FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, December 25, 2012

የቤተ ክርስቲያን አባቶች አጣብቂኞች /ለአራት የከፈለ አጋጣሚ


በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ያለችበት ጊዜ ነው፡፡ በአንድ በኩል በውጭ ሀገር ከሚኖሩ አባቶች ጋር ያለው የዕርቀ ሰላም ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ? እንዴትስ እንደሚቀጥል? በውል አልታወቀም፡፡ ለዕርቁ  የተላኩት አባቶችም የዕርቁ ስብሰባ ከተከናወነ ከሳምንታት በኋላ እንኳን ወደ ሀገር ቤት አልመጡም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በዕርቁ ሂደትና በቀጣይ ተግባራት ላይ እንዲወያይ አላደረጉም፡፡ ከዚያ ይልቅ በአሜሪካ ያለውን አስተዳደራዊ ችግር በመፍታትና በሌሎች ግላዊ ነገሮች ላይ ተይዘው ከዚያው ከአሜሪካ ሳይወጡ በጥር ወር ይካሄዳል የሚባለው ቀጣዩ ስብሰባ እየደረሰ ነው፡፡
አስቀድሞ ተወስኗል በተባለው መሠረትም ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ አውጥቷል፡፡ የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴም አቋቁሟል፡፡ ይህ ሂደት ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን የፈተነና ነገሮችን ረጋ ብለን እንድናይ የሚያደርገን አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ያሉትን አባቶች ይህ ሂደት ከአራት ከፍሏቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ‹የዕርቁ ሂደትና የምርጫው ሕግ ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው፡፡ በጥቅምቱ ሲኖዶስ በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ የምርጫ ሕጉን እናያለን ብለን ስንወስን ይህን ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህም ሥራ አቁመን ሳይሆን እየሠራን ዕርቁን እናካሂዳለን› በሚል አቋም የምርጫ ሕጉንና የአስመራጭ ኮሚቴውን የማዋቀርን ተግባር ሲያከናውኑ ነበር፡፡ ሌሎች አባቶች ደግሞ ስለ ነገሩ ያላቸው አቋም ግልጥ ባይሆንም ወደ ኅዳር 30 ጉባኤ ከመምጣት ተቆጥበው ሁኔታውን በሩቁ እያዩት ነው፡፡ ሦስተኞቹ አባች ደግሞ ‹ዕርቀ ሰላሙ አንዳች ምዕራፍ ሳይደርስ የመከራከርያ ነጥብ የሚሆን ነገር ማድረግ የለብንም፤ በተለይ ደግሞ አስመራጭ ኮሚቴ ማቋቋም የለብንም› በሚለው አቋማቸው እንደጸኑ ነው፡፡ ለዕርቀ ሰላሙ ወደ አሜሪካ የተጓዙት አባቶች ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ ተከናወነ በሚባለው ነገር ደስተኞች አለመሆናቸውንና በአቋምም መለየታቸውን እየገለጡ ነው፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ለአራት የከፈለ አጋጣሚ እንዴት ተከሰተ?
የዕርቁ ሂደት ምን መሆን አለበት? የሚላኩት ልዑካን ሥልጣናቸው የት ድረስ ነው? በዕርቁ ሂደት የሚፈጠሩ ስምምነቶች ገዥነታቸው ምን ያህል ነው? ይህ ዕርቅ አንድ ውል ላይ እስኪደርስ ድረስ ሁለቱም አካላት ላለማድረግ ምን ምን ተስማምተዋል? ለዕርቁ የሚላኩ ልዑካን ከዕርቁ ስብሰባ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ይመለሳሉ? ከእነርሱስ ምን ይጠበቃል? የሚሉት ነገሮች ግልጽና ዝርዝር ባለመሆናቸው ለዕርቅ በተላኩት አባቶችና በላኪዎቹ መካከል የልዩነት መነሻዎች ሆነዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ዕርቁ የሚፈለግም የሚደገፍም ነው፡፡ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ከጠብ በላይ በደል፣ ከዕርቅም በላይ ጽድቅ የላትምና፡፡ አካሄዱ ግን የሚቀሩት ነገሮች አሉ፡፡ በመጀመርያ እርቁ በሀገር ቤት ያለውን 45 ሚሊዮኑን አማኝ የዘነጋና ‹በአሜሪካኖች› ተጽዕኖ ሥር የወደቀ ነው፡፡ አስታራቂዎቹም ሆኑ የዕርቁ ቦታ አሜሪካ ሆኗል፡፡
የመከፋፈሉ ችግር አሜሪካ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ምናልባት ይበልጥ ተጎድታ ይሆናል እንጂ፡፡ ችግሩ የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ነው ከተባለ ግን የዕርቁ ሂደት የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ውክልናና አስተዋጽዖ ሊኖርበት ይገባ ነበር፡፡ ምናልባት እዚህ ያለው ሕዝብ ገንዘብ ማዋጣት አይችልም ተብሎ ካልሆነ በቀር፡፡ ግን ይህቺ 35,000 አጥቢያዎች፣ 400,000 ካህናት፣ 1,100 ገዳማት ያሏት ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደረው ከውጭ በሚገባ ገንዘብ ሳይሆን ቅጠል ሻጮቹ በሚያዋጡት ገንዘብ መሆኑ ሊዘነጋ ባልተገባው ነበር፡፡
አስታራቂዎቹም ሆኑ የዕርቁ ቦታ በአሜሪካ ተጽዕኖ ሥር እንዲወድቅ መደረጉ ደግሞ ሂደቱን ‹በአሜሪካ መንፈስ› እንዲመራ አድርጎታል፡፡ አሜሪካውያን እርስ በርሳቸው የሚያደርጉትን የቅርጫት ኳስ ውድድር ‹የዓለም ሻምፒዮና› ብሎ የመጥራት መንፈስ አላቸው፡፡ ለእነርሱ ዓለም አሜሪካ ናት፡፡ ይህ መንፈስ በዕርቁ ሂደት ላይ ይታያል፡፡ አስታራቂዎቹ ‹አሜሪካኖች› ዕርቁ የሚደረገው አሜሪካ፣ መግለጫ የሚሰጠው አሜሪካ፣ አባቶች ጸለዩ የሚባለው እንኳን አሜሪካ በሚገኙ አካላት በሚመሩ አብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡ ተደሰተ የሚባለውም እዚያ ያለው ሕዝብ፣ አዘነ የሚባለውም እዚያ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ አስታራቂዎቹም ሆኑ ታራቂዎቹ በአሜሪካ ሚዲያዎችና እዚያ በሚዘጋጁ ገጸ ድሮች እንጂ 45 ሚሊዮኑ ሕዝብ በሚሰማቸው የሀገር ውስጥ ሚዲያዎችና በሚያነባቸው ጋዜጦች መግለጫ አይሰጡም፡፡ ‹የኢትዮጵያ ሕዝብ› ማለት በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ማለት ሆኗል፡፡
ካልጠፋ ቦታ መጀመርያውኑ የዕርቁ ጉባኤ አሜሪካ መደረግ አልነበረበትም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነገ ልጆቻችን ይህን የዕርቅ ታሪክ ሲማሩት ‹ተከፋፍለው የነበሩት አባቶች በአሜሪካ ሀገር፣ እገሌ በተባለ ግዛት፣ እገሌ በተባለም ሆቴል በተደረገ ጉባኤ ታረቁ› ተብለው ነው የሚማሩት፡፡ ዕርቁን ምንም ዓይነት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትይይዝ በሌለው ቦታ ከማድረግ ይልቅ ለሁሉም አማካኝ በሆነው፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊም ትይይዝ ባለው፣ የመጀመርያዋ ጉባኤ ሐዋርያት በተደረገባት በኢየሩሳሌም ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ የቦታው በረከትና ቅድስና፣ የአባቶች ጸሎትና ምክርም ነገሩን ቀና ባደረገው ነበር፡፡ እዚያም ሆኖ ቢሆን ኖሮ ልዑካኑ ይህንን ያህል ጊዜ ባልቆዩና ጉዳዩንም ቀርበው ባስረዱ ነበር፡፡ ይህንን ታላቅ ጉባኤ ሆቴል ውስጥ ማድረጉ ለሻሂና ቡና እንጂ ለመንፈሳዊው ሂደት የሚፈይደው ነገር የለም፡፡
እነዚህ አባቶች ወደ አሜሪካ ሲላኩ በዚያ ያለውን አስተዳደራዊ ችግርም እንዲፈቱ ተልከዋል ይባላል፡፡ ምን ማለት ነው? የት ድረስስ ነው የሚፈቱት? ለብዙ ዘመን የተከማቸውን ችግርስ እንዴት አድርገው ነው አዳብለው የሚፈቱት? የዕርቁ ሂደት በራሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቅ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ዋጋ ያለው ሂደት ነው፡፡ የኅዳር 30 የሲኖዶስ ስብሰባ ሲቀጠርም ይህ ይታወቃል፡፡ ወይ ስብሰባውን ማዘግየት፣ ያለበለዚያም የልዑካኑን ተልዕኮ ዕርቁን ብቻ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ለአስተዳደራዊ ጉዳዩ ሌሎች አባቶችን መላክም ይቻል ነበር፡፡ አንዱ ጉዳዩን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተውም ይኼ የተልዕኮ መደራረብ ነው፡፡
አሁን ጉዳዩ እየታየ ያለው በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ሳይሆን በሚዲያዎች በሚሰጥ መግለጫ ላይ ሆኗል፡፡ የተላኩትም በቶሎ ተመልሰው ሁኔታውን ከማርገብና ሂደቱን ከማስረዳት ይልቅ እዚያው ተቀምጠው የመግለጫ ናዳ እያወረዱ ነው፡፡ መቼም የቤተ ክህነቱን ውሳጣዊ ጠባይና የውሳኔ አሰጣጥ ‹ወገብረ መብረቀ በጊዜ ዝናብ› የሚለው ዳዊት የሚደገምበትንም ጊዜ፣ ‹ነፋሳትም ከመዝገቦቻቸው› እንዴትና በማን እንደሚወጡ የሄዱትም ልዑካን ያውቁታል፡፡ ሠርተውበታልም፡፡ መፍትሔውም እዚያ ማዶ ተቀምጦ ወንጭፍ መወርወር አልነበረም፡፡ እዚሁ በአንድ ጉባኤ ተፋጭቶ አንድ ነገር ላይ መድረስ እንጂ፡፡
እዚህ የሚካሄደውም ነገር ግልጽ አይደለም፡፡ የፓትርያርክ ምርጫና አመራረጥ ቤተ ክርስቲያኒቱን አምስት ጊዜ ፈትኗታል፡፡ አባቶችንም ደጋግሞ ለያያቷቸዋል፡፡ እናም አሁን የሚደረገው የምርጫ ሂደትም ሆነ የሕግ ሥራ ቢያንስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ሁሉንም አባቶች ያሳተፈ እንዲሆን ጥረት መደረግ ነበረበት፡፡ የቀሩትስ ለምን ቀሩ? አንፈርምም ያሉትስ ለምን አንፈርምም አሉ? ይህ ሁኔታ ሂደቱ የሁሉንም አባቶች ይሁንታ አለማግኘቱን የሚያሳይ ነው፡፡
ወደ ሕጉ ማጽደቅና ወደ ኮሚቴ ምርጫ ከመሮጡም በፊት ሦስት ነገሮች ከግምት ውስጥ መግባት ነበረባቸው፡፡
  1. ሁሉም አባቶች ተገኝተው መሳተፋቸውና በዝርዝሮቹ ባይስማሙ እንኳን በሂደቱ መስማማታቸው መረጋገጥ ነበረበት፡፡ ይህ ካልተገኘ ግን ቅድሚያው ለዚህ መሰጠት ነበረበት፡፡ የራቁትን ለማቅረብ እየተሠራ የቀረቡትን ማራቁ የሚጋጭ ነውና፡፡
  2. የተላኩት አባቶች ተመልሰው በስብሰባው እንዲገኙና ከተስማሙባቸው ነጥቦች አንጻር ሂደቱ መጣጣም አለመጣጣሙ መገምገም ነበረበት፡፡ ሁለቱ ተግባራት አብረው ይሄዳሉ? ወይስ ይቀዳደማሉ? የሚለው መታየት ነበረበት፡፡
  3. የእርቁ ሂደት ዋነኛ ትኩረት የሆነው የአራተኛው ፓትርያርክን ቀጣይ ሁኔታ አሁን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚያካሂዳቸው ተግባራት አንጻር እንዴት ሊያስኬደው አስቧል? በቀጣዩ የጥር ጉባኤ የአሁኑን ሂደት የሚቀለብስ ወይም የሚያሻሽል ስምምነት ቢደረስ የቱ የትኛውን ይገዛዋል? የሚለው ከግምት ውስጥ መግባት ነበረበት፡፡
አሁን ምን ይደረግ
በቤተ ክርስቲያን ትውፊት አንድ ወደ አጣብቂኝ የገባ ሰው አጣብቂኙ እንዳይዘው ሁለት ነገሮች ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የመጀመርያው ‹ንጽሕናውን› ጠብቆ በአጣብቂኙ ማለፍ ሲሆን፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ቢያዝ ደግሞ ንስሐ ገብቶ ከአጣብቂኙ መውጣት ነው፡፡ እኛም ያሉን እነዚህ ይመስሉኛል፡፡ እየሄድንበት ያለው መንገድ የአባቶችን ሐሳብ ብቻ የያዘ፣ ለእውነትና ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ከማሰብ የመጣ ‹ንጽሕና› ያለበት ከሆነ ከአጣብቂኙ መውጣት ቀላል ነው፡፡ ይህ ካልሆነም በጊዜ ችግሮችን አስተካክሎ ከተያዙበት አጣብቂኝ ማምለጥ ይቻላል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ እየተከናወኑ የሚገኙትንና የልዩነትና የብዥታ መነሻ የሆኑ ሂደቶችን ገታ አድርጎ የወጡትም መጥተው፣ የቀሩትም ተጠርተው በምልዐት መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካ ሆኖ በሚሰጥ መግለጫና፣ ሀገረ ስብከት ተቀምጦ በሚኖር ቅሬታ ችግሩ አይፈታም፡፡ ችግሩ በመወያየት፣ መግባባትና ቅድሚያውን ለፍቅርና ለአንድነት በመስጠት ግን ይፈታል፡፡
የዕርቁንም ሂደት የተወያዮች ሥልጣን፣ የአወያዮች ሚናና ከውይይቱ በኋላ የሚፈጠሩ ነገሮች ስለሚኖራቸው ገዥነት ግልጽ የሆነ መመሪያ ያስፈልጋል፡፡ ‹እኛ እንዲህ መስሎን ነበረ› የሚለው ችግር የሚወልደው መከራከርያ ወንዝ አያሻግርም፡፡ የዕርቁ ቦታም ሆነ ሂደት የትኛውንም አካል ተጽዕኖ ውስጥ የማያስገባና ጥገኛ የማያደርግ መሆን አለበት፡፡
አሁን የዕርቁ የመጨረሻው ነጥብ ተለይቷል፡፡ ‹አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ ወይስ ክብራቸው ተጠብቆ በአንድ ቦታ ተወስነው ይኖራሉ፣ ሌላ ፓትርያርክም ይመረጣል› አጀንዳው ይኼ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ሁለቱም ወገኖች በየበኣታቸው ተሰባስበው ቁርጡን መናገር አለባቸው፡፡ አማራጮቻቸውንም ማቅረብ ይገባ ቸዋል፡፡ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ አማራጮች ያስፈልጋሉ፡፡ ‹እንትን ወይም ሞት› የሚለው መፈክር ዛሬ የሚሠራ አይደለም፡፡
ይኼ ሀገር ቤት ያለውን ሕዝብ አግልሎ ነገሩን ሁሉ በአሜሪካ መጨረስ ዛሬ መልካም መስሎ ቢታይም ነገ የሚያመረቅዘው ችግር ግን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከመለያየቱም የከፋ ነውና እዚህ ያሉ ሊቃውንት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የገዳማት አባቶች ተጠርተው ስለ ዕርቁ ሂደት፣ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ አቋም፣ ሊሆኑ ስለሚችሉት አማራጮች ሊገለጥላቸው ይገባል፡፡ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን አካላት እንጂ የበጀት ምንጮች ብቻ አይደሉም፡፡ ነገ መልካሙ በረከትም ሆነ ዕዳው የዚሁ ሕዝብ ዕድል ፈንታ ነው፡፡
ለመሆኑ ጸሎት የጽድቅ ሥራ ነው ወይስ የዲፕሎማሲ መግለጫ? ሁለቱ ልዑካን አብረው ጸልየዋል፣ ባርከዋል፣ አስቀድሰዋል፡፡ መልካም፡፡ ታድያ ‹ከእንግዲህ እኛ በጸሎትና በቅዳሴ አንድ ስለሆንን፤ ልጆቻችን እናንተም ዕርቁን ሳትጠብቁ እንድ ሁኑ› ብለው ለምን አልገለጡልንም? ከዚህ በፊት የተከናወነው ውግዘትስ ተነሥቷል እንዴ? ለምን በይፋ አይነገረንም? ሲወገዝ በአደባባይ ሲነሣ ለሦስት አባቶች ብቻ ነው እንዴ? ይህ ጉዳይ ማብራርያ ካልተሰጠው ማደናገርያ ሆኖ ይቀራል፡፡ ወይ በይፋ ውግዘታችሁን አንሡ፣ ወይ ራሳችሁ ያወገዛችሁትን ራሳችሁ ጠብቁ፡፡
አሁን የሚያስፈልገው ወደ ጉባኤው ገብቶ፣ ተከራክሮና ተፋጭቶ፣ ሁሉንም የሚያግባባና ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አቋም ወስዶ፣ አንድ ሆኖ መውጣት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሊቃውንቱ ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ፓትርያርክነቱን ወደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያመጡትኮ በዘመኑ የተሰባሰቡ ሰባ ሁለቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነበሩ፡፡ አሁን ለምን እነርሱ ይዘነጋሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር ነን ብለው ነገር ግን አቡነ እገሌን ሲያገኙ አንድ አቋም፣ አቡነ እገሌንም ሲያገኙ ሌላ አቋም፤ ኢትዮጵያ ሌላ አቋም፣ አሜሪካ ሌላ አቋም፤ የሚያንጸባርቁትንም መገሠጽ ያስፈልጋል፡፡ አቋም መያዝ መብታቸው ነው፤ አራት ዓይነት አቋም በአንድ ጊዜ ማራመድ ግን ለራስም ለቤተ ክርስቲያንም ችግር መሆን ነው፡፡ አባቶችንም አጣብቂኝውስጥ መክተት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment