮጵያ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድም፤ በሌላም ጉዳይ በአብዛኛው አንድ አይነት አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች አንድ ላይ ተቀናጅተውና ጠንካራ መሰረት ይዘው የተበጣጠሰውን ኃይል ወደ አንድ መስመር ለማምጣት ችግር እንዳለባቸው ይነገራል፡ ፡ ይሄ ከምን የመነጨ ነው? በርካታዎቹ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ግንኙነታቸው ከመተማመን ይልቅ በመጠባበቅ ላይ የተመሰረተ ነው ይባላል፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ፕ/ር መራራ፡- የአቋም ልዩነቱ መኖሩ ያን ያህል አይደለም፤ ጨዋታውን ካወቁ ነው፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ሁለት አቅጣጫ ነው ያለው፤ ኢህአዴግ አካባቢ ያለ ችግር አለ፡፡ ተቃዋሚ በራሱም አካባቢ እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡
ከኢህአዴግ ልጀምር፤ ኢህአዴግ የቀጥታም ሆነ የስውር እጆቹ ተቃዋሚ እንዲዳከም ህገ ወጥ ስራዎችን ጭምር ይሰራበታል፡፡ በገንዘብ ይገዛል፡፡ ‹‹አሞሌ›› እና ‹‹ዱላ›› ነው ይዞ የሚሄደው፡፡ ለምሳሌ፤ ሌሎች ሀገሮች ኢህአዴግ የሚሰራቸው ህገ ወጦች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ አባል ህዝብ ዝም ብሎ በሆነ መንገድ ለጥፎ አንድ ጊዜ ‹‹ሽብርተኛ ነው››፣… ወዘተ እያለ፤ ውሸት መሆናቸውን እያወቀ፣ የሚሰራቸው መዓት ነገሮች አሉ፡ ፡ አሞሌና ዱላ ይዞ እየዞረ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የድርጅት አባሎችን ይገዛል፣ ስራ እንዳይሰሩ ያደርጋል፣ እዚያ ሁናችሁ ስሩልን ብሎ ብዙ ነገር ያደርጋል፣ ጠንከር ጠንከር ያሉትን ደግሞ ሽብርተኝነት እያለ በድርጅታቸው ላይ ይለጥፋል፡፡
ለምሳሌ፤ በቀለ ገርባ የሚባለው ልጅ ላይ የመሰከረበትን ልጅ እኔ አምቦ ስሙንም ጭምር አውቀዋለሁ፡፡ የእኛ አባል ነው፡፡ እና በእኔ ደረጃ የሚታወቅና በሺዎች የሚቆጠሩ የአምቦ ልጆች የሚያውቁት ልጅ ‹‹ወለጋ የሆነ ቡና ቤት ስራ አስኪያጅ ሆኜ ለስራ እዚያ መጥቶ ለኦነግ ቀስቅሶኛል›› ብሎ ነው የመሰከረበት፡፡ ልጁን አሁን አምቦ ብትሄድ ታገኘዋለህ፡፡ ሽፈራው አባይ ነው የሚባለው፡፡ ግን ሌላ ስም ቀይሮ ነው የመሰከረበት፡፡
መንግስት እንዴት ህግ ለማዛባት ብሎ የውሸት ምስክር ፍርድ ቤት ያቀርባል?
ስለዚህ፤ ኢህአዴግ በቀጥታም ሆነ በስውር እጆቹ፤ አሞሌም ይዞ በተቃዋሚዎች ላይ የሚሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ እኛኑ ጨምሮ አብዛኛው ተቃዋሚ እንቅስቃሴ በዚያ ችግር የተተበተበ ነው፡፡
ሁለተኛ የኢህአዴግ ችግር ሜዳውን ዘጋው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስም ተንቀሳቅሶ፤ ምሁር የሚባለውም ከፍርሃቱ ወጥቶ የሚሰራበትና ትግል ውስጥ ገብቶ ሀገርን የሚያገለግልበት ሁኔታ አልፈጠረም፡፡
አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እኔ የማውቀው 95 በመቶ በላይ buffer zone የሚባለው ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለመንግስትም እየሰራ አይደለም፡፡ ‹‹ለሆዱ አደረ፣ እንደ እንትና እሱም እንደዚህ ሆነ እንዴ!›› እባላለሁ ብሎ ይፈራል፡፡ ያፍራል፡፡ እንደገና ከተቃዋሚ ጋር እንዳይሰለፍ የመንግስትን ዱላ ይፈራል፡፡ ስለዚህ፤ ለሀገር እየሰራ አይደለም፤ የፖለቲካውን ዓለም በሚመለከት ማለት ነው፡፡ ‹‹ልጄን ላሳድግበት›› ብሎ፤ ክፍል ገብቶ መውጣት እንጂ ሀገሬን ለመለወጥ፣ ሀገሬን ለማሳደግ ልነሳ የሚል ምንም አይታይም ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ፤ የኢህአዴግ ጫና ተቃዋሚዎቹን እንዲያድጉ፣ እንዲጠናከሩ፣ ልዩነቶቻቸውን እንዲያቻችሉ፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ውይይት እንዲፈቱ እያደረገ አይደለም፡፡ ስለዚህ፤ እዚህም ጫናው አለ ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚዎቹም ደግሞ የየራሳቸው ችግር አለባቸው፡፡ ከድሮውም የፊውዳል ኢትዮጵያ የወረስነው አለ፡፡ አንተ ቅድም ያልከው አንዱ ሌላውን የመጠራጠርም አለ፡፡ ብዙ ስልጣን ሳይኖረው ፈረንጆቹ (aggregation interest) የሚሉት አለ፡፡ ፖለቲካ ስትሰራ የፍቅር ጥያቄ ሳይሆን አንተም እኔም ጥቅም አለን፤ እነዚያን ጥቅሞችን ለማስከበር መተባበር አለብን ነው፡፡ አንዱ ሌላውንም እየጠላም ቢሆን፡፡ ክሊንተን ያደረገችው እሱን ነው፡፡
ኦባማን ስትከስ ነበር፡፡ ‹‹እስላም ነው፤ ጥቁር ነው›› እያለች፤ በቀጥታም፤ በተዘዋዋሪም ማለት ነው፡፡ ግን ኦባማ ማሸነፉን ሲያውቅ ዴሞክራቲክ ፓርቲው ‹‹በይ አንቺም ሂጂና አገልግይ!›› ስትባል፤ ይኸው አምስት ዓመት ከማንም ያላነሰ ስታገለግለው ቆየች፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲው ፍላጎቱም አለ፤ እንደዚያ የሆኑት አንድ ላይ ሆነው እንዲሰሩለት፡፡ ኦባማ ያንን ሁሉ ቀውስ ችሎ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሸነፍ የቻለውም ለዚህ ነው፡፡
እኛ እንደዚህ አይነት ባህል የለንም፡፡ አንዱ ሌላውን የመግፋት እንጂ አንተም ጥቅምህን ለማስከበር፤ እኔም ጥቅሜን ለማስከበር ወይም ጥቅሞቹን ወደ አንድ የተሻለ የላቀ የጋራ ጥቅም ለመለወጥ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል የተነሳ ችግር አለ፡፡
ሌላው፤ ሁለት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጫፎች አሉ፡፡ ትልቁ ችግሩ እዚያ ላይ ነው፡፡ አንዱ፤ የኦሮሞ ብሔርተኞች የሚመሩት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የአማራ ብሔርተኞች ያው በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ስም የሚመሩት ነው፡፡ የትግራዩ ብሔርተኝነት ግልፅ ነው፡፡ ጥቅሞችን አግኝቷል፤ የትግራይ ልሂቃን (Elites) የሚባሉት፤ ሰማይ ምድር ገብተው እሱን ለመጠበቅ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር ይወቀው እንጂ ለዛሬው እሱ ነው ዋናው ስራቸው፡፡ ነገር ግን የእነዚህ የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን ሁለቱን የኢትዮጵያ የሀገሪቷን የፖለቲካ ጫፎች ይዘዋል፡፡ በዚያም ሆነ በዚህ ደግሞ ሰፊ ድጋፍ አላቸው፡፡ ስለዚህ፤ እነዚህ ሁለቱን ጫፎች ወደ መሀል መንገድ ለማምጣት ጎትተን፣ ጎትተን እስከአሁን አልተሳካም፡፡ ለእኔ ማለቴ ነው፡፡
የኦሮሞ ልሂቃን የሚባሉት አሁንም ቢሆን ብዙ ቦታ ኢትዮጵያ የምትባለውን መስማት አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለውን በሀገር ደረጃ ለውጦ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ አታይም፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት ከነበረው ሁኔታ ተለውጧል፤ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ግን አሁንም ቢሆን በበቂ ደረጃ ወደዚህ፤ ወደ መሀል መንገድ አልመጣም፡፡ ስለዚህ፤ ያንን ጫፍ ይዞ በብዛት የቆመ አለ፡፡ ቀላል ባልሆነ መንገድ ማለት ነው፡፡
የአማራ ልሂቃን የሚባለው ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያን የፈጠርኩ እኔ ነኝ›› በሚል አይነት፤ ከዚያም፤ ከላይም፤ ከታችም፤ ከዚህም፤ ከሁሉም ቦታ ‹‹እኛ የፈጠርናት ኢትዮጵያ ልትጠፋብን ነው›› ወደሚል፤ አንዳንድ ጊዜም ‹‹የኢትዮጵያዊነት ሠርተፍኬት ሰጪና ከልካይ እኔ ነኝ›› ብሎ፤ ራሱን ሰይሞ ማዶ ቆሟል፡፡ ‹‹እዚህ መሀል መንገድ መጥቼ እስቲ ከሌሎቹ ጋር ልገናኝ›› እና ‹‹የጋራ ሀገርን በጋራ የፖለቲካ አጀንዳ እንለውጥ›› የሚለው ለእነሱም የተሳካላቸው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ፤ እሱም ያለው ሌላ ጫፍ ላይ ነው፡፡
ለምሳሌ፤ እኔ ሰሜን አሜሪካ አንዳንድ ቦታ ስዞር በግልፅ አይቼያለሁ፡፡ ሌሎች ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እኛ በማናስበው በተለያየ መንገድም እያሰቡ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይሄንን ‹‹የጋራ ሀገር›› እና ‹‹የጋራ የፖለቲካ›› አጀንዳ ላይ መሀል መንገድ ላይ ተገናኝተን ይሄንን ነገር እንታደግ ወደሚለው አይመጣልህም፡፡ ስንት ቦታ ተበጣጥሶ ከእኔ የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ውሰድ ይልሃል፡፡ ያን ደግሞም የሚፈልግም ቢኖር ምናልባት ልቡ የሚፈልግ ብዙም ቢሆን በአደባባይ ወጥቶ የሚደረገውን አያደርግም፡፡ ስለዚህ፤ ለመሐሉ በሚሆን መንገድ ማሰባሰብ አልቻለም፤ ይሄ ካልተሰባሰበ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሰብስቦ አቅጣጫ አይዝልህም፡፡ በተቃዋሚ በኩል ማለት ነው፡፡ ይሄ ነው ብዙ ቦታ የሚገጥመኝ፡፡
ባለፈው ክረምት ለምሳሌ ሰሜን አሜሪካ ብዙ ከስዬ ጋር ዞሪያለሁ፡ ፡ ኢህአፓም የዛሬ 40 ዓመት ፋይል ይዞ ነው የመጣው፡፡ እንደዚያ ይዘው የመጡ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ‹‹እባካችሁ! በደቡብ አፍሪካ መንገድም ይሁን በሩዋንዳ መንገድም፤ በምንም መንገድ የጋራ የሆነች ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ስትፈጠር፣ ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሲፈጠር ነፃ ፍርድ ቤት ሲፈጠር እንዳኛለን፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ሂሳብ የማወራረዱን ፖለቲካ እናቁም፡፡ ሂሳብ ማወራረድ ከመጣ ሁሉም የየራሱ ሂሳብ አለው፤ ከሌላው ላይ የሚጠይቀው፡፡ እዚያ ውስጥ አንግባ›› ብል፤ ምን ብል እዚያው ላይ ነው፡፡ ገባህ! የዛሬ 40 ዓመት ህወኃትና ኢህአፓ አሲምባ ላይ ተዋጉ፤ ያሸነፈው ብዙ ጐዳ፣ የተሸነፈው ተጐዳ፡፡ እንደዚያ ነው፡፡ ከዚያ ነው የሚጀምረው ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ኦሮሞና አማራ ፖለቲካ ስትለውጠው የኦሮሞውም ልሂቃን የዛሬ ሁለት መቶ ዓመት፤ መቶ ሃምሳ ዓመት ያንን ሂሳብ ለማወራረድ ይፈልጋል፡፡ የአማራው ሊሂቃን ደግሞ ‹‹እንዴት ስለዚያ ሂሳብ ታነሳለህ፤ እንደውም የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ከእኔ ናና ውሰድ›› ይላል፡፡ ሂሳቡን አትጠይቅም ብቻ አይደለም፡፡ በአደባባይ የሚሉትን ተዋቸው፤ የሁላችንም አሠራራችንን ስትገመግም ያንን ታገኛለህ፡፡
ለምሳሌ፤ በእውነት ለመናገር የደቡብ ሊሂቃን ብዙ ችግር አላይባቸውም፡፡ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ችግር ውስጥ የገባችው በእኔ እምነት ከሁሉም በላይ በእነዚህ ሶስቱ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሞ ሊሂቃን በሚፈጥሩት ፍጭትና ግጭት ነው፡፡ ሀገሪቷን ወደሌላ አቅጣጫ እንጂ የጋራ አቅጣጫን ወደምንገፋበት አላመጣንም፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት በእሱ ላይ ነው የኖርነው፡፡ የድሮ መፅሐፍ ብታነብ የምታገኘው ይሄንኑ ነው፡፡ ስለወደፊቷም ኢትዮጵያ የጋራ አመለካከት ለመያዝና መፍትሔውም ላይ አንድ መሆን አልቻልንም፡፡
በአሁኑ ችግሮቻችን ዙሪያም የጋራ ግንዛቤ አጥተናል፤
ኢትዮ-ቻናል፡- ወደ መድረክ ስንመጣ ወደ ግንባርና ወደ ውህደት የመምጣት ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ እና እዚያ ላይስ አሁን የገለፁልኝ ችግር አያጠላበትም?
ፕ/ር መረራ፡- መድረክ ከዚያ ሲወጣ አሁን ካልኩህ ጋር ነው የሚገናኘው፡፡ ከስብሰባ ስትወጣ እኮ አሁን ካልኩህ ችግሮች ጋር ትፋጠጣለህ፡፡ እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ በስተቀር ችግሩ አለ፡፡
ለምሳሌ፤ ኢህአዴጐች ጋ ይሄዱና ‹‹እናንተ ሀገር አቀፍ ናችሁ፤ ከጐሳ ድርጅቶች ጋር ምንድነው የሚያስጨንቃችሁ? ግዜያችሁንም የምታጠፉት?›› ይላሉ፡፡ በዚያም፤ በዚህም የሚታየው ይሄ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ጋር ይሄዱና ደግሞ ‹‹ከነፍጠኞች ጋር ምን የጋራ ጉዳይ አላችሁ?›› ይላሉ፡ ፡ ኦህዴዶች የህወሓት አሽከር መሆናቸውን ይረሱና ጠዋትና ማታ ‹‹ብቻችሁን ብትሆኑ፣…›› ይላሉ፡፡ ስለዚህ፤ ያለውን የታሪክ አጥር በመስበር ብዙ ሰው የሚጠብቀውን ሥራ መሥራት አልቻልንም፡፡ ሙከራው አለ፤ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የምናወራበትም ግዜ አለ፡፡ ወጥተህ ከሰፊው ህዝብ ጋር በሀገር ውስጥም በውጭም ስትሰራ ጨዋታው ግን ቀላል አይደለም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ተመልሷል ይባላል፤ በርካታ በኦሮሞ ብሔር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች ግን አሉ፡፡ አሁንም እነዚህ በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ድርጅቶችን የሚያስታርቀው አመለካከት የትኛው ነው ብለው ያምናሉ?
ፕ/ር መረራ፡- የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥም ሁለት ጫፎች አሉ፡፡ እኛ እዚህ መሐል ነን፡፡ መሐሉን እንዲሰፋ ደግሞ እየገፋን ነን፡፡ በአንድ በኩል የመንግስት የገዥው ፓርቲ አሽከር ነው የምንለው ወይም የኦሮሞ ህዝብ አብዛኛው የሚለው ‹‹ኦህዴድ›› አለ፡፡ ጠዋትና ማታ የሚያስበው ኢህአዴግን ማገልገልና ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ እንዴት ይቆይ እንጂ የኦሮሞ ጥያቄ የሚባለውን፤ መጀመሪያውንም ያንን ይዞ መፈጠሩን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አሁንም ቢሆን ያንን እየገፋ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ብሔርተኞች ኦነግን ጨምሮ ሌሎች አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የሚባለውን የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ መያዝ አቅቷቸዋል፡፡ ያንን የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ለኦሮሞውም፣ ለተቀረውም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሻል የጋራ አጀንዳ መግፋትም አልተሳካላቸውም፡፡ ስለዚህ፤ እኛ እዚህ መሐል ነው ያለነው ማለቴ ነው፡፡
በአንድ በኩል ‹‹የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ተመልሷል፤ ድንቅ ሥራ እየተሰራ ነው፤ ለኦሮሞ ህዝብ ወርቅ እየተነጠፈ ነው›› ለማለት፤ የሚሞክሩ አሉ፡፡ የገዥው ፓርቲ እንደዚህ ቢሉም በግልፅ ስታገኛቸው ግን እንደዚያ አይሉም፡፡ ስብሰባ ላይ ግን ያንን ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ የሚባል ነገር አታንሱብን፣ ይሄ የጋራ አጀንዳ የሚባለው እየሰራ አይደለም›› ብለው የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ እኛ ደግሞ ‹‹የጋራ አጀንዳው መሰራት አለበት፣ የሁላችንም የተሻለ አማራጭ የሚሆነው ሁላችን በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ መፍጠሩ ይሻላል፡፡ ለኦሮሞውም፤ ለኢትዮጵያ …ህዝቦችም›› ብለን፤ የምንገፋ ነን፡ ፡ እነዚህ ሶስቱ መስመሮች አሉ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ሁለቱ ወደ አንድ መስመር የሚመጡበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህ፤ ቀላል ባልሆነ መንገድ፣ በእኛ በኩል እነዚህ የፖለቲካ ክፍፍሎች የተፈለገውን ያህል ወደፊት ሄዶ ውጤት እየመጣ አይደለም፡፡ ያ ነው ችግሩ፡፡ ‹‹ሙሉ በሙሉ ተመልሷል›› የሚሉም ደግሞ አሉ፡፡ ‹‹የልማት ግዜ ነው›› የሚሉ አሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የሚባል ነገር አያዋጣንም፤ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ ይሻለናል›› ብለው የሚንቀሳቀሱም አሉ፡፡ እዚህ መሐል ደግሞ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ነገር ግን የተሻለ የሚመስለው በዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው›› የምንለው አለን፡፡ ይሄ እንግዲህ ሶስት የፖለቲካ መንገድ ጉዞ እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ዶ/ር መረራ ብዙ ግዜ በፓርላማም ሆነ፤ መግለጫ ሲሰጡ ፖለቲካን እያዋዙ በቀልድ መልክ ነው የሚያቀርቡትና ይሄኛውን መንገድ እንዴት መረጡ? የሚናገራቸውን ተረቶችና ቀልዶች አስቀድመው ተዘጋጅተው እያሰቡ ነው የሚናገሩት ወይስ…?
ፕ/ር መረራ፡- አንተ የምትለው ነገር ከአምቦ የተማሪዎች ንቅናቄ ተጀምሮ እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም አልፌ፣ ሰባት ዓመት ታስሬ ስወጣ በጣም ካልተገፋሁ በስተቀር የጭንቀት ፖለቲካውን ትቼያለሁ፡፡ ትዝ ይለኛል ‹‹ወደድክም፤ ጠላህም መኢሶን ያሸንፋል!…›› እንዲህ ያለ ነገር በወጣትነታችን ጠንከር ባለ መንገድ ተከራክረናል፡፡ በዚያ ውስጥ የተለወጠ ህይወት ነው፡፡
አክርረህ የፈለከውን ያህል ብታቀርብ ዝም ብሎ ውሃ ልኩን አያልፍም፡፡ ስለዚህ፤ የማክረር ፖለቲካውን የተውኩት በተወሰነ ደረጃ በዚያ ሰባት ዓመት እስራት ነው፡፡ በእርግጥ፤ ብዙ ጊዜ ሞት አጋጥሞኛል፡፡ ከአምቦም፤ ደርግ ጽ/ቤትም፣ ቢያንስ ሶስት፣ አራት ግዜ ከሞት በዕድል አምልጬያለሁ፡፡ በተለይ፤ የአምቦ የዕድል ነው፡፡ እዚህ እነ ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ የሚባሉ ታላቅ ወንድሜን ጨምሮ ወደ 11 ሰዎች ሲያልቁ፣ እኔ አምቦ ለማስተባበር ሄጄ ነበር፡፡
ስለዚህ፤ በተለይ ላለፉት 40 ዓመታት የከረረ ፖለቲካችን የትም አላደረሰንም፡፡ ያ ያለፍንበት ሁለመናዬን ለውጦታል፡፡ በዚያ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ አንዳንድ ግዜ ማክረሩን እየተውክ ስትመጣ ወደ ተፈጥሮ ትሄዳለህ፡፡ ሰውም ሁልግዜ ዘላለም እያደረቅ ደረቅ ነገሮች ብቻ ስታቀርብለት ይሰለቸዋል፡፡ ከሁለቱ የመጡ ነገሮች ናቸው ለማለት ነው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ገዥው ፓርቲ ወይንም መንግስት ጥሩም ነገር ቢሰራ ተቃዋሚዎች ‹‹ጥሩ ሰርቷል›› ሲሉ አይሰሙም፡፡ እዚህ ላይ እርስዎስ ጥሩ ነገር ተሰርቷል ብለው የሚስማሙበት ነገር አለ?
ፕ/ር መረራ፡- ትልቁ ችግር የገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ኢህአዴግ አራዳ መሆኑ ነው፤ አጠቃላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ያበላሸው፡፡ ‹‹ኢህአዴግ መጥፎ ሰርቷል፣ እነዚህ እነዚህ ትክክል አይደሉም›› ሲባል ይቆርጥና ‹‹ኢህአዴግ ጥሩ ሰርቷል›› የሚላቸውን ብቻ በቴሌቪዥንም፤ በሬዲዬም፣ በጋዜጣም፣ ድሮ እፎይታ መጽሔትም በነበረ ግዜ ያስተላልፍ ነበር፡፡
በተለይ በጣም በሚያናድድ መንገድ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ችግሩ ከዚያ ነው የሚመጣው፡ ፡ ኢህአዴግ የተሻለም ሚዲያና ሌሎችም ነገሮች ያሉት መንግሥት ቢሆንም አሁን ለምሳሌ ‹‹ይሄ ጥሩ ነው፤ ይሄ መጥፎ ነው›› ሰው የሚለውን፤ ስለእሱ ‹‹ጥሩ ነው›› የሚለውን ብቻ እያቀረበ፣ ‹‹መጥፎ ነው›› የሚለውን እያወጣ፣ ፈልጦ የመቁረጥ አቀራረብ የፖለቲካ ባህሉን አበላሽቶታል፡፡
ወደ ተቃዋሚዎች በምትመጣበት ግዜ ዋናው ጥያቄያችን ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ያንን ስለማያደርግ እነሱም ደግሞ ለዚያ ተመሳሳይ መልስ የመስጠት ባህል ነው እየተፈጠረ ያለው፡ ፡ ኢህአዴግ ለምሳሌ፤ ‹‹ይሄ ተቃዋሚ እኮ እንዲህ ማለቱ ጥሩ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ደግሞ ጥሩ አይደለም›› አይልም፡፡ በሁለት በኩል የሀገሪቱን የሚዲያ አቅጣጫ ኢህአዴግ ተቆጣጥሮታል፡፡ ስለዚህ፤ ከዚያ ሳጥን ውስጥ ለመውጣት የሀገሪቷን የፖለቲካ ባህል መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ እሱ ደግሞ በዋናነት በመንግሥት እጅ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም፤ አስፈላጊ ያልሆነ፣ ዓይንህ ያየውን ነገር እንዲህ ነው ብትል አስፈላጊ ያልሆነ የፖለቲካ ዋጋ ነው የሚያስከፍልህ፡፡ የሞከሩ ሰዎች አሉ፤ አንተ በምትለው አቅጣጫ ማለት ነው፡፡
እኔ ቃለ-ምልልስ በማደርግበት ብዙ ግዜ የምጠነቀቀው ኢህአዴግ መርጦ በተዛባ መንገድ ቃለ ምልልሴን እንዳያስተላልፍ ነው፤ ጥረት የማደርገው፡፡ እኔንም እንደዚያ የሞከሩበት ግዜ ነበር፡፡
አንድ ግዜ ትዝ ይለኛል፤ ስለዓባይ የሆነች ልጅ ትጨቀጭቀኛለች፡፡ የሆነ መድረክ ላይ ‹‹ተይኝ›› ብላትም እምቢ አለች፡፡ ‹‹የዓባይን ነገር ለዓባይ ተይ›› የሚመስል ዓይነት ያለው ሃሳብ ስናገር እሱን ይዘው ስንት ግዜ ዞሩ፡፡ ገባህ!
አንተ የምትላቸውን ነገሮች በተመዛዘነ መንገድ ለህዝቡ ከማቅረብ ይልቅ ከዚያ የሆነ ነገር ካገኙ እሷን ይዘው ይሮጣሉ፡፡ ‹‹ይሄ ተቃዋሚ እኛን ተቀበለ›› ለማለት ነው፡፡ ያ ደግሞ ሰውዬው ተመልሶ እንዳይናገር ያደርጋል፡፡ ሰው ‹‹መጥፎ ነው፣ ጥሩ ነው›› የሚለውን፤ ሁለቱን ሚዛናዊ ያደረገ ነው ብዙ ግዜ መናገር የሚፈልገው፡፡ ግን ኢህአዴግ እነዚያን ነገሮች ጨዋ ባልሆነ መንገድ አበላሸው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- በአሁኑ ወቅት መንግስት ከሚከተለው ርዕዬተ ዓለም እናንተ እንደአማራጭ የምታቀርቡት ለዚህች ሀገር የተሻለ ነው የሚሉት ነገር አለ?
ፕ/ር መረራ፡- እኔ የሚሻለው ለእኛም፤ ለኢህአዴግም፤ ለሁሉም ጨዋታውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ‹‹ኮሚኒስት ፓርቲ እዚህ ሀገር ያዋጣኛል›› ካለ ኮሚኒስት ፓርቲ ሆኖ የማይንቀሳቀስበት ምክንያት የለም፡፡ ብዙ ሀገሮች አሉ፡፡ ፈረንሳይ ‹‹ሶሻሊስት ፓርቲ ነኝ›› ነው የሚለው፡፡ እ… ዋናው ጉዳይ ምንም ይበል ምን በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ አንድ የፖለቲካ ኃይልና ድርጅት ከተንቀሳቀሰ እንዲንቀሳቀስ መፍቀድ ነው፡፡ ይሄ ጨዋታውን ያስተካክለዋል፡፡ ህዝብ ከፈለገ ‹‹ኮሚኒስት ነህ፤ የተሻልክ ነህ፤ ለደሃ የተሻለ ትቀርባለህ›› ብሎ ይምረጥ፡ ፡ ግን ጨዋታውን ህዝብ በሰጠው ውክልና ደረጃ መስራት አለበት፡፡
ኢህአዴግ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ይበለው ዞሮ፣ ዞሮ ያው ነው፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ከነማኦ ሴቱንግና ኒው ደሞክራሲ የተወረሰና የመጣ ነው፡፡ እነ ሌኒን ኋላቀር በሆኑ ሀገሮች ሶሻሊዝምን ለመገንባት ይሄ ሥርዓት ያስፈልጋል ብለው ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ለእኔ ኢህአዴግ ያንን መከተሉ አይደለም፡፡ ሌሎቹን ፓርቲዎች ‹‹አማራጫቸውን ይዘው ይንቀሳቀሱ›› የሚለውን በር ካልዘጋው ነው፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ‹‹በራሴ ቁመት የተሰፋች ጥብቆ የግድ ከዚያ ውጭ ሰው መልበስ የለበትም›› የሚለው አካሄድ፤ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ጨዋታው አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ለምሳሌ፤ መድረክ ውስጥ አንተ በምትለው ደረጃ ‹‹ሶሻል ዴሞክራት ነን›› የሚሉ አሉ፤ ‹‹ሊበራል ዴሞክራት ነን›› የሚሉ አሉ፡፡ ‹‹ሁሉንም አንቀበልም›› የምንለው አለን፡፡ ግን ጨዋታው ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ፣ የዴሞክራሲያዊን ጨዋታ መቀበል ነው፡፡ ያንን ከተቀበልክ በኋላ ህዝብ ቢፈልግ አንተን ወይም እኔን ይምረጥ፡፡ የውድድር ዓለም ውስጥ በነፃ መግባቱ ነው፡፡ የውድድሩ ዓለሙ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ የመመራት ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ካለ ታሪክ የራሱን ጉዞ ይይዛል፡፡
ሊበራል ዴሞክራሲ እንኳን በሶስተኛ ዓለም አሜሪካ ውስጥም የለም ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም፤ በተወሰነ ደረጃ መንግሥት ሚናውን መጫወት አለበት፡፡ ኢኮኖሚ ውስጥ እጁን ያስገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኑር የሚባለው ሊበራል ዴሞክራሲ አሜሪካ ውስጥም የለም፡፡ መንግሥትም ሚና ያለበት የተወሰነ መመጣጠን ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ኃይሎችም ሶሻል ማህበረሰቦችም ሚናው አላቸው፡፡ ገቢያውም ሚና አለው፤ የግድ በጠመንጃ የምታዘው መሆን የለበትም፡፡ ለዚያ ተፈጥሮአዊ ጉዞ መንገዶችን መክፈት ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚሻለው የዴሞክራቲክ ጨዋታ ነው፡፡ ከእነ አርስቶትል ጀምሮ የተሻለ ሆኖ የወጣው ‹‹ደሞክራሲያዊ ጨዋታ›› የሚባለው ሲሆን ይሄ ደግሞ በህዝብ ድምፅ ላይ የተመሠረተ ነው፡ ፡ ህዝብ ከፈለገ ሳይገባውም፤ ገብቶትም ለራሱ የማይሆነውን ሊመርጥ ይችላል፡፡
ጠመንጃ ይዘህ ከመጣህ፤ ሌላውም ጠመንጃ ይዞ ይመጣል፡፡ ካስገደድክ፤ ሌላውም ላስገድድ ይላል፡፡ ጨዋታውን ካበላሸህ፤ ሌላውም ጨዋታውን ሊያበላሽ ይችላል፡፡ ህዝቡ ግን በራሱ መንገድ የራሱን የወደፊት ጉዞ እየመረጠ፣ እያስተካከለ፣ ስህተትም እየሰራ እንዲጓዝ ለህዝብ መብት መስጠት የግድ ነው፡፡ ለእኔ ርዕዬተዓለም ያን ያህል አያስጨንቀኝም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ጠ/ሚ/ር መለስ ጋር ተያይዞ ቅድምም አንስተውልኛል፤ በህይወት በነበሩበት ግዜ በቅርበት ተገናኝተው ሃሳብ ተለዋውጠው ያውቃሉ? እርስዎ የተሰማዎትን ስሜት እንዴት ይገልፁታል? የጠ/ ሚ/ር መለስ ያለመኖር ለእርስዎ የሚሰጥዎ ትርጉም ምንድነው?
ፕ/ር መረራ፡- ብዙ ነገሮች እዚያ ውስጥ ባልገባ ይሻለኛል፡፡ ያው በድርድር ወቅት በተደጋጋሚ ተገናኝተናል፡፡ ብዙ ባልል ይሻለኛል፤ በሁለቱም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ‹‹Ethiopia After PM Meles- potential for instability and implications›› የሚል፤ ጥናታዊ ወረቀት አቅርበው ነበር፤ ስለእሱ እስቲ ይንገሩኝ?
ፕ/ር መረራ፡- ወረቀቱን እንዴት እንዳገኘህ አላውቅም! ባለፈው ክረምት ፔይንስቴት ዩኒቨርስቲ ሌክቸር የሰጠሁት ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከመለስ በፊት፣ ኢትዮጵያ በመለስ ሥር፣ ኢትዮጵያ ያለመለስ›› እነዚህ ሶስቱን በማወዳደር ነበር ያቀረብኩት፡፡
በአጠቃላይ ለማለት የሞከርኩት፤ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታውን የለቅሶ፣ አንዳንድ ነገሮችን፣… አሳይቼ ‹‹ኢትዮጵያ በጣም አደገኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት፡፡ ወዴትም እንደምንሄድ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያን በመለስ ሥር አቅጣጫ ይታወቃል፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ብዙ ቦታ ያደርሰናል ተብሎ ብዙ መንገድ መጥተናል፡፡ ከዚያ የጠ/ሚ/ር መለስ መውጣት ሀገሪቷን ምናልባት ወዴት እንደምትሄድም? ማን ወዴት እንደሚሄድ ወዴት እንደሚመራ? አይታወቅም ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን›› የሚል ነው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ባለፈው እንደታየው ሱዛን ራይዝ በጠ/ሚ/ር መለስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ የተናገሩት ‹‹መለስ የራሳቸው ርዕዬተዓለም የላቸውም፤ ራዕይ እንጂ ለሀገራቸው ይጠቅማል ብለው እስካመኑበት ድረስ….›› ዓይነት ንግግር አድርገው ነበር (he was driven not by ideology, but by his vision of a better future for his land he loved) እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ፕ/ር መረራ፡- ሴትዬዋ ብዙ ነገር ነው የቀባጠረችው፡፡ ለምን እንደቀባጠረች እሷ ራሷ ነች የምታውቀው፡፡ አንዳንድ ግዜ ፈረንጆች በትክክልም ስለገባቸውም፤ ስላልገባቸውም ነገር ብዙ ነገር ያወራሉ፡፡ በትክክል ገብቷት አውርታ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- እርስዎ የሚያስተምሩት የመንግስት የትምህርት ፖሊሲ ተፈፃሚ በሚሆንበት ተቋም ውስጥ ነው፡፡ ለእርስዎ የማስተማር ነፃነትዎ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን? ከሥራዎ ውጭ በፖለቲካው በኩል የመንግሥት ተቃዋሚ በመሆንዎ በሚያስተምሩበት ወቅት የግል ስሜትዎ ሊንፀባረቅ የሚችልበት አጋጣሚስ የለም?
ፕ/ር መረራ፡- ቅድም ካልኩት የፖለቲካ ህይወት ስለወጣሁ ሁሉንም ወገኖች ማክረር ውስጥ አልገባም፡፡ ስለዚህ፤ ክፍል ውስጥ የምችለውን ያህል አስተማሪ ሆኜ ለመሥራት፣ ለማስተማር፣ ሳልጨነቅ ትክክል ያልሆነውን ‹‹ትክክል አይመስለኝም›› ፤ ትክክል የሆነውን ደግሞ ‹‹ትክክል ይመስለኛል›› በሚል ደረጃ ለማቅረብ ነው የምሞክረው፡፡
ተማሪዎቹንም የግድ እኔ ያልኩትን ሳይሆን ክርክሩን እስከአወቁ ድረስ የፈለጉትን የመከተል መብት አላቸው፡፡ የግድ ‹‹እኔ ያልኩትን ብቻ ነው መቀበል ያለባችሁ›› የሚል እምነት የለኝም፡፡
እንደውም፤ ባለሥልጣኖች የሚመስሉም እዚህ ነበሩ፡፡ የፖሊስ ኮሚሽነሩ የእኛ ተማሪ ነበር፡፡ የደህንነት ኃላፊው ወ/ስላሴ የእኛ ተማሪ ነበር፡ ፡ ብዙዎቹም እነሱም ክፍል ውስጥ ተማሪ ሆነው፤ እኔም እንደ አስተማሪነቴ ሚዛን ጠብቀን ነው ያሳለፍነው፡፡ ክፍል ውስጥ አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ የገባንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ ወ/ስላሴ የእኛ ተማሪ መሆኑን ያወቅኩት እንኳን ከእኛ ጋር ከጨረሰ በኋላ ነው፡፡
ስለዚህ፤ ክፍል ውስጥ ማን አለ? ማን የለም? በሚለው ጭንቀት ውስጥ አልገባም፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ ግዜ ከኦሮሞ ተማሪዎችና ሌሎችም ስለምኒሊክ ተጠይቄ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ምኒሊክን በአንድ በኩል A hero of all time ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ እነሱም ኢትዮጵያኖች ናቸው፡፡ Menelik was a cold blooded colonizer ብለው የሚያስቡም ነበሩ፡፡ እነሱም ቢሆኑ ኢትዮጵያኖች ናቸው፡፡ ግን ዝም ብሎ ድርቅና ሳይሆን ሁለቱንም ወገኖች ‹‹በየራሳችሁ ለምን እንዳላችሁና ጥያቄው ክፍል ውስጥ ማንሳት እስከቻላችሁ ድረስ እኔ ለምን ይሄን አላችሁ የሚለው ውስጥ አልገባም›› ነበር ያልኩት፡፡ ደግሞ ታያለህ ጐበዝ ተማሪና ሰነፍ ተማሪ የትኛውንም አቋም ቢይዝ የተሻለ ተማሪ የሚሆነውን ታውቃለህ፡፡ ጥያቄዎችን በየትኛውም መንገድ ቢመልስ በደንብ ታነባለህ፤ ይነበብልኃል፡፡
ዛሬ የማልናገረው ሰው የማስተማር የፖለቲካ ህይወቴን እንትን ያለው አለ፡፡ ሌላ ግዜ አወጣው ይሆናል፡፡ አሁን የሆነ ነገር እየፃፍኩ ነው፡፡ እና ያ ሰው በኢሠፓ ጊዜ ነው ለተማሪ በስምና የፖለቲካ አቋም እያየ ይሰጥ ነበር፡፡ እኔን ከዚህ ዩኒቨርስቲ ለማስወጣት የሆኑ ሰዎች ባያድኑኝ ኖሮ ሞክሮ ነበር፡፡ በግሬድ ማበላሸት ብቻ አይደለም፡፡ አንድ ግዜ እንደውም ‹‹የፖለቲካ ሞት ሞቻለሁ›› ብዬ፤ ቁጭ ብዬ ያለቀስኩበት ወቅት ነበር፡፡ በፖለቲካ አቋም ለተማሪ ግሬድ ላለመስጠት ተማሪ ሆኜ ነው የማልኩት፡ ፡ ለህሊናም የመጨረሻ ወንጀል መሆኑን ተማሪ ሆኜ ህይወቴን ሊያበላሽ በሚችል መንገድ አጋጥሞኝ ነበር፡፡ ይሄን በራሴ ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ፤ ማንም ይሁን ማን ክፍል ውስጥ የራሴን ለመናገር ጭንቀት የለብኝም፡፡ እስከአሁን ድረስ ልኩን ያለፈ መጥፎ ነገር ደግሞ አላጋጠመኝም፡፡
ለምሳሌ፤ እኛ ዲፓርትመንት አንድ ወጣት አስተማሪ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲያስተምር ተደብድቦ ነበር፡፡ እና የሚያስተምር ሰው ሲጠፋ ርዕሱን ለማስጨረስ እኔ ነኝ የተመደብኩት፡፡ ስለዚህ ተማሪ፤ ተማሪ ነው፡፡ አስተማሪ፤ አስተማሪ ነው፡፡ የራሴ ፖለቲካ ደግሞ ከካምፓስ ውጭ የራሴ ፖለቲካ ነው፡፡ ይሄን ሚዛናዊ ለማድረግ የሞከርኩ ይመስለኛል፡፡
አንድ ግዜ የቀድሞ ጠ/ሚ/ር ፓርላማ ውስጥ ‹‹የማስተማር ችግር ያለባቸው ሰዎች…›› አሉ ብለው፤ ተናግረው ነበር፡፡ ለነገሩ እኔም ‹‹ኧረ! እዚህም ብዙ ተማሪዎቼ አሉ›› ስል ልደቱም ‹‹እኔም አለሁ!›› ማለቱ ትዝ ይለኛል፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ብዙ ግዜ ውጭ ስለሚሄዱ በቅርበት ያውቁታልና ዲያስፖራው አካባቢ ያለው ስሜትና አመለካከት ለሀገር ውስጥ ፖለቲካ ያላቸው ስሜት እንዴት ነው? የተቀዛቀዘ ይመስላል ነው የሚባለውና በእውነት ተቀዛቅዟል?
ፕ/ር መረራ፡- ለእኛ ነው የቀዘቀዘው እንጂ በአጠቃላይ ፖለቲካው አይደለም፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ ለእኛ መቀዝቀዙ ምንም ጥያቄ የለውም፡ ፡ በተለይ፤ ፓርላማ ለገባነው ችግር ነበራቸው፡፡ ፓርላማ መግባታችን አሁንም አልተዋጠላቸውም፡፡
ስለዚህ፤ ለእኛ ሀገር ውስጥ ለምንቀሳቀሰው አንዳንድ ግዜ እንደው ‹‹ሠላማዊ ትግል ሳይሆን ሠላማዊ እንቅልፍ እየተኛችሁ ነው›› ብለው የሚከሱን አሉ፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ በሀገሪቷ ፖለቲካ አይደለም፤ መቀዛቀዛቸው፡፡ ሀገር ውስጥ ለምንቀሳቀሰው የፖለቲካ ኃይሎች ያላቸው ጥላቻ ነው የቀዘቀዘው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- አሁን በሥራ ላይ ያለው የህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት እርስዎን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የተመናመኑበት ነው፡ ፡ እርስዎ በነበሩበት ወቅት የነበረው የምክር ቤት ቆይታና አሁን ያለውን ሲከታተሉት ልዩነቱ እንዴት ነው? እርስዎስ ብኖር ኖሮ ብለው ሊያነሷቸው የሚፈልጓቸው አስተያየቶችና አጀንዳዎች ካሉ ቢጠቅሱልኝ?
ፕ/ር መረራ፡- በዚያን ግዜ ስገባ የነበረው ጠ/ሚ/ሩ በሚገቡበት ቀን ብቻ ነበር፡፡ በቀጥታ ስርጭትም ስለነበር አንዳንድ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻል ነበር፡፡ በዚያን ቀን ነበር የምገባው፡፡ እኔ በአጠቃላይ ኢህአዴግ ፓርላማውን ለምን ለመግደል እንደፈለገ አላወቅኩም፡፡ ለራሱም ጨዋታ፤ ለሀገሪቷም በአጠቃላይ የተቃዋሚዎች መኖር ይጠቅመዋል፡፡ ፓርላማውም ፓርላማ ይመስላል፡፡ በተለይ፤ ‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት እገነባለሁ›› የሚል ኃይል ያንን ሲያደርግ፣ የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍናውን አስገድዶ ሊሆን ይችላል፤ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
አንዳንድ የኢህአዴግ የፓርላማ አባላት የሆኑት የሚነግሩኝ ‹‹የእናንተ መኖር ይሻል ነበር፤ ቢያንስ እነሱ መጡ ብለን እንጠብቅ ነበር›› የሚሉኝ አሉ፡፡ የዚያን ግዜም አንዳንድ ነገሮችን ‹‹እናንተ አንሱልን፤ እኛ ማንሳት አንችልም›› የሚሉባቸው ግዜዎች ነበሩ፡፡
አንድ ግዜ ትዝ የሚለኝ በኢኮኖሚ ጥያቄ ላይ ከጠ/ሚ/ር መለስ ጋር የተጨቃጨቅን ዕለት፤ ብዙ ግዜ ተናግሬ ስጨርስ እንደማደርገው ወደ ኢህአዴግ አካባቢ ነው የማየው፡፡ ፊታቸው ምን እንደሚመስል፡፡ ‹‹የሚበላውን ያጣ ህዝብ፤ መሪዎቹን ይበላል›› ያልኩኝ ቀን ዞሬ አየሁ፡ ፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ የአንዱ የኦህዴድ ፊት ትዝ ይለኛል፡፡ ከልቡ በጣም ደስ ብሎት፤ ከልቡ ዓይን ለዓይን ተገጣጠምን፡፡ ይስቃል፡፡ ‹‹እኛ ብንሆን ይሄንን ይሄን መናገር አንችልም›› ዓይነት የሚል ይመስል ነበር፡፡
ዞሮ ዞሮ በዚህ ህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀስ ፓርላማ ነው፡፡ እጅ ማውጣትና ማውረድ ብቻ ሳይሆን ባሉት የሀገሪቱ ጥያቄዎች ላይ መከራከሩ፣ መነጋገሩ፣ በተወሰኑ ነገሮች ኢህአዴግንም ይጠቅም ነበር፡፡ ያንን ኢህአዴግ ለምን እንዳደረገው እግዚአብሔር ይወቀው!
የዚያን ግዜም ቢሆን ፓርላማ ነው ብዬ ሳይሆን መሠረታዊ የሆኑ የህዝብ ጉዳዬች ቢያንስ፣ ቢያንስ በቀጥታ በሚተላለፍበት እየተመጠነ የአንድ ደቂቃ፣ ሁለት ደቂቃ፣ ሶስት ደቂቃ በምትባለውም ቢሆን ማንሳት ይቻል ነበር፡፡ መነሳቱ ደግሞ ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ ‹‹የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል›› የሚለውን፤ ኢህአዴግን ምን ያህል፤ እንደከነከነው አቶ በረከት መፅሐፍ ውስጥ መረራ እንዲህ ብሏል ብሎ አስቀምጧል፡፡ ብዙ ከማውራት በአጭር ዐረፍተ ነገር መናገሩ ይቻላል፡፡ ይሄ መጥፋቱ ለሀገሪቷም ኪሳራ ነው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ፕ/ር መረራ፡- በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሞቱ በኋላ ችግሩ ማነው ሀገሪቷን የሚመራው? ወዴት እየመሩ ነው? አንድ ፈረንጅ፤ ‹ሄነን ላፎንቴን› የሚባል ፈረንሳዊ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመቃብር ማዶ ሆነው ኢትዮጵያን ይገዛሉ›› የሚል ጥሩ ፅሁፍ ፅፎ ነበር፡፡ የአሁኑ አመራር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚናው ምንድነው? አሁን ስብሰባ ሲሰበሰቡ እኮ ቴሌቪዥን ላይ ሲታይ፤ የሞቱት ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰበስቧቸው ነው የሚመስለው፡፡ በዚህ እንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹ትራንስፎርሜሽን››፣ ‹‹ሌጋሲ››፣… የሚባለው ነገር ይቀናቸዋል፡፡ ያለው የኢህአዴግ አመራር ምን እየመራ ነው? ምን እየሰራ ነው? ምን እያደረገ ነው? የሚለውም ጥያቄ ውስጥ ትገባለህ፡፡
ስለዚህ፤ በአጠቃላይ ያየሁት ያለው በዚያኛው ግዜ እንኳን አንድ አምባገነን (dictator) አለ፡፡ የሚፈልጋቸውን አንዳንድ ነገሮች የሚያደርግ፣ የሚያስር፣ የሚፈታ፣ አቅጣጫ የሚያሲዝ፣ የሚመራ፣… አለ ትላለህ፡ ፡ አሁን ደግሞ እሱም እንደሌለ ነው የምታየው፡፡ የኢትዮጵያን ስቴት ማሽኑን (State Machine) የሚያንቀሳቅሱት እነማን ናቸው? እንዴት እያንቀሳቀሱት ነው? ወዴት እያንቀሳቀሱት ነው? መቼም በሙት መንፈስ ዘላለም አትገዛም፡፡
ድሮ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚባለው ‹‹ዓፄ ምኒሊክ አራት ይሁን አምስት ዓመት ገዙ›› ይባላል፡፡ በዚያኛው ዘመን፣ በእሳቸው ስም ተችሏል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን በየቀኑ ነው የምትፈተነው፡፡ ስብሰባ ስታካሂድ፣ ስትመራ፣ የዓለም መሪዎችን ስታገኝ፣ ዜጐችን ስታነጋግር፣… ወዘተ በብዙ ነገሮች ነው በየቀኑ የምትፈተነውና፤ የምኒሊክ ዘመን አይደለም በሙት መንፈስ የምትገዛበት፡፡ ይሄን ሁሉ ታያለህ፡፡ ስለዚህ፤ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ለማወቅ ባልተቻለበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡
ኢትዮ-ቻናል፡- ፕሮፌሰር መረራ ከኢትዮ-ቻናል ጋር ላደረጉት ቆይታ ልባዊ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ!
በሳምሶን መንገሻ
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment