በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
እንደ ላስኪት እየተወጠሩና እየተለጠጡ ቀዳሚና ትክክለኛ ትርጉማቸውን እየለቀቁና እየሳቱ በሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ሳይቀር በመጣስ ዜጎች እያሸማቀቁ ከሚገኙ የበላይነትና የራስ ጥቅም ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ የሚያራምድ ሀገራትና መንግሥታት ተቀናቃኞቻቸውን ድባቅ ለመምታት ከፈጠራቸው ቋንቋዎች መካከል “አሸባሪ” (ሽብር። ሽብርተኛ) የሚለውን ቃል ተጠቃሽ ነው፣
ቋንቋው ከቋንቋነቱ አልፎ ሁነኛ ፖለቲካዊ ድምጽ አልባ ገዳይ መሳሪያ በመሆን ሲያገለግልም እሄው አሥር ዓመታት አስቆጥረዋል፣ ዓለማችን አሁን የምትገኝበትን ገጽታ በማላበስ ረገድም “በአሸባሪዎችና” በኃያላን መንግሥታት የተከፈተውን ጦርነት የጎላ ሚና ተጫውተዋል፣ ኪዚህም አልፎ በራስ መተማመን ማጣት ከሚፈጥረው ፍርሃትና ውዥንብር ለማምለጥ “ፀረ-ሽብርተኝነት” በሚል ስም ሕግና ደንብ አርቀቀህ ተቀናቃኞችህን የውሃ ሽታ ማድረግ ከተያያዙት ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን በግምት ከሚመሩ ሃገራት መካከልም ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሰለባ ለመሆንዋ የሚያጠያይቅ አይደለም፣
እውነቱ- በሥልጣን ላይ የሚገኘውን የኢህአዴግ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር በትረ ሥልጣን ጨብጠው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን አቆራምተው አራቁተው ካለፉ ገዢዎች መካከል የባሰ አመጸኛ ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ሀገር የሚያደርገው ነገር ቢኖር መሰሬ ማንነቱንና አፋኝ አንባገነናዊ ሥርዓቱን በሕግ የተደጎሰ ለዘብተኛ ሰይጣን መሆኑ ነው፣
ለመግቢያዬ ይህን ያክል ካልኩ ዘንድ ወደ ዋና ርዕሰ ጉዳዬ ስመለስ በአንዳንድ ምክንያቶች የሕትመት ሥራውን የተጓተተብኝ በመጽሐፍ ሥራ ላይ ተይዜ ለጥቂት ወራት ከጠፋሁ በኃላ በዛሬው ዕለት ብቅ እል ዘንድ የተገደድኩበት ምክንያት በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ በተለይ ንጹሐን ዜጎችን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ረገጣ መልኩን ለውጦ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱና እንዲሁም ደግሞ ገዢው ፓርቲ ሕግን ሽፋን በማድረግ ዜጎችን ከማሸማቀቅ አልፎ ለእስርና ለከፋ እንግልት መዳረግ ሥራዬ ብሎ የተያያዘው ኃላፊነት የጎደልው ሥርዓት አላባ ቡድን ሰለባ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ወደ እስር መውረድን ተከትሎ በሀገር ውስጥ የሚገኙትም ሆነ በውጭው ዓለም የተጠለሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ምላሽ ለመቃኘት በተጨማሪም ሁኔታዎችን በማስመልከት ግላዊ አመለካክቴን ለመሰንዘር ነው፣
በተለይ በውጭ የሚኖረው ዳያስፖራ ያነሳን እንደሆነ ከወትረው በበለጠ መልኩ ድምጹ የሚሰማው በአምስት አመት አንድ ጊዜ የምትመጣውን የምርጫ ወቅትና ተለይተው የሚታውቁ የፖለቲካ መሪዎችና ግለሰቦች በገዢው ፓርቲ ወደ እስር ሲወርዱ፦ ይህን ተከትሎ ደግሞ የሚፈጠረው ሞቅታ ለሁላችን ግልጽ ይመስለኛል፣ ያም ሆነ ይህ ግን ሰዎቻችን በታሰሩ ቁጥር አድራጊውና ተደራጊው ከሚገኙበት መልከዓ ምድር ውጭ ሆነህ ይፈቱ! ይፈቱ! ብሎ ጮኸት በሳይንሱ ተሰማርተው በሳል ተሞክሮአቸውን ከሚያካፍሉን ሊቃውንት እይታ አንፃር ሲታይ/ሲመዘን ፈይዳው ድካም ብቻ ሆኖ ሲገኝ ትጮሃለህ ወይስ ትሞታለህ? ለማለት ግድ ብሎኛል፣
በፖለቲካው አለም ሁለት የሚመሳሰሉ ዳሩ ግን የተለያዩ ገጽታዎች አሉ፣ አንዱ በየዋኁ ማኅበረሰብ ዘንድ ስምና ዝና ለማትረፍ ለግል ጥቅም ባንዴራ ታጥቀው ሆ! በማለት የሚያስብሉ፤ ከሀገር ሀገር ከሰፈር ሰፈር ሽርጉድ በማለትም በዜጎች ደም ስር ላይ ሰርጸው ለመግባት የሚተጉ ሲሆኑ ሌላው ደግሞ ስለ ሕዝብ ስለ ሀገርና ስለ ትውልዳቸው ራሳቸውውን ክደው ። ቤተ ዘመዶቻቸውን ትተውና ጥለው ያመኑበት ዕላማ ከገባበት በመግባት መስዋዕትነት በመሆንና በመክፈል በትውልዳቸው ላይ ሰማያት ላይ የተንጣለለው የጨለማ መጋረጃ በመቅደድ ብርሃን የሚሲጡ ናቸው፣ እኒህዎቹ በሕዝቡ ዘንድ እምብዛም ታዋቂዎች አይደሉም በቁጥርም በጣት የሚቆጠሩ እጅግ ጥቂቶች ናቸው፣ ያም ሆነ ይህ ግን ሕዝብ የሚሆነውን ለይቶ የማወቅ ግዴታ እንዳለበት ነው፣
ትጮሃለህ ወይስ ትሞታለህ? ምን አስባለህ በማለት በቅንነት ጥያቃቸውን ለሚያነሱ ወገኖች ቀዳሚ ምላሼ በመታሰር መፈታትን እንጂ በአፍአ ጩኸት የሚወልቅ ሰንሰለት የለምና፣ አንድም የተፈቱ (ላቅ ያለ አመለካከት ያላቸው። የበራላቸው) ሰዎች ሲታሰሩ የታሰሩትን (ብዙሐኑን) ያስፈታሉና፣ ሌላው እንዴት ጩኸት የሚፈጥረው ነገር አለው እንጂ ለሚሉም መጽሐፍ ቅዱስ የኢያሪኮ ግንብ በጩኸት ፈረሰ ሲል ከአፋቸው በሚወጣ ድምጽ ሳይሆን ከአምላካቸው የመጣላቸውን ድምጽ ሳያቅማሙ በመታዘዝ ሞኝነት የሚመስለውን ነገር የህይወት መግቢያና መውጪያ በሆነ በልባቸው ይቅር የኢያሪኮን ግንብ የዓይን ቅንድብ ያንቀሳቅስ ዘንድ በማይቻለው ጩኸት እስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ይቻለዋል፤ እግዚአብሔር ይችላል፤ ለእሱ አንዳች የሚሳነው ነገር የለም፤ ፍጥረት ሁሉ ለእርሱ ይታዛዛሉ፤ ጉልበት ሁሉ ለስሙ ይንበረከል! በሚለውን እምነት ጢም ብሎ በሞላ ልብ ፊት የሰው እጅ የገነባው ግንብ መቆም ስላልተቻለው ሊፈር ችለዋል፣ ይህ ደግሞ ታሪክ ሳይሆን እውነት ነው!! እውነቱነቱን ለማረጋገጥ ደግሞ ሥነ-ጽሑፍን ለማጥናት ደፋ ቀና ማለት ሳይሆን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ማመንታት ለገባህ እውነት በመኖር (መኖር ሲጀምሩ) እውነቱነቱን ማረጋገጥ ይችላሉ፣
ጥያቄው- የትኛው ሕዝብና ሀገር የተጎናጸፈው፤ ያለው፤ ያገኘውና የሚያጣጥመው ነጻነት ለመቋስ ነው ይህ ሁሉ … አሜሪካውያን? እንግዲህ መንገዱ አጭር ነው! አሜሪካም ሆነች አሜሪካውያን የሚታወቁበት ገንዘባችን ለማድረግ ከተፈለገ ያለፉበትን ማለፍ፤ እነሱን መምሰል ነው፣ ይህ ትውልድ (አሜሪካውያን) ዛሬስ በቃን! እስከ መቼ ድረስ! ሲል ግንባሩና ደረቱ ተመቶ የወደቀ አባት እንጂ በሁለት ሃሳብ ላይ ተይዞ ሲመነታ ጀርባው ጥይት በስቶት ሲንደፋደፍ አንጀቱ ተዘርግፎ የሞተ አባት የላቸውም፣
ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” (የዮሐንስ ወንጌል 12፦24) ሲል እንዳስተማረውም አንድ ተክል እንዲገኝ ከተፈለገ ዘሩ በዘርነቱ መሞት እንዳልበት ሁሉ ማለት በመሞት ሕይወት ማግኘት በዕፅዋት አለም የማይታበል ሐቅ ከሆነ ነጻነት እንደ ሰማይ ከዋክብት የራቀበት ከኢትዮጵያዊ ዜጋስ ምን ይጠበቃል ያልን እንደሆነም በጩኸት ፈንታ የታሰሩትን እኛን ለማስፈታት እስከ ሆነ ድረስ እነሱን ለመምሰል ራሳችንን ማዘጋጀት እንደሚገባን ልባችን አይስተውም፣
በፖለቲካው ዓለም ይሄ በትርፍ ሰዓት የሚጮክ ዓይነት ጩኸት ከቁም ቅዥት የተለየ ትርጉም/አንድምታ የለውም፣ አፍ የመጣለት ሲናገር ሳይሆን ልብ የቆረጠለት ዕለት (ሁለት ሞት የለምና) ድል የአንተ ይሆናል፣ ቅድሳት መጻህፍትም ሆኑ ሌሎች የታሪክ መዛግብት የሚለግሱልን የጥበብ ምክርም ሆነ ከውስጣቸው የምናገኘው የተፈተነ ምስክርነትም ይህ ነው፣
ከዚህ ሁሉ ማብራርያ በኋላ አንባቢን ይፈቱ ብሎ ጩኸት ምን ማለት ነው? በማለት ጥያቄን ብሰንዝር በ ”ባህሪው” እንዲሁ ዓይነት ሰው ካልሆነ በስተቀር የሚከፋ ሰው ያለ አይመስለኝም፣ ምንነው ቢሉ? እነዚህ ሰዎች አይደለም መታሰር በእኛ ሞት በኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብ የሚመጣው ለውጥ ካለ በህይወቴ ልትመጣ ያለኸውን ሳትዘገይ ና ና ይህ ባርነት ያደከመው ሕዝብ ይረፍ! በማለት ስራቸውን ያለ አንዳች ስጋትና ፍራቻ ዜግነታዊና ሀገራዊ ግዴታቸውን ሲወጡ የነበሩ ሰዎች በመሆናቸው እንጂ አይ ብንታሰርም መውጣታችን አይቀርም የተባበሩት መንግሥታት። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች። ስቴት ዲፓርትመንት። ኢምንስት ኢንተርናሽናል። በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያውያን ዜጎች … በሚጮኹት ጩኸት በሚፈጥሩት ዲፕሎማስያዊ ተጽእኖና በሌሎች ምክንያቶች የኢህአዴግ መንግሥት ወዶ ሳይሆን ሳይወድ ይፈታል/እፈታላለሁ በማለት የግብር ይውጣ ስራ በመስራት ወደ ውህኒ እንዳልተወረወሩ ባለ ሙሉ እምነትም ነኝ እና፣ እስር ማለት ምን እንደሚመስልና ምን ማለት እንደሆነ ከአንድም ሁለት ጊዜ አውቀዋለሁና፣
እንግዲህ እዚህ ላይ ማወቅ የሚገባን ነገር ቢኖር እንደዚህ ዓይነት ለትውልዳቸው የተሰጡ ሰዎች ከማናችንም ቢሆን ጭብጫባና በስማቸው ቲ-ሸርት አሰርተን እንድንለብሳቸው የሚፈልጉ አይነት ሰዎች ሳይሆኑ እነዚህ ሰዎች ከእኛ የሚፈልጉት ነገር ቢኖር እንቅስቃሴያቸውን ማለት ስለ ፍትህ። ዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር መስፈን እንዲሁም ዜጎች በሕግ ፊት በእኩልነት የሚታዩበትና የሕግ የበላይነት የሚታይበት ሁኔታ ለማየትና ለመፍጠር በተጨማሪም የዜጎች የመናገር። የመሰባሰብ። ሃሳብህን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስከበር ባደረጉትና በሚያደርጉት ትግል ካመንን የጫማቸውን ምልክት እያነፈለፍን እንድንከተላቸው ብቻ ነው፣ እኛን ሲመሩ ከታሰሩ እኛ የእነሱ እነሱ የእኛ መሆናቸውን የምንገልጸው በጩኸት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ ነው፣ ያን ጊዜ ለዓመታት የተገነባ ሴረኛ ሥርዓት ከሥር መሰረቱ ቦቅሰህ ለመጣል የአንዲት ሌት ስራ ብቻ ይሆናል።
በተረፈ አሁንም ወደድንም ጠላንም በኢትዮጵያውን እጅና እግር ላይ የተጠፈረውን ሰንሰለት የሚወድቀው በውል ባለየለት ጩኸት ሳይሆን እግዚአብሔር ፊቱን ወደ ሕዝቡ ሲመልስ/ለድሃና ምስኪን ሕዝብ ሲራራ በዘመናት መካከል በሚሰጠን አንድ ጊዜ ፈጽመው ትኩር ብለው ከተመለከቱ ያዩትን የራሳቸውን ሳይደርጉ የማይመለሱና ለምንም ነገር የማይንበረከኩ ፊታቸው እንደ አንበሳ ኮቴአቸው እንደ ሺህ የፈረስ ድምጽ ጠላቶቻቸውን የሚያርበደብዱ የልጅ የማያባራ ለቅሶና እንባ፤ የእናት ልመናና ምህጽንታ ወደኃላ በማይመልሳቸው። ሆድ በማይብስባቸው ግለሰቦች በሚከፍሉት የእምነት ዋጋና ውጤት ነው፣ ለዚህ ደግሞ ምንም ማስተዣዘኛ አያስፈልገውም፣ ያመነ ከዚህም አልፎ ላመነበትም እምነት የቆመ ሰው አይደለም እስር ሰባት እጥፍ በሚንቀለቀል እሳት ቢወረወርም ይሁንታው ነው፣
የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ሆነ የሌሎች ወገኖቻችን ከእስር መፈታት ሳይሆን የኢህአዴግ አደራሾች የሚሰነጣጥቀው ዜጎች በአንድ ልብና ሃሳብ የእነዚህ የቁርጥ ቀን ሰዎች አሰር ተከትለው/ተከትለን እስከ መጨረሻ ደቂቃ ድረስ ወገባቸንን ሸጥ አድርገን በመታጠቅ መክፈል የሚገባንን ዋጋ ለመክፈል በጽናት ሰላማዊ ትግሉን በማፋፋምና በመቆም ነው፣ ይህን ስናደርግ የማይቀርለት መሆኑን ሲገነዘቡ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ከጎናችን መቆማቸው የማይቀር ይሆናል፣ ፖለቲካ ይሉት ይህን ይመስላልና!!
በመጨረሻ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ቀጣይ እርምጃ “ለእናንተ ለምትጮኹ በደንብ ትጮኹ ዘንድ ድምጽ ማጉልያ ያስፈልጋቸዋል” በማለት ክፍያውን በተወካዮቹ አመካኝነት ፍጽመው ቅርባችን ከሚገኙ ስቶሮች የታዘዘልንን መሣሪያ እንወስድ ዘንድ ማውጫ ወረቀት እንዳይልኩልን ነው የምፈራው፣ ከዚህ ባሻገር ግላዊ አመለካከቴን የማይዋጥለት ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ጽሑፉን በማስመልከት የመስለውን የማለት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ስገልጽ በአክብሮት ነው፣
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com
October 3, 2011
E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com
October 3, 2011
No comments:
Post a Comment