FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, March 13, 2013

ከእሁድ እስከ እሁድ


(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)
misraq harergie
የሟቾች ቁጥር ተደብቋል
በምስራቅና በምዕራብ ሃረርጌ ድርቅ በመግባቱ አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ዶይች ቬለ ሬዲዮ የአሜሪካን የርዳታ ድርጅት USAIDን ጠቅሶ ዘገበ። የድርጅቱ የምግብ አቅርቦት ተንታኝ ብሬክ ስታበረር እንዳሉት በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ በሶማሊና በኦሮሞ አርብቶ አደሮች መካከል ግጭት አስከትሏል።
በተፈጠረው የውሃ ችግር ምክንያት ከብቶቻቸውን ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ይዘው በሚሄዱ አርብቶ አደሮች መካከል የይገባኝልና ውሃና የግጦሹ ሳር ያልቃል በሚል ግጭት ተነስቷል። ተንታኙን የጠቀሰው ሬዲዮ በግጭቱ ስለደረሰው ቀውስ ያለው ነገር ባይኖርም ከተለያዩ ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሶማሊና ኦሮሞ አርብቶ አደሮች መካከል በተከሰተው ግጭት ከሰባ የማያንሱ ሰዎች ተገድለዋል።
የበልግ ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ችግሩ መከሰቱን ተመልክቷል። በዚሁ ሳቢያ ምርቱ ከጠጠበቀው በታች ሃያ ከመቶ ሊሆን ችሏል። የዝናብ እጥረቱ በዚሁ ከቀጠለ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው አስጠንቅቀዋል። ከብቶቻቸውን በመያዝ ምግብና ውሃ ፍለጋ የሚንከራተቱት አርብቶ አደሮች ከቤታቸው ርቀው ስለሚጓዙ ቤተሰቦች ወተት ማግኘት አልቻሉም። በአካባቢው ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘው የጫት ምርትም በውሃ እጥረቱ ጉዳት ደርሶበት አርሶ አደሮቹን ገቢ እያሳጣቸው ነው። መንግስት ተከሰተ ስለተባለው ድርቅ ያለው ነገር የለም። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በዘንድሮው ዓመት የሚጠበቀው ምርት ከፍተኛ ስለሚሆን ግሽበቱን ያውረደዋል በማለት ለፓርላማ መናገራቸው ይታወሳል። መንግሥት የምግብ እጥረት እንጂ ድርቅ የለም በማለት እንደሚከራከር የሚዘነጋ አይደለም።
የ“አባባ”ታምራት ንብረት ለባንክ ተሰጠ

(ፎቶ: ዕንቁ መጽሔት)
በሰው ግድያና በማታለል ወንጀል ሞት ተፈርዶበት የነበረውና በይግባኝ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮለት በማረሚያ ቤት የሚገኘው ታምራት ገለታ ወርቆች በየካራታቸው ተለይተውና ተጨፍልቀው ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መሆናቸውን በፌዴራል መንግስት የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አቶ አወቀ አበራን ጠቅሶ ለአዲስ አድማስ ዘግቧል።
የግለሰቡ የንብረት ጉዳይ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ በመድረስ የፍርድ አፈፃፀም ውሳኔ ካገኘ በኋላ የርክክብ ሂደቶቹ በኤጀንሲው በኩል ተፈጽሟል። ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ወርቆች በየካራታቸው ተለይተውና ተጨፍልቀው ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተገርገዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ ውስጥ የሚገኙት የግለሰቡ “አቢዶ” የተባለ ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴልና መጠነኛ መኖሪያ ቤቱን ኤጀንሲው የተረከባቸው ሲሆን ለማስወገድ ጨረታ እንደወጣባቸውም አዲስ አድማስ አስታውቋል።
“ዳይኖሰር”
“… በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምርጫ ሥርዓት “ዳይኖሰር” ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም በብዙ አገሮች እየጠፋ ነው ያለው፡፡ የምርጫ ሥርዓቱ በሥልጣን ላይ ላለ ፓርቲ የሚያደላ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሥልጣን በቀጣይነትና በቋሚነት እንዲይዝ ዕድሎችንና ሁኔታዎችን የሚያመቻች ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡ ከዚያ አኳያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲቀጭጩ ያደርጋል …”
ዶ/ር ያሬድ ለገሠ፣ የሕገ መንግሥት ተመራማሪ ታህሳስ21፤2005ዓም ለሪፖርተር ከተናገሩት የተወሰደ
ከየት አባቱ
እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል
እንባ ከየት አባቱ
ደርቋል ከረጢቱ:
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እያለቀሰች መከረኛ ነብሴ::
(በአሉ ግርማ “ኦሮማይ”) ከበዓሉ ግርማ መድረክ የተወሰደ
ከሐረር የጭካኔ ወሬ ተሰማ
በአረብ አገር የተለመደው በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው አደጋ በኢትዮጵያ ወገኖቻችን መፈጸሙን ሸገር አዲስ ገለጸ። ሸገር በዘገባው እንዳስታወቀው በሐረር አንደኛ መንገድ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ከቤቷ የወጣች የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ጨዋታ አታሏት መንገድ ትስታለች። የታዳጊዋን መደናገር የተመለከተች አንዲት ሴት ታዳጊዋን በወር 100 ብር ደሞዝ እንደምትከፍላትና ከእሷ ጋር ያለችግር እንደምታኖራት በማባበል አስረድታ ወደ

ቤቷ ትወስዳታለች ከሃያ ቀን በኋላ ታዳጊዋ ስራ እንደበዛባት በመግለጽ ወደ ቤቷ እንድትመልሳት ትጠይቃለች። ሸገር ታዳጊዋ በኦሮሚኛ ስትናገር በማሰማት እንዳመለከተው ሴትየዋ ታዳጊዋ ወደ ቤት እሄዳለሁ በማለቷ ሳቢያ ተናዳ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ቁልቁል ወረወረቻት። በአካባቢው ሰዎች ርዳታ ድሬዳዋ ሆስፒታል የደረሰችውን ታዳጊ ህክምና የሚከታተሉት ዶክተር እንደተናገሩት አስራ ሁለት ጥርሶቿ የረገፉ ሲሆን፣ እግሯ ከጉልበቷ በታች ተሰባብሯል።
ታዳጊዋ በአስተርጓሚ እንዳለችው ሴትየዋ “ራሴን ከፎቅ የወረወርኩት እኔ ነኝ በይ፣ ይሀንን ካደረክሽና ከእስር ነጻ የምታደርጊኝ ከሆነ ወርቅ እገዛልሻለሁ። ገንዘብ እሰጥሻለሁ” ብላኛለች ብላለች። ከሀረር የተሰማው ዘግናኛ ዜና በአረብ አገራት ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ ወደ አገር ቤት መዛመቱን ያመለከተ ነው። ሸገር ድርጊቱን የፈጸመችውን ሴት እምነትና ማንነት አልገለጸም።
ሜኔጃይተስ እንደ ሰደድ ተራባ
መንግሥት አልተነፈሰም
በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ቪኦኤ እንዳስታወቀው ሜኔጃይተስ የሚባለው አደገኛ ወረርሽኝ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። የዓለም የጤና ድርጅትን እንዳስታወቀው ወረርሽኙ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል አስራ አራት ዞኖችን፣ ስልሳ ወረዳዎችን አዳርሷል። በተለይም በአስራ ስድስት ወረዳዎች ወረርሽኙ የከፋ ነው።
አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለዜጎቹ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል። እንደ ቪኦኤ ዘገባ አሜሪካውያን የቅድመ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱና፣ ክትባቱን ከወሰዱ ከአስራ አራት ቀን በፊት ወደ ስፍራዎቹ እንዳያቀኑ መመሪያ ተላልፎላቸዋል። ቪኦኤ ጉዳቱን መጠን አልዘረዘረም። ከመንግሥት ወገን ያገኘውና ያስተላለፈውም መረጃ የለም። አገር ቤት የሚታተሙ የግል ጋዜጦችም በሳምንቱ መጨረሻ ያሉት ነገር የለም። ወረርሽኙ ተስፋፍቷል የተባለባቸው ቦታዎች ሃዋሳን ጨምሮ የቱሪስት ገበያ ያለባቸው ከተሞችን ያዳረሰ በመሆኑ በሆቴሎችና በቱሪዝም ገበያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለ። ከሁሉም በላይ ግን ወረርሽኙ ያስከተለው ጉዳት ይፋ አለመሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።
ተመስገን ደሳለኝ “ልዕልና” ይዞ ወደ ህትመት ተመለሰ
“ይህ ለአፈና እጅ የማይሰጥ የህዝብ ድምጽ ነው”
“ለዜጎች ክብር የማይሰጠው ኢህአዴግ፣ ህዝብ በሚከፍለው ግብር መልሶ የሚያፍነው ኢህአዴግ፣ የሀይማኖት ተቋማትን ወደ “አጋር ፓርቲነት” እየቀየረ ያለው ኢህአዴግ፤ ፍትህ ጋዜጣን እና አዲስ ታይምስ መፅሄትን በጉልበት ከነጠቀን በኋላ፣ ለሶስተኛ ጊዜ በሌላ ጋዜጣ ተመልሰናል” ሲል ተመስገን ደሳለኝ “ይህ ለአፈና እጅ የማይሰጥ የህዝብ ድምጽ ነው” በሚል ስም በሚታወቀው የፌስ ቡክ ገጹ አስታወቀ።
“ልዕልና” ተመስርታ አንዴ ከታተመች በኋላ መቋረጧን ያመለከተው ጋዜጠኛ ተመስገን የመንግስት ዕዳ ተከፍሎ፣ አሳታሚ ድርጅቱ የአገሪቱ የአክሲዮን ሽያጭ ህግ በሚያዘው መሰረት ወደ “እኛ” ተላልፋለች ብሏል። ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ “አርብ አርብ ይሸበራል” እንዲል ንጉሥ ቴዎድሮስ፣ ልዕልና ጋዜጣም የዕለት አርብ ድምፅ ሆና እንደምትቀጥል ተመስገን አመልክቷል።
በኢሚግሬሽን ጉቦ ነግሷል
የጉዞ ሰነድ የሚያዘጋጀው የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት በመንግሥት ታማኝ የደህንነት ሰዎች የሚተዳደር ቢሆንም በጉቦ መነከሩን ኢሳት የካቲት 28 ቀን 2005 ዓ ም ምንጮቹን ጠቅሶ ዘገበ። ኢሳት እንዳስታወቀው አገልግቱን ፍለጋ ወደኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት የሚሄዱ ዜጎች አስከ አምስት ሺህ ብር በነፍስ ወከፍ ይጠየቃሉ።
አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት፣ ለማሳደስ፣ የስም ስህተት ለማረም እና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከክልሎች ጭምር በየቀኑ በሺ የሚቆጠሩ አግልግሎት ጠያቂዎች ወደ አዲስ አበባው ኢምግሬሽን መ/ቤት ይጎርፋሉ። ጉዳያቸው ባስቸኳይ ስለማይፈጸም በገንዘብ እጥረት ጎዳና ላይ ለማደር ጭምር የሚገደዱ እንዳሉ ኢሳት አስታውቋል። በዚህ ምክንያት በርካታ ሴቶች ለመደፈርና ለዝርፊያ እየተዳረጉ ቢሆንም መ/ቤቱ አገልግሎት አሰጣጡን አሻሽሎ ቀልጣፋ ከማድረግ ይልቅ አንዳንድ ሰራተኞቹ በአካባቢው ካሉ ደላሎች ጋር በመሻረክ ቅድሚያ አግልግሎት ለማግኘት ከሚፈልጉ ግለሰቦች እስከ አምስት ሺ ብር የሚገመት ጉቦ በነፍስ ወከፍ እየተቀበሉ በማስተናገድ ላይ ናቸው ሲል ኢሳት ማህበራዊ አደጋውን በማካተት ዘግቧል።
በቦረና ባለስልጣናት በግና ገንዘብ ወሰዱ
በቦረና ዞን የኦህዴድ ባለስልጣናት ከ400 ሺህ በላይና በስጦታ የቀረቡ የበግ ጠቦቶችን መውሰዳቸው ተሰማ። ፍኖተ ነጻነት የካቲት 23 ቀን 2005 ዓ ም ባሰራጨው ዜና እንዳስታወቀው የተጠቀሰው የገንዘብና የጠቦት ስጦታ ሊወሰድ የቻለው በየስድስት ዓመቱ ለአባገዳው የሚቀርበው ስጦታ  ከህዝብ “እኛ እንሰበስባለን” በማለት ነው።
ድርጊቱ በዞኑ አመራሮችና በአባገዳው መካከል ልዩነት ያስነሳ መሆኑን የጠቆመው ጋዜጣው ጉዳዩን ለማጣራት ለቦረና ዞን አስተዳደር ማግኘት እንዳልቻለ፣ ለክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ጥያቄ አቅርቦ መልስ አለማግኘቱን አስታውቋል። አባገዳ በየትኛውም ጉዳይ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከመሆናቸው በላይ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የማይቀለበስ የክልሉ ባህል መሰረት በህዝብ ፍጹም ተቀባይነት ስላላቸው ጉዳዩ ሌላ ችግር ሊያስከትል እንዳይችል ፍርሃት እንዳለ ታውቃል።
የሳምንቱ ፎቶዎች
በአዲስ አበባ የሚገኙ የሕዝብ ስልኮች ያሉበትን ሁኔታ የሚያመለክተውን ፎቶ ያገኘነው ከፎርቹን ጋዜጣ ነው፡፡ በኔትወርክ ችግር መከራውን የሚበላው የሞባይል ስልክ መበራከት ነው ወይስ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ውጤት?
http://www.goolgule.com/briefs-20/

No comments:

Post a Comment