መጋቢት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ በሚገኘው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ ቦሌ ለሚ በሚባል አካባቢ ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2005ዓ.ም. ኮብልስቶን በሚሰሩ ሰዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 8 ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ፍኖተ ነጻነት ዘገበ፡፡
የግጭቱ መንስኤ የሞባይል መጥፋት እንደሆነ እና በዚህም ኮብልስቶን ትሰራ የነበረችን የአንዲት የአካባቢው ነዋሪ ሴት ጡት ሌላው ሰራተኛ በመቁረጡ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በአካባቢው ነዋሪዎችና በኮብል ስቶን ሰራተኞቹ መሀከል ግጭት ተነስቷል፡ ፡ ፀቡን ለማረጋጋት የሞከረ ፖሊስም በኮብልስቶን ተመቶ ወዲያው ህይወቱ ማለፉን ጋዜጣው ዘግቧል።
ጉዳዩ ወደ ብሔር ግጭት ተለውጦ ፀቡ እስከ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን መዝለቁንና ህይወቷ ያለፈው ወጣት የአካባቢው (ኦሮሚያ) ተወላጅ በመሆኗ ጉዳዩ ወደ ማኀበረሰቡ በመድረሱ በርካታ የአካባቢው ሰዎች ከአያት ኮንዶሚኒየም እስከ ቦሌ ለሚ ድረስ ከበባ በማድረግ በሰራተኞች መካከል የኢህአዴግ አደራጅና ሰላይ ናቸው የተባሉ 6 የወላይታ ተወላጆችን በመግደልና በርካታ ሰዎችን በማቁሰላቸው በአካባቢው ከ3 ተሸከርካሪ ያላነሱ የፌደራል ፖሊሶች ግጭቱን ለማረጋጋት ቢገኙም ለማረጋጋት እንዳልቻሉ ሆኖም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን ወስደው እንዳሰሩ የዓይን እማኞች መግለጻቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
በርካታ ሰዎች የኮብልስቶን ስራ ይሰሩበት የነበረው አያት ጨፌ እና ቦሌ ለሚ የሚባል አካባቢ ማንም ሰው እንዳይገባ የተደረገ ሲሆን ከሰራተኞች ጋር እዛው በሚገኝ ቀበሌ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ የመንግስት ባለስልጣናት እያወያዩ መሆናቸውን ፍኖተ ገልጿል።
ኢሳት ችግሩ እንደተነሳ በእለቱ ዘገባ ማቅረቡ ይታወቃል። ኢሳት 10 ሰዎች እንደተገደሉ መረጃ ደርሶት የነበረ ቢሆንም፣ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ሳይችል ቀርቷል። አንዳንድ ወገኖች የሟቾች ቁጥር 4 መሆኑን ለኢሳት ተናግረዋል። ከ15 ሺ በላይ ህዝብ የሚሳተፍበት የኮብል ስቶን ማንጠፍ ስራ መስተጓጎሉን እስካሁንም አለመጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።
No comments:
Post a Comment