ታህሳስ ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የተማሪዎች ዲን የሆኑት አቶ ናትናኤል ህዳር 27 ቀን 2005 ዓ.ም የሚያስተምሯትን ተማሪ ስልክ በመደወል ከምሽቱ 1፡30 ገዳማ ቢሯቸው ድረስ ካስጠሩ በኋላ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደፈጸሙባት ከጎንደር ያገኘነው ዜና ያስረዳል።
የተደፈረችው ተማሪ በግሏ ጥረት ወደ ዩኒቨርስቲው ሆስፒታል በመሄድ አስፈላጊውን የህክምና ምርመራ ያደረገች ሲሆን የምርመራው ውጤትም ተማሪዋ የአስገድዶ መደፈር ሰላባ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው።
ተማሪዋን አስገድደው የደፈሩት ግለሰብ ያላቸውን የኃላፊነት ቦታ እንዲሁም የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑ ወዳጆቻቸውን በመጠቀም የምርመራ ውጤቱን ማስረጃ ከዩኒቨርስቲ ሆስፒታሉ ደብዛውን ለማጥፋት ቢሞክሩም ተጠቂዋ የህክምና ምርመራ ውጤቷን አስቀድማ በመውሰዷ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
የተጠቃችው ተማሪ የህክምና ውጤቱን ማስረጃ በመያዝ ታህሳስ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ለጎንደር ከተማ አስተዳደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያመለከተች ቢሆንም ፖሊስ መረጃውን ተቀብሎ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ የቆየ ሲሆን የተጠቂዋ ተማሪ ቤተሰቦችና አንዳንድ መምህራን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት እና ጫና ታህሳስ 20 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ገዳማ ተጠርጣሪው አቶ ናትናኤል በፖሊስ ተይዘው እንዲታሰሩ ተደርጓል።
ይህ ከሆነም በኋላ የ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊስ አባላት ከጎንደር ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ም/ፕሬዝዳንት ከሆኑት አቶ ሰለሞን አብርሃ ጋር በመሆን ወንጀሉን ለማድበስበስ እና ተጠቂዋ ተማሪን በተደጋጋሚ ስልክ እየደወሉና እየተገናኙ ጫና በመፍጠር ልጅቷ ክሷን እንድታቆምና ነገሩን በእርቅ አሳበው የወንጀሉን ዱካ ለማጥፋት እየተሯሯጡ ይገኛሉ።
የልጅቷን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰቦችም ደፍረዋል የተባሉት ግለሰብ ያላቸውን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና መንግስታዊ ስልጣን ተጠቅመው ወንጀሉን በቀላሉ እንዲጠፋ ሊያስደርጉ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
አስገድደው ደፍረዋል ተብለው የተጠረጠሩት የተማሪዎች ዲን የሆኑት አቶ ናትናኤል ልጅና ሚስት ያላቸው ሲሆን ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከመግባታቸው በፊት በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በወረዳ ካቢኔነት አገልግለዋል።
ለገዢው ፓርቲ ባላቸው ታማኝነትና አገልጋይነት በቀላሉ የዩኒቨርስቲ መምህር መሆን የቻሉ ሲሆን ግለሰቡ ለገዢው ፓርቲ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በሚሰሩት የፖለቲካ ስራ ያለ ትምህርት ዝግጅታቸው እና ያለ ብቃታቸው የተማሪዎች ዲን መሆን ችለዋል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ውስጥ በዩኒቨርስቲው አመራሮች የሚፈጸመው ሙስና ከልክ እያለፈ መምጣቱን የግቢው ሰራተኞች ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment