FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, March 21, 2013

የትግራይ ህዝብ ስማ!!


(ርዕሰ አንቀጽ)
mekelle


ሰሞኑን በውዴታም ይሁን በግዴታ በመቀሌ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ሲጨፍሩ፣ ሲዘሉ፣ ከበሮ እየመቱ የባህላቸውን ዘፈንና ውዝዋዜ ሲያወርዱ አይተናል። ምክንያቱ በግልጽ ባይነገርም ሲደበቅ የነበረው የህወሃት ሃብትና ንብረት ውጤት የሆኑ፣ በልዩ የመንግስት ድጋፍ የተከናወኑ ግዙፍ ተቋሞች በጎዳና ለህዝብ ሲቀርቡም ተስተውሏል። ልማቱ መልካም ነው። ደስ ይለናል። ምንም ተቃውሞ የለንም። ግን መልዕክት አለን።
ለማን?
ምሬትን፣ ጭቆናና መንገፍገፍ ሲበዛ በፍቃደኛነት በቦንብ ላይ እንደሚያስሮጥ ለሚያውቀው የትግራይ ህዝብ!! የትግራይ ህዝብ ስማ!!
ሰሞኑን ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት የትግራይ ክልል በትምህርት፣ በኤሌክትሪክ፣ በመንገድ፣ በእርሻ፣ በደን፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ ወዘተ ከሌሎች ክልሎች ሁሉ ርቃ መሄዷን ይፋ አድርጓል። በዚህም ደስ ይለናል። አይከፋንም። ከዚህ በላይ እንዲሆን እንመኛለን። ነገር ግን አንድ መልዕክት አለን።
ለማን?
አሁንም ለትግራይ ህዝብ!!
ሓውዜን የትግራይ ወጣቶች ለትግል ግልብጥ ብለው እንዲወጡ አደረገ። ሓውዜን የደረሰው የቦንብ ድብደባ ማንና እንዴት እንደተቀነባበር ብዙ የሚባልለት ቢሆንም የምሬት ጫፍ ሆኖ ህዝብን አሸፍቷል። ዛሬ መጨቆን ያንገፈግፋል ብለው ለትግል በተነሱና በተሰው ታጋዮች ደምና አጥንት ላይ የቆሙ ሌሎች ሓውዜኖች እንዲፈጠሩ አድርገዋል። እያደረጉም ነው።
ይህ በማን ስም እየሆነ ነው? በህወሃት አማካይነት በትግራይ ህዝብ ስም!!
ኦሮሚያ ልጆቿን በእስርና በጥይት እያጣች ነው። በጨለማ ቤት እየተሰቃዩ ያሉ የኦሮሞ ልጆች ግፍ ሰፍሮ ሞልቷል። አማራው አገር አልባ ሆኖ በየጎዳናው እየወደቀ ነው። እየተለዩ ከየክልሉ እየተባረሩ ነው። የመኖር ዋስትናቸውን ተከልክለው በሞትና በጣር መካከል ያሉ ህጻናትና ነፍሰጡሮች ለቅሶ ሰማይ ደርሷል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ እስር ቤት የሚማቅቁና የሚሰቃዩ ሰውነታቸውም የሚተለተል አሉ። የተገደሉ አሉ። ይህንን የሚያደርገው ደህንነቱ የተቆጣጠረውና መሳሪያ ያነገተው ኃይል ነው። ይህ ኃይል ደግሞ ህወሃት ነው። ህወሃት ይህንን ሁሉ ግፍ የሚፈጽመው በትግራይ ህዝብ ስም ነው። እያመረተ ያለው ደግሞ ብዙ ሓውዜኖችን ነው። በደልና የበቀል ስሜት ላንድ ጎሳ ወይም ሕዝብ ብቻ የተሰጠ አይደለምና ሌሎችም ሊነሱ ይችላሉ። መቼና እንዴት? አይታወቅም። በሲዳማ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ … ብዙ ችግርና ምሬት አለ።
በጋምቤላ ግፍ ነዶውን እየወዘወዘ ነው። በጋምቤላ በዘመናት ወደፊት የማናገኛው የደን ሃብት እየወደመ ነው። በጋምቤላ ሰላማዊ ህዝቦች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ መሬታቸውን እየተነጠቁ ለውጪ “ባለሃብቶች” እንዲሁም ለትግራይ ተወላጆች እየተከፋፈለ ነው። በባሌ፣ በቦንጋ፣ በወለጋ፣ ድፍን ኦሮሚያና የደቡብ ክልል ደን እየተጨፈጨፈ ትግራይ በደን እየተሸፈነች ነው ብሎ መጨፈር ለትግራይ ህዝብ ኩራት አይሆነውም። ኢትዮጵያዊ ነው የሚባለው የትግራይ ህዝብ እሱ የሚጠላውና ልጆቹን የገበረለት ግፍ በሌሎች ወገኖቹ ላይ ሲፈጸም ዝም ማለቱ ለምንና ከምን የመነጨ እንደሆነ ለማወቅ የሚፈልጉ አሉና ጥያቄውን እናቀርባለን።
ስለመፈናቀል ስናወራ “የትግራይ ተወላጆች ተፈናቀሉ” ሲባልና “ተፈናቀልን” ብለው ቅሬታና አቤቱታ ሲያቀርቡ አንሰማም። ይልቁኑም የአማራን ለም መሬት ለትግራይ በመከለል በደል የሚፈጽመው ህወሃት የሚባለው በትግራይ ህዝብ ስም የተደራጀና በነጻ አውጪ ስም እስካሁን አገር የሚመራ ቡድን ነው። ይህ ሁሉ ሲደረግ የትግራይ ህዝብ ያውቃል። ቢያንስ ቢያንስ የሰው መሬት ወርረው የተቀመጡት አይክዱትም። ግን ይህ እስከመቼ ይቀጥላል? ፍርሃት አለን። ለምን? ይህ ሁሉ ሌላኛው የሓውዜን ክፍል ነዋ!!
ስለ ግብር ሲነሳ የትግራይ ተወላጆች በግብር ዕዳ፣ በባንክ እዳና እንደ ልብ ነጻ ሆኖ በመንቀሳቀስ ችግር ቅሬታ ሲያሰሙ አይደመጥም። በመላው አገሪቱ በኢንቨስትመንት ተሰማርተው በሰላም እየሰሩ ነው። ሌሎች ግን በብሔር ተለይተው መከራ ይደረስባቸዋል። ህወሃት በማንነታቸውና ባመለካከታቸው እየነጠለ ከጨዋታና ከኑሮ መስመር ያወጣቸዋል። የጭቃ ቤት፣ አርሰው የሚበሉበት ከብት፣ ዶሮና በግ ሃብት ተብሎ ይወረስባቸዋል። ይህ እውነት ለትግራይ ምሁራን የተሰወረ አይደለም። ይህም ሌላው ህወሃት በትግራይ ህዝብ ስም በሌሎች ዜጎች ላይ የሚፈጥረው የምሬት ሓውዜን ነው!!
ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ሲነሳ የመጀመሪያው መስመር ላይ ሆነው አገሪቱን የሚያልቡት የቀድሞ ታጋዮችና የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ነጋዴዎች ናቸው። ጤፍ ወደ ኤርትራ በማጋዝ፣ ባህር ዛፍና ቡና በማሻገር፣ የዱር እንስሳትን ቆዳና ቀንድ በመነገድ የተሰማሩት ይታወቃሉ። ብዙ እጅግ ብዙ ማለት ይቻላል። የምናነሳቸው ማሳያዎች ሁሉ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ፣ … ሓውዜኖች ናቸውና እዚህ ለጊዜው ላይ  እናቁም!!
ሻዕቢያ ድንገት ወረራ አካሂዶ ድፍን ትግራይን ሲቀጠቅጥ፣ ህጻናትን በቦንብ ሲቆላ፣ አገሬ ብሎ የተነሳን ህዝብ በማያውቀው ወንጀል እየሰፈሩ ማሰቃየት ይቆም ዘንድ የትግራይ ህዝብ በቀጥታ ድምጹንና ተቃውሞውን በአግባቡ ማሳየት የሚገባው ወቅት ላይ እንደሚገኝ ይሰማናል፤ ደግሞም እናምናለን። ዛሬ “ውርሱን እንጠብቃለን” በማለት የሚጮህላቸው አቶ መለስ በወቅቱ ክህደት ሲፈጽሙ የደረሰው ዛሬ እየተነጠሉ የሚመቱትና መድረሻ ያጡ ወገኖች ናቸው። ዛሬም ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ናቸው። በሰባና ሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ ልብ ውስጥ የተፈጠሩት ሓውዜኖች ወደ ቁጣ ሲለወጡ አምስት አምስት ሆኖ መደራጀት፣ በስውር መታጠቅና በየሰፈሩ ያሉትን አስተባባሪዎች ስም ለቅሞ በመያዝ “ሳልቀደም ልቅደም” ብሎ መራወጥ አያዋጣም፤ ጊዜው ስለሚያልፍበት የትም አያደርስም። ሓውዜናዊ ህይወት የሚኖር ሕዝብ ከደረሰበት በላይ የሚያጣው ስለማይኖር እንኳን ስለማጣት ስለመኖርም አያስብም፡፡ በዚህ ከቀጠለ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በየቦታው ራሱ ህወሃት የፈጠራቸው ሓውዜኖች መናደፍ መጀመራቸው አይቀርም።
“ህወሓትን እናስቀድም … ጠላቶቻችንን እናጥፋ” በሚል የማያቋርጥ ጥላቻ መቀጠል ተጨማሪ ሓውዜኖችን ከመፍጠር በስተቀር “ጠላትን” ማጥፋት የማይቻል እንደሆነ ከዚህ በፊት በሕዝብ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ተሞክሮ ማስረጃ ነው፡፡ በበረሃ “ጠላትን እናጥፋ”፤ ሥልጣን ይዞ “ጠላትን እናጥፋ”፤ አገር እየመሩ “ጠላትን እናጥፋ”፤ ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ “ጠላትን እናጥፋ” … 40ዓመት ሙሉ በ“ጠላትን እናጥፋ” መርህ የሚጓዘው ህወሃት “ጉድጓድ የሚምስ ራሱ ይወድቅበታል” የተባለው የተቀደሰ አባባል ሲፈጸም እንዳየነው ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለማጥፋት የሚመኘው ህወሃት የራሱ መጥፊያ የሆኑ በርካታ ሓውዜኖችን ፈጥሯል፡፡
“የ100 ዓመት የቤት ስራ ሰጥተናቸዋል” በሚል በየድረገጹ የሚለጠፉ ተራ ድንፋታና ትዕቢት የሚፈጠሩትን ሓውዜኖች ከማብዛት ውጪ ትርፍ የላቸውምና ወደ ደጉ መንገድ መመለስና ሰብዓዊነትን በማስቀደም፤ ተደጋግፎ መኖርን ማጎልበት ይሻላል ለማለት እንወዳለን። ተሳስበውና ተረዳድተው የሚገነቡት የትም ሆነ የት የአገር ነውና ሁሉም ይኮራበታል፤ ይጠብቀዋል። ተጠቃሚ ይሆንበታል። የሚያምርብንም ይህ ነው። ህወሃት አልሰማም ብሏል። የትግራይ ህዝብ ግን ስማ!! ይህ ሁሉ የሚደረገው በስምህ ነው!!
http://www.goolgule.com/listen-people-of-tigray/

No comments:

Post a Comment