FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, March 15, 2013

ታሪክ አልባ ባለሃብቶች በከተማችን አዲስ አበባ


images
(በፋኑኤል ክንፉ) ሰንደቅ ጋዜጣ
በከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ ብዛት ያላቸው ሃብታሞች በቅለው ይገኛሉ፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ሕንፃዎችም እየበቀሉ ወደ ላይ እየተመነደጉ በኩራት ነዋሪውን ቁልቁል እያዩት፣ ሃፍረት ሳይሰማቸው ቆመዋል፡፡ ነዋሪውም በበኩሉ በፍጥነት በቁመት የሚበልጡትን ሕንፃዎች ዕድገት በአግራሞት እየተመለከታቸው ለዕድገታቸው ትንታኔ መስጠት አቅቶት ኑሮውን ቀጥሏል፡፡
ከተማው ውስጥ ከበቀሉት በጣም ከሚያምሩት ሕንፃዎች መካከል አንዱ ከሆነው ሕንፃ በምሽት ከሰዎች ጋር ገባሁ፡፡ በሕንፃው ውስጥ ባር አለ፡፡ መጠጥ በሚቀርብበት ባንኮኒ ላይ የሚጠጣው ውስኪ ሲሆን፤ ሽያጩ በመለኪያ ሳይሆን ከግማሽ ጠርሙስ አንስቶ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ በየጠረጴዛውም ላይ የሚደረገው የውስኪ ፍሰት አስገርሞኛል፡፡ እየመሸ በመሄዱ የጠጡበትን የውስኪ መጠን ክፍያ እየፈጸሙ ወጣ የሚሉ ባለፀጎችን እመለከት ጀመር፡፡ የሚከፍሉት ሂሳብ መጠን አስገራሚ ብቻ ሳይሆን ጥያቄ ይጭራል፡፡ በብላህርዚያ የተወጠረ ሕፃን የሚመስል አንድ አጭር የአልኮል ጠርሙስ መጠጥ ዋጋው ከ4 ሺ በላይ ነው፡፡ በጠረጴዛዎቹ ላይ እንደቀላል መጠጥ ተበትኗል፡፡ በአማካኝ በአንድ ሰው የሚከፈለው የገንዘብ መጠን ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የወር ደሞዝ በእጅጉ የሚልቅ ነው፡፡
ሆኖም በተወሰኑ ጠረጴዛዎች ላይ የተከፈለው የገንዘብ መጠን ግን ክፍኛ አትኩሮቴን ወሰደው፡፡ አብሪያቸው ከሄዱኩት ሰዎች መካከል አንዱ በጣም መገረሜ አስደንቆት፣ ጠየቀኝ፡፡ “በተከፈለው ገንዘብ ደነገጥክ እንዴ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ አዎ! የሚል ምልሽ ሰጠውት፡፡ “Spiderman” ተብለው ከሚጠሩት ባለሃብቶች መካከል ናቸው” ብዙም አትገረም አለኝ፡፡ መልሼም “Spiderman” የሚባሉ በላፀጎች አሉ እንዴ? ምንስ ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ወረወርኩለት፡፡
ሊያስረዳኝ ጊዜም አልወሰደም፤ “የስፓይደር ማን የሚለውን ፊልም ያየኅው ይመስለኛል፡፡ ስፓይደር ማን ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ መንደርደርያ አይፈልግም፡፡ ከሕንፃ ወደ ሕንፃ፣ ከምድር ወደ ሰማይ፣ ክንፍን እየዘረጋ እንደመለአክ እንደእርግብ ይበራል ሰንጥቆ ወደ ሰማይ ይወጣል እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራት ሲፈጽም መነሻም፣ መንደርደሪያም የለውም፡፡ አልፎ ተርፎ የመሬት የስበት ኃይል ለስፓይደር ማኑም አይደለም፡፡”
“እዚህ ውስኪ ቤት ያየሃቸው ‘ባለሃቶችም’ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዴት? ሚሊዮኖች ላይ እንደተሳፈሩ አይታወቅም? እንደስፓይደር ማን ያለመነሻ፣ ያለመንደርደሪያ ብድግ ብለው ሚሊዮኖች ላይ የተቀመጡ ባለፀጎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን አንድ ሚሊዮን ብር እንዴት እንደፈጠሩት እንኳን? ራሳቸውም አያስረዱህም፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ሃብታም ለመሆኑን የመጀመሪያውን አንድ ሚሊዮን ብር መስራት መቻል ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሚሊዮን ብር ለመስራት ከፍተኛ የሆነ ውጣ ውረድ አለው ከሚል መነሻ ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን ብር ላይ ሲደረስ ግን ራሱ አንድ ሚሊዮን ብሩ እና በሂደት የተገኘው የስራ ልምድ ተደምረው ብዙ ሚሊዮኖች ይፈጥራሉ የሚል ጥናታዊ ዕሳቤ አላቸው፡፡ አሁን ያየሀቸው ከፋዮች ግን ታሪክ አልባ ሃብታሞች ናቸው፡፡ በኅብረተሰብ ውስጥ የፈጠሩትም ሆነ የጨመሩት ዕሴት ሳይኖር ሚሊዮኖች ላይ የሰፈሩ ስፓይደሮች ናቸው፡፡”
አያይዞም፤ “በፊት በሚኖሩበት ሰፈር አካባቢ ሄደ ስለነሱ ለማወቅ ብትሞክር ማንም በንግዱ ዓለም ውስጥ መኖራቸውን ምስክርነት አይሰጥህም? የአካባቢው ሕዝብም ከትንሽ ነገር በመነሳት ወደ ትልቅ የለውጥ ጎዳና የደረሱ ለልጆቻችን ጥሩ አረዓያ የሆኑ ናቸው የሚል ምስክርነት የሚሰጣቸው አንድ ሰው አታገኝም፡፡ ብቻ ብድግ ብለው የሚሊዮኖች ጌታ ሆነዋል፡፡ አሁን አግራሞት የፈጠረብህን ያህል የገንዘብ መጠን የከፈሉት ያልለፉበት ሃብት በመሆኑ ነው፡፡ የገንዘብ አወጣጥ አመጣጡን ያሳያል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ከስፓይደር ማን ጋር የሚለያቸው አንድ ብቸኛ ነጥብ ቢኖር፤ ስፓይደር ማን በፊልም ውስጥ ድንቅ ተግባሩን ሲከውነው እነሱ በእውኑ ዓለም ውስጥ መፈፀማቸው ነው፡፡ ስለዚህም ይህን ያህል መጠን ገንዘብ መክፈላቸው አስገራሚ አይደለም፡፡” አለኝ፡፡
ልብ በሉ፤ ስለባለሃቶቹ ማንነት ስለሚታወቅ አይግረምህ እያለኝ ነው፡፡ መታወቁ አንድ ነገር ሆኖ፤ ባለሃብቶቹ አንዴ በተአምር ገንዘብ አግኝተዋል ስለዚህም ምንም ማድረግ አይቻልም የሚል ስምምነት መቀበል ወይም መፍጠር ወዴት ያደርሰናል፡፡ መቼም ተለቅመው ይታሰሩ ለማለት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ቢያንስ ግን ለእስር ሳይዳረጉ፤ የሃብታቸውን ምንጭ በአቃቢ ሕግ በኩል እንዲያስረዱ ለምን አይደረግም? ያከማቹት ሃብት ለመንግስት ከከፈሉት ግብር ጋር የሚታረቅ ከሆነ ሕዝብ ፊት አቅርቦ እንዲመሰገኑ ማድረግ አንድ አማራጭ ነው፡፡ ሌላው፤ ያከማቹት ሃብት ከከፈሉት የመንግስት ግብር ጋር የማይታረቅ ሆኖ ከተገኘ ሃብታቸው እንዲወረስ ማድረግ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ውጪ የአደባባይ ታሪክ አልባ ባለፀጎች መሆናቸው እየተነገረ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በምን መመዘኛ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን ለመዋጋት ሕዝቡን የድርሻውን እንዲወጣ ማሳመን ይችላል?
ወጋችን ቀጥሏል፡፡ ይህን መሰል የባለፀጎች ተግባር ስመለከት የመጀመሪያ አይደለም፡፡ አሁን ለየት ያለብኝ ነገር በዚህ ጉዳይ የሚቆጭ ባለሃብት መኖሩን ለመገንዘብ መቻሌ ነው፡፡ አብሬ ከሄድኳቸው ሰዎች መካከል አለመሆኑ ደግሞ ሌላው አስገራሚው ነጥብ ነው፡፡ በአንድ ክብ ጠረጴዛ ላይ ሆን ነበር ያወጋነው፡፡ ቀጥለናል፡፡
“በቂ ገንዘብ አላቸው እንጂ ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ ናቸው ብለህ አታስብ” ሲል ሊያስረዳኝ ሞከረ፡፡ በርግጥ ገንዘብ ብቻውን ደስተኛ እንደማያደርግ ባውቅም ጠቃሚ አቅም እንዳለው ግን መካድ ከባድ ነው፡፡ “እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጠኝ፤ “እነዚህ ታሪክ አልባ ባለሃብቶች የሚኖሩበትን መኖሪያ ሄደህ ተመልከተው፡፡ በአብዛኛው ቤታቸው ከሶስት ሜትር ከፍታ በላይ ርዝማኔ ባለው የግንብ አጥር የተከበበ ነው፡፡ በአጥሩ ዙሪ ላይ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መጠን የሚሸከም ሽቦ ተጠምጥሞ ታገኛለህ፡፡ በአጥሩ አንዱ ማዕዘን ስር ወይም ወደ ላይ የዘበኛ ቤት ታገኛለህ፡፡ ዘበኞቹ በአብዛኛው የጥበቃ መሣሪያ አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ባለሃብቶቹ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በሰላም እንዲተኙ ነው፡፡”
“ልብ በል፤ ይህ ሁሉ ጥበቃ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ለምን አስፈለገ? ባለሃብቶቹ የሚፈሩት ማንን ነው? የአንድ ኢትዮጵያዊ ቁመት ከ2 ሜትር በላይ አይዘልግም፤ የሚሰሩት አጥሮች ግን ከ3 ሜትር በላይ ናቸው፡፡ የኤሌትሪክ ሽቦም ይጠመጠምባቸዋል፡፡ ጦር መሣሪያ የያዘ ዘበኛም ለሊቱን ሙሉ መኖራያ ቤታቸውን እየዞረ ባለሃብቶቹን ሲጠብቃቸው ያድራል፡፡ ምን ፈርተው ይመስልሃል ይህ ሁሉ ጥበቃ ያስፈለጋቸው? የከተማውን ሌቦች ፈርተው ይመስልሃል? ሁሉም እንደሚያውቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደደቡብ አፍሪካ የተደራጁ ጦር መሣሪያ የታጠቁ ወንጀለኞች የሉም፡፡ ይህ ከሆነ እውነቱ፤ ማን ፈርተው ይመስልሃል? ….. የፈሩት ሕብረተሰቡ ነው፡፡ የአካባቢውን ሰዎች ነው፡፡ የሚፈሩትም ሕብረተሰቡን ነው፤ እንደዘረፉት ሕሊናቸው ስለሚያውቅ ነው፡፡ የሕብረተሰቡን ሃብት አላአግባብ በመዝረፋቸው አንድ ቀን ሕብረተሰቡ ሊነሳባቸው እንደሚችል ሕሊናቸው ስለሚነግራቸው መሆኑ አሻሚ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ጥበቃም የሚያድናቸው ከሆነ ወደፊት የምናየው ሆኖ ግን የአጥሩ ከፍታ የሃብታቸው መገለጫ አድርገን መውሰዳችን ግን ስህተት ነው፡፡” ምክንያቱም እውነቱ ሌላ ነው ሲል ተደመጠ፡፡
የሚገርም ነው፡፡ እነዚህ ባለሃቶች ሕብረተሰቡን ይፈሩታል ከተባለ ለልጆቻቸው ስለራሳቸው ምን ብለው ይናገራሉ? ታሪክ አልባ ሃብት እንዴት ለልጅ ይተረካል? የእነዚህ ባለሃብቶች ልጆች በአደባባይ ሲኮሩ ነው የሚታዩት፣ ሕብረተሰቡ ግን የማን? ልጆች መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ልጆቹ በአባቶቻቸው የሚኮሩት ምን አይነት ታሪክ ተወርቶላቸው ይሆን? በዚህ ጉዳይ ላይ በተነሳው ክርክር ልጆቹ ከአባቶቻቸው ታሪክ ጋር አይገናኙም፣ ማዛመድም ተገቢ አይደለም የሚል ነበር፡፡
ሃብታሞቹ ግን ለልጆቻቸው እንዲህ ሊሏቸው ይችላሉ፤ “እኔ አባትህ ከልጅነቴ ጀምሮ እድለኛ ነኝ፡፡ ብዙ ነገሮች ይሳኩልኛል፡፡ ለምሳሌ፤ ሃብት ማፍራ ስጀምር ድንገት አንድ ሚሊዮን ብር አገኘው፡፡ ቅድም እንደነገርኩ እድለኛ ነኝ፡፡ ትንሽ ቆይቼ 5 ሚሊዮን ብር ድንገት አገኘሁ፡፡ በእድሌ በጣም ተደሰትኩ፡፡ ከዚህም በኋላ አንተም ልጄ ስትወለድ ግንባር ጥሩ ነበር፤ በአናት በአናቱ ሚሊዮኖች ማግኘት ጀመርኩ፡፡ በውጤቱም እናንተ ጥሩ ትምህርት ቤት እንድትገቡ፣ የተሻለ ስራ እንድትሰሩ፣ በቂ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖራችሁ ለማድረግ በቅቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ አባታችሁ እስካለሁ ድረስ ምንም አይገጥማችሁም ይላቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ በቂ ታሪክ ለልጅ እንዴት ሊቀርብ ይችላል፡፡ በዚህ ጣፋጭ ታሪኳ መነሻነትም ልጆቹም “እንደ አባቴ እንድለኛ አድርገኝ” እያሉ ፈጣሪያቸውን መለመናቸው ሳያቆርጡ ይቀጥላሉ፡፡ ማን ያውቃል ወደፊትም ይህ ፀሎታቸው ይሳካላቸው ይሆናል? እንደአባታቸውም ይሆኑ ይሆናል፡፡”
(ይህ ጹሑፍ በሰንደቅ ጋዜጣ ቁጥር 389 ረቡዕ የካቲት 13/ 2005 ታትሞ የወጣ ነው)
source: yehabesha.com

No comments:

Post a Comment