FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, March 10, 2013

ሦስት የሊፍት መካኒኮች ከሰባተኛ ፎቅ ተከስክሰው ሕይወታቸው አለፈ


በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባምቢስ ሱፐር ማርኬት አጠገብ አፈወርቅ ኢንተርናሽናል ከሚያስገነባው ባለ 11 ፎቅ ሕንፃ፣ ከሰባተኛ ፎቅ ላይ የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም. የተከሰከሱ ሦስት የሊፍት መካኒኮች ሕይወታቸው አለፈ፡፡
ሕይወታቸው ያለፈው ሦስቱ ወጣቶች የባማኮ ኢንጂነሪንግ ቋሚ የወርክሾፕ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ተከስክሰው ሊሞቱ የቻሉት፣ የሕንፃው ግንባታ በመጠናቀቁና ሊፍት ፈታትተው ለማውረድ በመጡበት አጋጣሚ ነው፡፡
መካኒኮቹ ከ11ኛ ፎቅ ጀምረው ሊፍቱን እየፈቱ ሰባተኛ ፎቅ ላይ ሲደርሱ፣ ሊፍቱን ለመፍታት የሚረማመዱበት ርብራብ እንጨት በመናዱ መሆኑን በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ መካኒኮቹ ብርሃኑ ዓለሙ፣ ክፍሌ ዋቢና አህመድ መሐመድ የሚባሉ ሲሆኑ፣ ከሆሳዕናና ከወለጋ የመጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
መካኒኮቹ ሊፍቱን የሚፈቱት በተለያየ ርቀት ላይ ሆነው ስለነበር፣ የሚረማመዱበት የእንጨት ርብራብ ሲደረመስ ሁለቱ ምድር ላይ የተከሰከሱ ሲሆን፣ አንዱ ግን በሚገነባው ሕንጻ ስር የነበረ መኖሪያ ቤት ጣሪያ በስቶ በመግባት መኝታ ቤት አልጋ ላይ ማረፉን የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
አንደኛው መካኒክ ወዲያውኑ ሕይወቱ ሲያልፍ፣ አንዱ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ በመንገድ ላይ እንዲሁም ሌላኛው ሆስፒታል ደርሶ ሕይወቱ ማለፉን በሥራ ላይ የነበሩ የቀን ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ የሦስቱም አስከሬን ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልኮ ቀብራቸው መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡
ሕንፃዎች ሲገነቡ አስገንቢዎቹም ሆኑ ኮንትራቱን ወስደው የሚገነባው ተቋራጮች ሥራው ስለማለቁ እንጂ ስለሠራተኞች ስለማይጨነቁ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ በቀን ሠራተኞች ላይ አደጋ እየደረሰ መሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ፡፡ በሕንፃ ሥራ ላይ የሚሰማሩ ሠራተኞች አብዛኞቹ የአደጋ መከላከያ አልባሳትና ቁሳቁሶች ስለማይቀርቡላቸው የሠራተኞች ደኅንነት አደጋ ውስጥ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በተለይ ከሁለት ፎቅና ከዚያ በላይ ያላቸው ሕንፃዎች ሲገነቡ መወጣጫቸው ከእንጨት ስለሚሠራ፣ ሕንፃዎቹ እስከሚጠናቀቁም ስለማይታደስ በመበስበስና ክብደትን ባለመቋቋም እተደረመሰ የዜጎች ሕይወት እያለፈ በመሆኑ፣ የሚመለከተው የከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤት አንድ ሊለው እንደሚገባ አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል፡፡
ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment