በኢትዮጵያ ከ11 ሚሊዮን በላይ ተረጅዎች አሉ
ታህሳስ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና በአለም ባንክና በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ በምግብ ለስራ ታቅፈው የሚረዱ 7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ታውቋል።
መንግስት ሴፍቲኔት እያለ በሚጠራው መርሀግብር የታቀፉ ኢትዮጵያውያን ምእራባዊያን ለጋሾች እርዳታቸውን ቢያዘገዩ ወይም ቢያቋርጡ ወደ አስቸኳይ ተረጅነት የሚወርዱ ናቸው።
በአገሪቱ ውስጥ በሚታየው የምግብ እጥረት የተነሳ በሴፍቲኔት የሚታቀፉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም ታውቋል። ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግስት ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገበ ቢገልጽም፣ ከ15 ኢትዮጵያውያን አንዱ ከውጭ በሚሰፈር እርዳታ የሚኖር መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።
መምህራን ተማሪዎችን ፈርመው እንዲረከቡ የሚያደርግ መመሪያ ተዘጋጀ
ታህሳስ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች መጨመራቸውን ተከትሎ ፣ በአማራ ክልል የሚያስተምሩ መምህራን ተማሪዎችን በሰሚስተሩ መጀመሪያ ላይ ቆጥረው ተረክበው፣ በሰሚስተሩ መጨረሻ ላይ ቆጥረው እንዲያስረክቡ የሚያደርግ መመሪያ ወጥቶ ለውይይት ቢቀርብም፣ መምህራን ግን አጥብቀው ተቃውመውታል።
በአንድ የትምህርት ዘመን ውስጥ መምህሩ ቆጥሮ ከተረከባቸው ተማሪዎች መካከል ከ2 ተኩል በመቶ በላይ ተማሪዎች ቢያቋርጡ፣ መምህሩ በጥፋተኝነት የሚመዘገብ ሲሆን፣ አስፈላጊውን እድገትም አያገኝም።
በክልሉ የሚማሩ ተማሪዎች በብዛት ወደ አረብ አገራት በስደት መልክ እንደሚሄዱ መዘገባችንን ተከትሎ እንዲህ አይነት መመሪያ መተላላፉ ታውቋል።
መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸው መመሪያዎች መምህራን ተስፋ እንዲቆርጡ እያደረጋቸው መሆኑን መምህሩ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment