አቶ እንዳልካቸው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ሰብአዊ መብትን ከ 23 ባላነሱ አንቀፆች አካቶ መያዙን አስታውሰው በተግባር ግን በተዘዋዋሪ መንገድ በህገ መንግሥት የተጠቀሱትን መብቶች የሚዳፈሩና የሚሸረሽሩ ሌሎች ህጎች መውጣታቸውን ይዘረዝራሉ ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች መርኀ ግብር አስፈላጊ ቢሆንም ተግባራዊ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በምህፃሩ ሰመጉ ሃላፊና የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል አስታወቁ ። የሰመጉ ሃላፊ ና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የአመራር አባል ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ከልምድ እንደተገነዘቡት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ ህግ ማውጣት ሳይሆን በህገ መንግሥቱ የተደነገጉት ሰብአዊ መብቶች ተግባራዊ አለመሆናቸውና ይህንንም ተከታተሎ ማስፈፀም አለመቻሉ መሆኑን ተናግረዋል ። በተለያየ ደረጃ ውይይት የተካሄደበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች መርሃ ግብር በቅርቡ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀው ይቀርብለታል ተብሎ ይጠበቃል ። ሰነዱም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትና በሚኒስትሮች ምክርቤት ደረጃም እንደፀደቀ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ። ምንም እንኳን መንግሥት ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በመርሃ ግብሩ ላይ ማወያየቱን ቢገልፅም የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በምህፃሩ ሰመጉ ግን ለውይይት አለመጠራቱንና የተባለው ሰነድም እንዳልደረሰው የሰመጉ ሃላፊ አቶ እንዳልካቸው ሞላ ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የሥራ አስፈፃሚ አባልና የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባያፈርስ ድርጅታቸው የመርሃግብሩን ሂደት በመከታተል ላይ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል ። አቶ ጌታቸው ሌላው ቢቀር ሰመጉ ቢቻል ደግሞ ሌሎችም ወገኖች በውይይቱ ላይ ቢሳተፉ ጠቃሚ ይሆን ነበር ብለዋል ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች መርሃ ግብር ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአፍሪቃ ቀንድ ተጠሪ ፣ አምባሳደሮችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ፣ በተገኙበት ከትናንት በስተያ ምክክር ተደርጓል ። በዚሁ ምክክር ላይ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ማግኘታቸውና እንዲሁም የሰብአዊ መብት አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተናግረዋል ። ሆኖም ይህን የመንግሥት ባለሥልጣናት አባባል የሰመጉ ሃላፊ አቶ እንዳልካቸው ሞላ አይቀበሉትም ። አቶ እንዳልካቸው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ሰብአዊ መብትን ከ 23 ባላነሱ አንቀፆች አካቶ መያዙን አስታውሰው በተግባር ግን በተዘዋዋሪ መንገድ በህገ መንግሥት የተጠቀሱትን መብቶች የሚዳፈሩና የሚሸረሽሩ ሌሎች ህጎች መውጣታቸውን ይዘረዝራሉ ።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ባያፈርስ በኢትዮጵያ ህግ የማውጣት ችግር የለም ይላሉ ። ይሁንና በርሳቸው አስተያየት ችግሩ የህጉ አፈፃፀምና ክትትል እንዲሁም ህጉን የማስከበር ሃላፊነት ጉድለት ነው ። እነዚህ ሁሉ ጉዱለቶችና ክፍተቶች ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች መርሃ ግብር በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ እንደ መኢአዱ አመራር አባል አቶ ጌታቸው እንዳሉት ውጤት ያመጣል ተብሎ አይታመንም ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ
www.dw.de
No comments:
Post a Comment