FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, December 23, 2012

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ነገ ድምፃቸውን ያሰማሉ


ኢሳት ዜና:-<<ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቅና ሰላም ይቅደም>>በሚል መሪ ሀሳብ የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በመጪው እሁድ ከቅዳሴ በሁዋላ የተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ቀረበ።
ደጀ ሰላም እንደዘገበው ላለፉት 20 ዓመታት በውግዘት የተለያዩ አባቶች አንድ እንዲሆኑ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ አንድ አስተዳደርና አንድ ቅ/ሲኖዶስ እንዲኖር ለማድረግ ሲካሄድ የሰነበተው የእርቀ-ሰላም ሂደት በመልካም ውጤት ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ በደረሰበት ጊዜ፤ የታየውን የተስፋ ጭላንጭል በሚያዳፍን መልኩ በጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ግፊት 6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም “አስመራጭ ኮሚቴ” ተቋቁሟል።
“የቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ ያገባኛል” የሚሉ ምእመናን በሙሉ ውሳኔውን በጽኑዕ በመቃወም ላይ ይገኛሉ>> ያለው ድረ-ገጹ፤ይህንን “ከኮምፒውተር ጀርባ” እና በስልክ የሚደረግ የኢንተርኔት ተቃውሞን መልክ ለመስጠት፤ በመጪው እሑድ፣ ቅዳሴ ካለቀ በኋላ በየአጥቢያችን በመሰባሰብ  ሐዘናችንንና መከፋታችንን እንዲሁም በውሳኔው ማዘናችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለመግለጽ መሰባሰብ ይኖርብናል>>ብሏል።
<<ሰንበት ት/ቤቶች፣ ማኅበራት፣ ሰንበቴዎች እና ምእመናን በሙሉ ከሚያውቋቸው ሰዎች በመጀመር ለእሑዱ ቀጠሮ መያዝ እና የመሰባሰቡን ሁናቴ መልክ መስጠት መጀመር ይኖርባቸዋል>>ያለው ደጀ ሰላም፤ << ዓላማችን አንድ ነው። እርሱም <<ስብስባችንን የሚጠሉ ሰዎች በፖለቲካ በማሳበብ በመንግሥት ዱላ ለማስደብደብ የሚያደርጉት ሙከራ እንደሚኖር ስለምናውቅ ከወዲሁ ለሚመለከተው ሁሉ ዓላማችንን መግለጽ እንፈልጋለን። መነጋገር የምንፈልገው ከቅ/ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አባቶች ጋር ነው።>> ብሏል።
<<ባልመረጥነው መጂሊስ አንተዳደርም፣ መንግስት የማንቀበለውን የ አህባሽ አስተምህሮ በሀይል አይጫንብን!>> በማለት  እጅግ በርካታ የ እስልምና እምነት ተከታዮች ያነሱት ተቃውሞ መፍትሔ ሳያገኝ  አንደኛ ዓመቱን እያስቆጠረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ከፓትርያርክ ምርጫ ጋር በተያያዘ  መንግስት  በቤተክርስቲያን አስተዳደር ውስጥም ጣልቃ መግባቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን ለተመሣሳይ ተቃውሞ እንዳይጋብዛቸው ተፈርቷል።
በስደት የሚገኙት አራተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከነ ሙሉ ስልጣናቸውና ክብራቸው ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ በፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አማካይነት ደብዳቤ ከተፃፈ በሁዋላ፤ ውሳኔው እንደገና እንዲቀለበስ መደረጉና መንግስት አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ሆነው እንዲመጡ ፍላጎት የለውም መባሉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በ ኢዮሩሳሌም የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ የሆኑትን አቡነ ማትያስን ለማስሾም እየተንቀሳቀሰ  እንደሆነ በተለያዩ ብዙሀን መገናኛዎች ተዘግቧል።
በዚህም ሳቢያ ቤተ ክርስቲያንን ወደ አንድ ለማምጣት የተጀመረውናታላቅ ተስፋ የታየበት የእርቀ-ሰላም  ጥረት እየተደናቀፈ ነው መባሉ ብዙዎችን የቤተክርስቲያኒቷን ምዕመናን እጅግ ያሳዘነ ሆኗል።
<<ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቀ-ሰላም ይቅደም >>በሚል መሪ ሀሳብ እሁድ ከቅደሴ በሁዋላ ለሚደረገው ተቃውሞ በተለያዩ ማህበራዊ ገፆች ጥሪዎች እየተላለፉ ነው።

No comments:

Post a Comment