FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, March 6, 2013

የጎልጉል ቅምሻ (ከዚህም ከዚያም)

alwaleed
“ሐብቴ ቢያንስ 20ቢሊዮን ፓውንድ ነው”
የዓለማችንን ባለጠጋዎች ዝርዝር በማውጣት የሚታወቀው ፎርብስ የተሰኘው መጽሔት የሳውዲ ንጉሥ አብዱላ ወንድም ልጅ የሆኑትን ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላል ያላቸውን ሃብት ዝቅ አድርጎ በመናገሩ ልዑሉ እጅግ ተቆጥተዋል፡፡
የሐብታቸው መጠን ቢያንስ 20ቢሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ እንደሚደርስ የተናገሩት ልዑል በደንብ ከተሰላ መጠኑ 29.6ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚደርስ አስታውቀዋል፡፡ ሮልስ ሮይስን፣ ፌራሪን እና ላምበርጊኒስን ጨምሮ ከ200 መኪናዎች በላይ ያሏቸው የ57ዓመቱ ልዑል ጣላል፤ በአውሮጳ እጅግ ውድ የሆኑ ሆቴሎችን ባለቤት ከመሆናቸው አልፎ እጅግ ትልልቅ የሆኑ ሁለት መርከቦች እና የዓለም ትልቁ የግል አውሮፕላን ጀት ባለቤትም ናቸው፡፡ በለንደኑ ሳቮይ ሆቴል፣ በአፕል ኩባንያ፣ በሲቲግሩፕ እና ኒውስ ኮርፕ ያላቸው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ዋጋው ዝቅ ተደርጎ እንደተገመተ ያስረዱት ልዑል ለሁኔታው ተጠያቂ ነው ያሉትን የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ከሥራው እንዲባረር ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩንም ፎርብስ ለመካከለኛው ምስራቅ ባለሃብቶች ያለውን የተጣመመ አመለካከት የሚያሳይ ነው በማለት ወንጅለውታል፡፡
በርካታ የዓለማችን ባለጠጋዎች የሃብታቸውን መጠን በይፋ ለመናገር ፈጽሞ የማይፈልጉ መሆናቸው እየታወቀ ባለበት ሁኔታ የልዑሉ ግልጽነት በርካታዎችን አስደምሟል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ሃብታቸው በትክክል ቢመዘን ኖሮ ከ26ኛ ደረጃ ወደላይ ከፍ በማለት ከሎሪዬል (የሽቶና ማስዋቢያ አምራች) ወራሽ ሊሊያን ቤተንኩር ቀጥሎ የ10ኛ ደረጃ ይጎናጸፉ ነበር፡፡
ከእስርቤት ወደ ሆቴልቤት
ቦታው ከዚህ በፊት ሰዎች የተቻላቸውን ሁሉ አድርገው ቢቻል መውጣት የሚመኙት ነው፡፡ አንድ ቀን እንኳን ማደር የማይፈልጉበት ነበር፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ እስረኞች የሚታሰሩበትና ላለፉት 150ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው በኔዘርላንድ የሚገኝ እስርቤት ፍጹም ማሻሻያ ተደርጎበት ወደ ሆቴልነት ከተቀየረ ወዲህ ግን ሰዎች በርካታ ቀናት የሚያድሩበትና ቢቻላቸውም ጨምረው መቆየት የሚፈልጉበት ቦታ ሆኗል፡፡
105 የእስረኛ ክፍሎች የነበሩት ወደ 40 ሰፋፊ ያጌጡ የሆቴል ክፍሎች ተቀይረው በክፍሎቻቸው ዘመን አመጣሽ ቲቪዎች፣ ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ … ከውብ መኝታዎቻቸው ጋር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ተጠቃሚዎችም ዳጎስ ያለ ገንዘብ በመክፈል ያድሩባቸዋል፡፡
ልማት፣ ሕዳሴ፣ … እያለ ሕዝባችንን የሚያደነቁረው ኢህአዴግ ከልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ የእስርቤት ግንባታውን ጉዳይ ቢሰርዘው ከሰማን እንነግረዋለን፡፡ በተለይ አሁን ደግሞ ሙስሊሞችን ጥያቄ አቀረባችሁ በማለት በገፍ እስርቤት እያስገባ ከሚያሰቃይና ተጨማሪ እስርቤቶችን ከሚሠራ ጥያቄያቸውን ቢመልስና ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ለቅቆ የኔዘርላንድን ፈለግ መከተል ከሁሉ የላቀው ህዳሴ ነበር፡፡
“ኪርዛኪስታን” – አዲሷ የጆን ኬሪ አገር
የአሜሪካ ፖለቲከኞች ለሌላው ዓለም ስምና አጠራር እምብዛም አይጨነቁም፡፡ አጣምመው፤ አወላግደው፤ … የአገር፣ የቦታዎችን፣ የመሪዎችን ስም ሲጠሩ ይሰማሉ፡፡
በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ጆን ኬሪ ሥልጣን ከመያዛቸው አንድ ወር ባነሰ ጊዜ አዲስ አገር ፈጥረዋል – “ኪርዛኪስታን” የምትባል! በቅርቡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ወዳጅ የሆነችውን ኪርጊስታንን እና የሰሜን ጎረቤቷ የሆነችው ካዛኪስታንን በመቀላቀል ኪርጊስታንን የጠሩ መስሏቸው ኪርዛኪስታን በማለት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አዲስ አገር አስተዋውቀዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ስህተቶችን በመስራት የሚታወቁት ጆን ኬሪ ከስድስት ዓመት በፊት በኢራቅ የሚገኙትን የአሜሪካ ወታደሮችን ዝቅ የሚያደርግ ቃል ተናግረው አያሌ ሕዝብ ተከፍቶባቸው ነበር፡፡ “ትምህርታችሁን በደንብ ከተከታተላችሁ፤ እንደሚገባው ካጠናችሁ፤ የቤት ስራችሁን ከሰራችሁ ጎበዝ ተማሪ ትሆናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ኢራቅ ተቀርቅራችሁ ነው የምትቀሩት” በማለት ነበር በወቅቱ ለመቀለድ የሞከሩት፡፡ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ብዙ ሲሉ እንሰማቸዋለን፡፡
1.6 ሜትር የጾታ ግድግዳ በየሱቁ
ሳውዲአረቢያ በምትከተለው ጥብቅ ሃይማኖታዊ ሕግ ምክንያት የቅርበት ዝምድና የሌላቸው ወንድና ሴት በሙሉ ተለያይተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ሰፋፊ ሱቆች 1.6ሜትር (5ጫማ ከ3ኢንች) ከፍታ ያለው ግድግዳ እንዲያቆሙ ታዝዘዋል፡፡ ወንድና ሴት ሠራተኞችን የሚቀጥሩ ሱቆች ይህንን ትዕዛዝ እንዲተገብሩና ሁኔታውንም ሃይማኖታዊ ፖሊሶች (ሙታዋ) እንዲያስፈጽሙ ተነግሯቸዋል፡፡
ሆኖም ጉዳዩ አሉባልታ ነው በማለት ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ባለሥልጣን ወንድና ሴት ሠራተኞች የሚቀጥሩ ሱቆች ሁኔታው እንዳመቻቸው የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ በማለት ጉዳዩን አጥላልተውታል፡፡ እስላማዊው ግዛተአጼ በሚከተለው ዋሃባዊ የሻሪያ ሕግ ምክንያት በሳውዲአረቢያ ሴቶች መኪና መንዳት የማይፈቀድላቸው ሲሆን በባንኮችና ቢሮዎች የራሳቸው የመግቢያ በር የሚጠቀሙ እንዲሁም በአለባበስ በኩል ጥብቅ ሥርዓት መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሰሜን አፍሪካ የአረብ ጸደይ የለውጥ ማዕበል ለዘመናት በሥልጣን የቆዩ መሪዎች ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ በሆነችው ሳውዲአረቢያ እጅግ መጠነኛ ለውጦች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡ ባለፈው ወር ንጉሥ አብዱላ በምክርቤታቸው አወቃቀር ላይ ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ 150 አባላት ከሚገኙበት የሹራ ምክርቤት 30 የሚሆኑት ሴቶች መቀላቀል ችለዋል፡፡
“ሒትለር በአመጋገቡ እጅግ ጠንቃቃ ነበር” ምግብ ቀማሹ
የአዶልፍ ሒትለርን ምግብ ለዓመታ ሲቀምሱ የነበሩ የ95ዓመቷ ጀርመናዊት ሒትለር በአመጋገቡ በኩል እንዴት ጠንቃቃና አትክልትና ፍራፍሬን በታማኝነት ይመገብ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ሒትለር በምግብ መርዝ እንዳይሞት ከፍተኛ ጥበቃ እንዲካሄድ በማስፈለጉ ይህንኑ የምግብ መቅመስ ጉዳይ እንዲያከናውኑ ከተመደቡት 12ሴቶች መካከል አንዷ የነበሩት አዛውንት ሲናገሩ “ከእኩለቀን በፊት ከ5 እስከ 6ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁላችንም ምግቡን እንቀምሳለን፤ ከዚያም ምግቡ ወደኤስ ኤስ ጠቅላይ ጽ/ቤት ይወሰዳል” ብለዋል፡፡ ምግቡ በሙሉ አትክልት እንደነበረና የሥጋ ምግብና አሣ ሲቀርብ እንደማያስታውሱም ገልጸዋል፡፡ ባሳለፏቸው ዓመታት ከባድ ፍርሃት ላይ ወድቀው እንደነበር የተናገሩት ሴት በሆነ አጋጣሚ ምግቡ ተመርዞ ቢሆን ኖሮ እንኳን የመቅመስ ግዴታ ስለነበረባቸው ቀምሰው ሊሞቱ ይችሉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የጀርመን ሕዝብ የአትክልት ተመጋቢ እንዲሆን ከፍተኛ ምኞት የነበረው ሒትለር ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ነድፎ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ የአትክልትን ብቻ ምግብነት የሚደግፉ ቡድኖች በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሥጋ ውጤቶች በኬሚካልና በሌሎች ሆርሞኖች እየተበላሸ በመምጣቱ የእንስሳትንም ሆነ የዶሮ ሥጋ ለምግብነት መጠቀም ለበርካታ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ይመክራሉ፡፡
“ስለ እናት”
ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ ያገኘነው ከዮሐንስ ሞላ ፌስቡክ (Yohanes Molla) ነው፡፡ ስለእናቱ የጻፈውን አጭርና እጅግ መሳጭ ጽሁፍ እንዳለ አቅርበነዋል፡፡ ዮሐንስ ለጽሁፉ ርዕስ ባለመስጠቱ “ስለ እናት” ብለን ሳናስፈቅድ ርዕስ በመስጠታችን እንደማይቀየመን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምስጋናችንም የላቀ ነው፡፡
“… በልጅነቴ ተድሬ ልጅነቴን ሳላውቀው አለፈኝ። ከዚያ በኋላ ግን ከጓደኞቼ ጋር… አሻሮ እየቆላን፣ እንኩሮ እያነኮርን እንጫወት ነበር። ስራችንን ከጨረስን ዝም ብለን እየተቀላለድን እንጫወታለን። እንዘፍናለን። እንጨፍራለን። ልጆች ነን፥ ዝም ብሎ መሳቅ መቀለድ ነው። ግን የግድ ማስተዋልም አለ።… ታዲያ ሁሉም ነገር መሽቶ ባሎቻችን ቤት እስኪመጡ ነው።… ከመሬት ተነስተው ስለሚመቱን እንፈራለን።
ያኔ ሳንቲም እንዳያጥረኝ መሸታ እጠምቅ ነበር። … መጥመቁን ከእናቴ የተማርኩት ነው። እናቴ ትነግዳለች፤ መሸታ ስለምትጠምቅ ብር አይቸግራትም ነበር። እኔም አንድ ልጇ ስለሆንኩ አይከብዳትም መሰለኝ በጣም ትንከባከበኝ ነበር። በልጅነቴ – 9 ዓመት ሲሆነኝ – ሞተች። ታዲያ ግን እርሷ የምትለውን ያምታደርገውን ሁሉንም አስታውሳለሁ። እንደሷ መሆን እፈልግ ነበር።…
ባለቤቴ የቀን ወጪ 30 ሳንቲም ይሰጠኛል። 30 ሳንቲም ብዙ ነው። ቡናውን፣ የቡና ቁርሱን፣ ወጡን፣ እንጀራውን፣ እንጨቱን፣ ሁሉንም በዚያው በ30 ሳንቲም ነው። እርሱን አብቃቅተን እንበላበትና ያልቃል።… ከሆድ አያልፍም ነበር። እንግዳ ቢመጣብኝ እንኳን አንድ ጣሳ ጠላ ገዝቼ ላስተናግድ ብል ስለማልችል ተጨማሪ ፍራንክ እፈልግ ነበር። ለዚያ ነው ጠላ የምጠምቀው። እንደዛ ስለማደርግ ሳንቲም አይቸግረኝም።
የብር ከሃምሳ ጠላ ብጠምቅ፣ ብር ከሃምሳ ትርፍ ያመጣልኝ ነበር። እንግዳ ቢመጣ አላፍርም፤ በደንብ ነው የማስተናግደው። ከጓደኞቼም ጋር አምስት አምስት ሳንቲም እናዋጣና እንጀራ፣ ጠላ ቆሎ ሁሉን ነገር ገዝተን እየበላን እየጠጣን እንጫወታለን። ጨዋታ ሳንጨርስ ስላገባን ዝም ብሎ መጫወት ያምረን ነበር። በየቀኑ ጨዋታ ነው።… እንደዚያም ሆኖ ግን ቤት አለ። የቤት ስራው አለ። ባል ይማታል። ልጅ ማሳደግ አለ።…
በ21 ዓመቴ 3 ልጆች ወልጃለሁ። ራሴ ግን ልጅ ነበርኩኝ። (ትስቃለች) እንኳን ልጅ ላሳድግ ጨዋታም ያምረኝ ነበር። መጀመሪያም ሳልፈልግ ስላገባሁ ሁሌ መፋታት እፈልግ ነበር። አባቴን በመጡ ቁጥር እጨቀጭቃቸው ነበር። ዛሬም አስፈቱኝ። ነገም አስፈቱኝ ነው። እርሳቸውም ‘ልጅነት ነው። ልጅ ስትወልድ ትተወዋለች።’ እያሉ በቀጠሮ ያራዝሙብኛል።
ብልህ ነበሩ፥ ቆይ ለፋሲካ፣ ቆይ ለመስቀል ይሉኛል። እኔም አልረሳም። እውነት መስሎኝ አስታውሼ እጠይቃቸዋለሁ። ለመስቀል ስጠይቃቸው – ‘ቆይ ለፋሲካ’ ይሉኛል። ለፋሲካ ሳስታውስ – ‘ቆይ ለገና’ ይሉኛል። እኔም ሳልረሳ እጠይቃለሁ። ታዲያ ሁለት ልጅ ተከታታይ ሞቶብኝ ሶስተኛውን ልጄ ሳይ የትም መሄድ አስጠላኝ። እንኳን አፋቱኝ ልል ከዚያ ቤት ሞት ይንቀለኝ አልኩኝ። ብማረርም መፋታቱን ማሰብ ተውኩኝ።
ታዲያ ተፋትቼ ቢሆን ኖሮ ይፀፅተኝ ነበር። ይሄን ሁሉ አላይም ነበር። ሳልፈልግ አግብቼ ከእግዚአብሄር ጋር ቤት ሙሉ ልጅ አሳደግሁኝ። … ፀጋው አይጓደል። ምን አጣሁ? ባጣም የማላውቀውን ነው።… ” ~ My Mom ♥

http://www.goolgule.com/sweet-golgul-10/

No comments:

Post a Comment