መጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በተለያዩ ፎቶግራፎቹ ከፍተኛ እውቅና ያተረፈው ጋዜጠኛ ቢንያም መንገሻ አገሩን ጥሎ ለመሰደድ የተገደደው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ እያወደማት መሆኑን በመገንዘብ፣ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው።
ጋዜጠኛ ቢንያም ከኢሳት ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለምልልስ በስልጣን ላይ ያለው ሀይል ኢትዮጵያ በመኖርና ባለመኖር መካከል ከትቷታል።
በመንግስት የተበላሸ ፖሊሲ የተነሳ ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ ምደረ በዳነት እየተቀየረች መሆኑን በፎቶግራፍ በማስደገፍ ለኢሳት ገልጿል።
ፎቶ ጋዜጠኛ ቢንያም መንገሻ በሪፖርተር ጋዜጣ እና በአቢ ዊክሊ መጽሄት ሲሰራ ከቆየ በሁዋላ፣ ያራሱን ግላመር ፎቶ ስቱዲዮ በማቋቋም ፎቶ ኢግዢቢሺኖችን ማሳየቱን፣ በዚህም ስራው፣ የአገሪቱን መልካም ገጽታ አበላሽቷል በሚል በደህንነት ሀይሎች ሲዋከብ እንደነበር ገልጿል።
ከጋዜጠኛ ቢንያም መንገሻ ጋር የተደረገው ቃለምልልስ በቅርቡ ይቀርባል።
እነ አቶ አያሌው ተሰማ ጥፋተኞች ተባሉ
መጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 8ኛው ወንጀል ችሎት የአያት አክሲዎን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አያሌው ተሰማ፣ የአክሲዮን ማህበሩ የፋይናንስና ኢንቨስትምንት ዳይሬክተሩ ዶ/ር መሀሪ መኮንን እና የፋይናንስ ዋና ክፍል ሀላፊ አቶ ጌታቸው አጎናፍር በተደራጀ መልኩ የባንክ ስራን ሲሰሩ በመገኘታቸውና በታክስ ማጭበርበር በፍርድ ቤት ጥፋተኞች ተብለዋል።
ተከሳሾች ከቀረበባቸው ክሶች ውስጥ በ21ዱ ጥፋተኞች ሲባሉ፣ የዱቤ አገልግሎት በማከናወን፣ በዱቤ የተሸጡ ቤቶችን ካርታ በመያዝ በእነዚህም ካርታዎች ከባንክ ብድር በመበደር ወንጀል መከሰሳቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
አክሲዮን ማህበሩ ከ1996 እስከ 2001 ባሉት አምስት አመታት ውስጥ 287 ሚሊዮን ብር ቢያንቀሳቅስም መክፈል የነበረበትን 8 ሚሊዮን ብር ታክስ አልከፈለም የሚል ክስ ቀርቦበታል። አንዳንድ ወገኖች መንግስት የተወሰኑ ብሄር ተወላጆችን ባለሀብቶች ሆን ብሎ እየመታ ነው በማለት እንደመከራከሪያ ከሚያቀርቡዋቸው ምክንያቶች አንዱ የአቶ አያሌው ተሰማ ጉዳይ ነው። ግለሰቡ እንደ ማንኛውም ሰው ተለቀው ጥፋት አለባቸው ከተባሉ እንኳ ስራአቸውን እየሰሩ እንዲከራከሩ ማድረግ ይቻል ነበር፣ በማለት ጉዳዩ ከታክስ ባለፈ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው እነዚህ ወገኖች ይከራከራሉ። በቅርቡ በተመሳሳይ የታክስ ማጭበርብር ተከሰው 4 አመታት ተፈርዶባቸው የነበሩት የሜጋው ም/ል ስራ አስኪያጅ አቶ እቁባይ በርሄ ከአንድ ሳምንት የእስር ቤት ቆይታ በሁዋላ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment