FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, December 23, 2012

የባህርዳር ሹማምንት በከፍተኛ ሙስና ተዘፍቀዋል ተባለ


ኢሳት ዜና:-ለአቶ በረከት ስምኦን የተጻፈ ሚስጢራዊ ደብዳቤ እንዳመለከተው በባህርዳር ከተማ ከንቲባ በአቶ ፋንታ ደጀን አማካኝነት በርካታ ወንጀሎች እየተፈጸሙ ናቸው።
ደብዳቤው በብአዴን ውስጥ ሁለት በጥቅም የተሳሰሩ ቡድኖች መፈጠራቸውን ያመለክታል። አንደኛው ቡድን ደጀኔ ሽባባው በተባለው የብአዴን ጽሀፈት ቤት ሀላፊ የሚመራ ሲሆን በዚህ ቡድን ውስጥ የገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆነው ክብረት ሙሀመድ፣ የከተማ አግልገሎት የቴክኒክ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅር መኮንን፣ የቤቶች ልማት ስራአስኪያጅ አቶ ክንድይሁን እገዘው፣ የንግድና ትራንስፖርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መንግስቴ አምሳሉ እና የጥቃቅን ምክትል ሀላፊ አቶ ሙላቱ ጸጋየ ይገኙበታል።
አቶ ስማቸው ወንድማገኘሁ በተባለው ሰው በሚመራው ቡድን ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ሀላፊው አቶ ቢያድግልኝ አድምጠው፣ የጥቃቅን ጽህፈት ቤት ሃለፊ አቶ ንበረት ታፈረ፣ የገንዘብ ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ ፍትሀነገስት በዛብህ፣ የከተማ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል ሙሉ፣ የትምህርት ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ ሙሉቀን አየሁ፣ የፍትህ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ነጋ ተመስገን፣ የከንቲባ ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ አላዩ መኮንን፣ የጤና ጽ/ቤት ሀላፊው አቶ ወርቅነህ ማሞ፣ የትምህርት ጽ/ቤት ምክትል ሃለፊውን አቶ ሙለጌታ ካሳ እና የከተማዋ ም/ቤት ም/ል አፈ ጉባኤዋ ወ/ሮ አበባ ካህሊው ይገኙበታል።
 ሁለቱ ቡድኖች የዘጌና የደቡብ ጎንደር በሚል የሚታወቁ ሲሆን በቡድኖቹ መካከል ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ትስስር መኖሩ ተገልጿል።በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው በ2004 በተደረገው ግምገማ አቶ ሰማቸው ወንድማገኘው ያለአግባብ በተለያዩ እህቶቹና ወንድሞቹ ስም  ሁለት ኮንዲሚኒየም ቤቶችን መግዛቱ ፣   ሁለት ቪላ ቤቶች መስራቱ ፣  በደብረታቦር ከተማ ውስጥ በራሱ ስም አንድ ቤት እያለው በተሳሳተ መረጃ  200 ካ.ሜ ቦታ መውሰዱ፣ በባህርዳር ከተማ 200 ካ.ሜ ቦታ ወስዶ በት መስራቱ ተጠቅሷል።ፀረ ሙስና ኮሚሽን በግለሰቡ ላይ ምርመራ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በከንቲባው በአቶ ፋንታ ደጀን ጫና ምርመራውና ክትትሉ እንዲቆም መደረጉ ተጠቅሷል።  መረጃውን ያጋለጡ ግለሰቦችም አደገኛ በሆነ መንገድ ክትትል እየተደረገባቸው ከመሆኑም ባሻገር በግልፅ እረፉ አየተባሉ የማሳደድ ስራ እየተሰራባቸው እንደሚገኝ ተመልክቷል።
 አቶ ፋንታና አቶ ስማቸው በከተማው  ውስጥ የዝርፊያና የአፈና የአመራር ቡድን እንዳደራጁ የተጠቀሰ ሲሆን ፣ ከከተማው አመራር በስተጀርባ ሆነው የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ፣ የዲፕሎማሲ ስራ የሚሰሩና የበላይ ጠባቂ  ሆነው ቡድኑን የሚያጠናክሩ ነጋዴዎች፣ የክልል አመራሮች እና ስራቸውን የረሱ የሚመስሉ የፌዴራል ደኅንነቶች እንዳሉበት ደብዳቤው ይጠቅሳል።
በብአዴን አባላት የተጻፈው ደብዳቤ በመጨረሻም “በክልሉ የሚታየው አካሄድ  ስርዓቱንም ሆነ ህዝቡን እየጎዳ ያለና የሰማዕታትንም ደም ከንቱ የሚያስቀር በመሆኑ . ፍትህ የጠፋበትንና ዝርፊያ የተበራከተበትን ከተማ ለህዝባችን ነፃነትና ጥቅም መከበር ሲሉ በተሰውት አእላፋት ጓዶቻችንና ከሁሉም በላይ በቅርብ ቀን ባጣነው ባለራዕይውና ቁርጠኛ ክቡር መሪያችን ስም ችግሩን በመፈተሽ ነፃ እንደምታወጡትና የህዝባችንንም ጩኸት እንደምትመልሱት ተስፋ በማድረግ ነው” በማለት ገልጿል።
ውድ ተመልካቾቻችንና አድማጮቻችን በርካታ የወንጀል ዝርዝሮችን የያዘውን ለአቶ በረከት ስምኦን የተጻፈውን ደብዳቤ በድረገጻችን ላይ የምናወጣው መሆኑን ለመግልጽ እንወዳለን።

No comments:

Post a Comment