በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲከበር፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር እና በዲሞክራሲያዊ ስርኣት ዉስጥ ዜጎች በእኩልነት ሰብኣዊ መብታቸዉ ተጠብቆ እንዲኖሩ የሚያስቡ፡ የሚናገሩ፤ የሚፅፉና የሚቆረቆሩ በጠቅላላዉ ለነዚህ ፅንሰ ሃሳቦች ዘብ የሚቆሙ በሙሉ የስርኣቱ ጠላቶች ተደርገዉ በመቆጠር ላይ ናቸዉ።
ለአገሪቱ አንድነትና ሉኣላዊነት፤ እድገትና ብልፅግና በጣት ከሚቆጠሩ መሪዎቿና የፓርቲያቸዉ ጠባብ ጎሰኛ ፖሊሲ የተለየ የሚያስቡ ዜጎችና ቡድኖች ሁሉ “የስርዓቱ ጠላት” እና “ሽብርተኞች” ወይንም “አሸባሪዎች” ተደርገዉ ይቆጠራሉ።
በመሆኑም ህወሃት/ኢህአዴግ “ሽብርተኞች” የሚላቸዉን ለማሸበርና ለማፈን ባወጣዉ ህግ አገርንና ዜጎችን በማሸበርና ንፁሃንን በየእስር ቤቱ በመወርወር ላይ ከመገኘቱም በላይ ህገ መንግስቱንና የአገሪቱን የፍትህ ስርኣት ለጊዜያዊ ስልጣንና ጥቅሙ በመርገጥና በማዋረድ ላይ ይገኛል።
ህዝብ አመኔታ ያልሰጠዉ መንግስት በምንም መመዘኛ ታማኝ ሊሆን አይችልም። በዜጎች ድምፅና ፈቃድ ሳይሆን በጦር መሳሪያና በማጭበርበር ስልጣኑን እንደተቆጣጠረ ስለሚያዉቀዉ እንደመንግስት ለሚያስተዳድረዉ ህዝብ እምነትና ፈቃድ አይጨነቅም።
በኢኮኖሚ፤ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፍ የሚከተላቸዉ ፖሊሲዎች…. የሚያፀድቃቸዉ አዋጅና ህጎች፡የሚያወጣቸዉ ደንቦችና መመሪያዎች፡ የሚሰይማቸዉ አስፈፃሚ አካላት…. በህዝብ ፈቃድ ላይ የተመረኮዙና ለህዝብ ዘለቄታ ጥቅም እንዲያበረክቱ የሚታሰብባቸዉ አይደሉም።
አምባገነኖች ከስልጣን መንበራቸዉ ዉጭ አርቀዉ መመልከትም ሆነ ማለም አይሹም። አንድም ከስህተቶቻቸዉ ሁለትም ከቀደምት ቢጤዎቻቸዉ ዉድቀትና ዉርደት በመማር እራሳቸዉን ለመለወጥ፡ ከህዝባቸዉና ከፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸዉ ጋር እርቅ ለመፍጠር ቅንነትና ፍላጎት የላቸዉም።
የዛሬዉን እንዴት እንደተቆናጠጡ ስለሚያዉቁት ነገ የእነሱ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም። ወደዱም ጠሉ ትተዉ በሚያልፉት ስርዓት ዉስጥ የፈፀሟቸዉ እኩይ ተግባራት ሊያስከትሉ የሚችሏቸዉ አገራዊ ቀዉሶች በግልም ሆነ በጋራ ተጠያቂነት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ግን አያጡትም።
ነገ በታሰባቸዉ መጠን ዘወትር ዉስጣቸዉ ይረበሻል። የዛሬዉ ማን አለብኝነት፡ህገ ወጥነትና የበላይነት፡ ከነገዉ ተጠያቂነት፤ ዉርደትና ቅሌት አንፃር በፍርርቅ እየታየ ሠላም ይነሳቸዋል፡ ይረብሻቸዋል፤ ያሸብራቸዋል። በመሆኑም ዘወትር ህዝብን ሠላም ይነሳሉ፤ ያሸብራሉ። በየጊዜዉ በፍርሃት እየበረገጉ እንደሚኖሩ ሁሉ ህዝብን በፍርሀት ለማስበርገግ እንቅልፍ ያጣሉ።
ይህ የአምባገነኖች የጋራ ባህሪ ነዉ። ነገ የነሱ እንዳልሆነ ተስፋ በቆረጡ መጠን ለነገ ብሩህ ተስፋ የሰነቀ ሁሉ ሰላም የሚያሳጣቸዉ፡ የሚረብሻቸዉ “ ፀረ ሠላም፡ አሸባሪ” “ ጠላት የሆነ ሃይል” ነዉ መስሎ የሚታያቸዉ። በመለስና በመንግስታቸዉ ላይ የሚንፀባረቀዉ የተስፋ መቁረጥ ባህሪይ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት አገሮችን ተሸብረዉ እንዲያሸበሩ ምክንያት መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም። አይቀሬዉ ዉድቀትና ዉርደት የሚያባንነዉ አገዛዝ ህዝብን በፍርሃት በማሸማቀቅ ቀን ከመግፋት ባሻገር አርቆ ማየት አልቻለም። ስለዉድቀታቸዉና በምትኩ ነገ ሊኖር ስለሚገባዉ የህግ የበላይነት፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት በስዉርም ይሁን በግልፅ የሚያስቡ፡ የሚናገሩ፤ የሚፅፉ ሁሉ የስርኣቱ ጠላቶች ናቸዉ። ስለሆነም “የስርዓቱ ጠላት ” እና “ሽብርተኞች” ወይንም “አሸባሪዎች” ተደርገዉ ሊከሰሱ የሚችሉበት ጭፍን ህግ ተረቅቆና በመለስ አሻንጉሊት ፓርላማ ፀድቆ የስርኣቱ ዘብ በመሆን ያገለግላል።
የፀረ ሽብር ሕጉ በአፈፃፀም ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከመነሻዉ አላማዉ ህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹንና በተሳሳተ ፖሊሲዎቹ ላይ ነፃ አስተያየት የሚሰነዝሩበትን ተቺዎች ለማሸበርና ለማፈን ያወጣዉ በራሱ መንግስታዊ ሽብርን ለማስፋፋት የተረቀቀና የፀደቀ ነዉ።
ህጉ ዜጎች ሃሣብን በነፃነት ለገንቢ ዓላማ መግለፅ እንዳይችሉ ለማፈን፤ በህገ መንግሰት የተቀመጡ የዜጎችን ማህበራዊና ግላዊ ነፃነቶች የሚገፍ፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች…. የአገር ብሄራዊ ደህንነት፤… የህዝብ ሰላም ….. በሚሉ ግልፅነት በጎደላቸዉ አንቀፆች እንዳሻዉ ሊተረጎም በሚችል ገደብ ባጣ መልክ፤ መንግሰት ሊያፍናቸዉና ሊያጠቃቸዉ የሚፈልጋቸዉን ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ሳይሆን፤ የአገሪቱ የበላይ የሆነዉን ህገ መንግሰት በመርገጥ፤ የፍርድ ቤቶችንና የአስፈፃሚ አካላትን መብት በመጣስ የፍትህ ስርኣቱን የጠባብ ዘረኛ ቡድን ፍላጎት ማስፈፀሚያ መሳሪያ ለማድረግ የታለመ ነዉ።
በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ አመለካከታቸዉ በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያላቸዉን የህዘብ ወገኖች ለማዳከም፣ በጠባብ ዘረኝነት ላይ የተመሰረተዉ የፖለቲካ ስርኣቱ አገልጋዮችን ስልጣንና ጥቅም ለማስጠበቅና አገራዊና ብሄራዊ ተቆርቋሪነትን ለማጥፋት የተረቀቀ ነዉ።
በሰላማዊ መንገድ መስተናገድ የሚገባን የህዝብን ድምፅና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማፈን በሐሰት ሽፋን የሚመሰረቱት ተራ ወንጀሎች በሂደት ትርጉም አጥተዉ አገርን የሀሰተኞች፤ የወንጀለኞችና በሃይል እርምጃ ድምፃቸዉን ለማሰማት፤ ፍላጎታቸዉን ከግብ ለማድረስ የሚቆሙ ዜጎች መፈልፈያ እንዳያደርጋት ያስፈራል።
ህጋዊነትን ያልተከተለ አካሄድ ህገ ወጥነትን እንደሚያስከትል ግልፅ ነዉ። ህወሃት/ኢህአዴግ እንደመሳሪያ የሚገለገልበት የፀረ ሽብር ህግ የፍትህ ስርኣቱን ሙሉ በሙሉ እያሽመደመደዉ እንደሆን በፅናት ቆመዉ መናገር ያለባቸዉ ከማናችንም ይልቅ በቅድሚያ የህግ ባለሙያዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። የፍትህ ስርኣት አለኝታ የማይሆነዉ ህብረተሰብ ኑሮዉ አንድም እስር ቤት ተፈርዶበት፤ ሁለትም ሸሽቶ በፋኖነት ከመኖር ዉጭ ሌላ አማራጭ የለዉም።
በየጊዜዉ በመበርገግና በመሸበር በደንቆሮ ግምት እነመለስ በህግ የሚመሩ ለማስመሰል የሚወስዱት እርምጃ የአገሪቱን የፍትህ ስርኣት አደጋ ዉስጥ እንደጣለዉ እንረዳለን።
በሃሰት ክስ ወንጀለኛ ለማድረግ የሚፈፀመዉ የተሳሳተ ተግባር የዜጎች በጋራ አብሮ የመኖርና፡ የመከባበር መሰረት በሆነዉ ፍትህና ዳኝነት ላይ ይቅር የማይባል ከፍተኛ ወንጀል እየፈፀመ መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል።
በርግጥ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል እምነት የታወሩ መሪዎች የዛሬን እስከታደጋቸዉ ድረስ ነገ የእነሱ ባለመሆኑ የፍትህ ስርኣቱ ሊገጥመዉ የሚችለዉ አደጋ ደንታ አይሰጣቸዉም።
በመፈፀም ላይ የሚገኙት ወንጀል ነገ የሚኖረዉ ማህበረሰባዊ ጉዳት፤ በአገርና በወገን የወደፊት ሚዛናዊ ህይወት ላይ የሚያሳርፈዉ እንድምታና ትቶት የሚያልፈዉ ጠባሳ፤ በቀላሉ እንደማይታይ በትክክል መገንዘብ የሚችሉት በህግ የበላይነት የሚያምኑ ሃይሎች ብቻ ናቸዉ።
የፍትህ ስርአቱ መሳቂያና መሳለቂያ የሆነበት ዜጋ ዋስትና የሌለዉ ነዉ። ህይወትና ኑሮ ትርጉም የማይሰጡት ዜጋ ነዉ፡ መብቱን የሚያስጠብቅለት፡ጥቃቱን የሚከላከልለት ሃይልና ከለላ የሌለዉ ዜጋ መሸሸጊያ ካጣ የዱር አዉሬ ተለይቶ ላይታይ ይችላል። ሀይልና ጡንቻ፡ ዉሸትና ቅጥፈት በሚገዙት ህገወጥ ስርኣት ዉስጥ እንዲኖር የተፈረደበት እስረኛ አድርጎ እራሱን እንዲቆጥር ይገደዳል።
በሃሰት በ“አሸባሪነት” ከተከሰሱት ከነአንዱአለም አንዳርጌ፤ እስክንድር ነጋና ሌሎች ተከሳሾች በላይ ዛሬ መለስና ፓርቲያቸዉ ለስልጣን እድሜያቸዉ ማራዘሚያ እንዲያገለግሏቸዉ ክብር የሚያሳጧቸዉ ዳኞችና የፍትህ አካላት ወንጀል እየተፈፀመባቸዉ እንደሆነ በህግ የበላይነት የሚያምን ሁሉ ልብ ይለዋል።
የፀረ-ሽብር አዋጁን በመጠቀም በፍትህ ላይ የሚፈፀመዉ ይህ ወንጀል ከተራዉ ዜጋ ይልቅ በቅድሚያ ሊያስጨንቅና ሊያሳስብ የሚገባዉ ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩትን ባለሙያዎች መሆኑ አያጠያይቅም። ከፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከታች በዘርፉ የሚያገለግሉት የህግ ባለሙያዎቻችን ሁሉ ህሊናቸዉ በፈቀደ መጠን በቅንነት ለማገልገል በምህላ የተቀበሉት ክቡር የስራ መስክ ነዉ።አንፃራዊ በሆነ እኩልነት የዜጎች ማህበረሰባዊ ግንኙነት እንዲጠበቅ ሃላፊነት የተቀበሉና፤ የሞራል ግዴታ የተጣለባቸዉ ዜጎች ተደርገዉ ስለሚቆጠሩ ….
መለስና መንግስታቸዉ ቀናቸዉ ደርሶ ከመንበራቸዉ ሲወርዱም ሆነ ሲዋረዱ ዳኞቻችን እንደደረቡት ካባ አዉልቀዉ የሚጥሉት ሙያ አይደለም።
ዛሬ በሀሰት የወንጀል ክስ የተሰየሙት ዳኞችና አቃቢያነ ህጎች ከህወሃት/ኢህአዴግ ስርአት ዉጭ ነገ ሙያቸዉን መተዳደሪያችን አይሆንም በማለት ሌላ የሙያ ስልጠና ወስደዉ ሌላ ሙያተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ላንጠራጠር እንችላለን። ይሁንና የህግ እዉቀታቸዉ በተሰየሙበት መንበር የሰጡትን ብይን፤የፈፀሙትን ተግባር በየአጋጣሚዉ እያነሳ የራሳቸዉ ህሊና ዳኝነት እየሰጠ ሰላም እንደሚነሳቸዉ ግልፅ ነዉ።
በማህበራዊ ህይወታቸዉ ዉስጥ የትም ይሁኑ የት የህግ ሰዎች ናቸዉና የተዛባ ዳኝነትና ሚዛናዊ ያልሆነ ዉሳኔ በገጠማቸዉ ቁጥር በድፍረት “ይህ ዉሳኔ ትክክል አይደለም” ብለዉ ለማለት የሞራል ብቃት አይኖራቸዉም። እንደሰዉ የሚያስቡ እስከሆነ ድረስ ዘወትር ህሊናቸዉ ይሞግታቸዋል። እስከዕለተ ሞት በህሊና ባርነት ዉስጥ ከመዉደቅ በላይ የሚሰቀጥጥ የፍርድ ዉሳኔ የለምና።
ህወሃት/ኢህአዴግ ጠባብና ዘረኛ የፖለቲካ አላማዉን ከግብ ለማድረስ ላለፉት 20 አመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ በፈፀማቸዉና ዛሬም በሚፈፅማቸዉ መንግስታዊ የሽብር ተግባሮች ምክንያት የአገሪቱ፤ አንድነትና ሉኣላዊነት እንደተሸረሸረ፤ ሀብትና፤ ታሪካዊ ቅርሶቿ አላግባብ እንደተዘረፉ፤ ዜጎቿ እስራት፤ እንግልት፤ ድብደባ፤ ሰቆቃና ግድያ እንደደረሰባቸዉ አለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች በየጊዜዉ ይፋ ያደረጉት ሃቅ ነዉ።
ሰራተኛዉ የአገልግሎትና ሌሎች ማህበራዊ መብቶቹን ያለህግ ተነፍጎ፡ ከስራ፡ ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ታግዶ፡ የንብረት ባለቤትነቱን ተነጥቆ፤…. የገጠሩ አነስተኛ ገበሬ ለባዕዳንና ለባለሃብቶች ጥቅም…. ከይዞታዉ ያለፈቃዱ… ያለ መጠጊያና ያለ ዋስትና ተፈናቅሎ፡…. ረሀብ፤ ድህነትና ግፍ ያስመረረዉ በሌላ በኩል ቤተሰቡን፤ ወገኖቹን የሚወደዉን አካባቢና ታሪካዊ አገሩን ጥሎ መሰደዱን፤ የባዕድ መሬትና ድንበር ሲያቋርጥ በማያዉቀዉ ምድር ለእስር መዳረጉን፤ በባህርና በየበረሃዉ ወድቆ መቅረቱን በጠቅላላዉ በዜጎቿ ላይ ስለደረሰዉና በመድረስ ላይ ስላለዉ ግፍና በደል ከእኛ ይበልጥ በርካታ የዉጭ ምሁራንና አለምአቀፍ ድርጅቶች ምስክርነታቸዉን ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በግል የስልጣን፤ ጥቅምና ጠባብ የጎሰኝነት አላማ በታወሩ መሪዎች ስንገዛና ዉርደት ሲደርስብን የመለስ ዜናዊ አምባገነን አገዛዝ በታሪካችን የመጀመሪያዉ ነዉ።
ይህ ሁሉ ህገ መንግስቱን በመርገጥ የሚፈፀመዉ… ዜጎችንና አገርን የሚጎዳ አካሄድ…. የህግ አግባብነት እንዲኖረዉ፤ ፍትህና ርትእ የሚነግሱበት ስርኣት እዉን እንዲሆን…. በሃይል ሳይሆን በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ….. ከማናችንም በላይ በቅድሚያ እንደዜጋ ድምፃቸዉን ማሰማት፡በተለያየ ዘዴ ቁጣቸዉን መግለፅ የነበረባቸዉ የአገራችን የህግ ባለሙያዎች ናቸዉ ቢባል ስህተት አይሆንም። ከነሱ ዉጭ ለሕግ ጥብቅና ሊቆም የሚችል ሃይል ከቶዉኑ ሊኖር አይችልምና።
በፓኪስታን፤ በህንድ፤ በቱኒዚያና በግብፅ የህግ ባለሙያዎች የህዝብን አመፅ በግንባር ቀደምትነት መርተዋል፡ የሙያ ማህበራቸዉን ጊዜያዊ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ተቋም በማድረግ አደራጅተዋል፡… በህዝባዊ አመፆች ወቅት የመንግስት ሃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀሟቸዉን የህግ ጥሰቶች መዝግበዉ ይዘዋል፡… ለሰብኣዊ መብት አስጠባቂ ድርጅቶች እና የዉጭ አገር የዜና ማሰራጫዎች ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል።
በተለያዩ የዉጭ አገሮች ዉስጥ የህግ አዉጪ አካላት ከህዝባቸዉ በተሰጣቸዉ ህጋዊ ዉክልና መሰረት የዜጎችን ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር መንግስታቸዉን ይነቅፋሉ፡ይተቻሉ። ከዚህ አልፈዉ ተርፈዉ ስሜታቸዉን መቆጣጠር ተስኗቸዉ በፓርላማ ዉስጥ እስከመደባደብ የደረሱበትን ሁኔታ ታዝበናል።
በርግጥ እኛ ለዚህ አልታደልንም። ፓርላማችን ጠ/ሚሩ የሚሰነዝሯቸዉ ያልታረሙና ስነምግባር የጎደላቸዉ አባባሎች የሚያስፈነድቋቸዉ፡ ለህዝብ ሳይሆን ለመለስና ድርጅታቸዉ ተጠሪ የሆኑ የአሻንጉሊቶች ስብስብ መሆኑ አይጠፋንም።
የህግ ባለሙያዎቻችን ለሕጉ አተረጓጎምና አፈፃፀም አገራዊ ሃላፊነት ስላለባቸዉ ስብዕናቸዉ ፈተና ዉስጥ መዉደቅ ነበረበት። የስርዓቱ ተጠቃሚ በመሆናቸዉ በህሊና ባርነት የሚታሰሩበት ምክንያት ሊኖር ባልተገባ ነበር።
የደረቡት ካባ፡የተሰየሙበት ችሎትና የተጣለባቸዉ ማህበረሰባዊ ግዴታ ከፊት ለፊታቸዉ በተከሳሽ ሳጥን ዉስጥ በሰንሰለት ታስረዉ ለሚቆሙ ፍትህ ፈላጊ ወገኖች ሚዛናዊ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችላቸዉን የአእምሮና የሞራል ፅናት ሊያድላቸዉ በተገባ ነበር።
ግና ለዚህ አልታደልንም። ከህሊና ነፃነት ይልቅ ባርነትን፤ ከሞራል ፅናት ይልቅ ዉድቀትን የመረጡ የህግ ባለሙያዎች ለፍትህ ስርዓታችን ዘብ መቆም አልቻሉም።
ሚዛናዊ ፍትህ ለማግኘት ፍርሀት፤ እልህና ሲቃ እየተናነቀዉ…ዓይን ዓይናቸዉን እየተመለከተ፤ ታሳሪዉ ““በማዕከላዊ እስር ቤት ግፍ ተፈጽሞብኛል፡፡ ከወንጀል ምርመራ ሃላፊ እስከ ታችኛው ወንጀል መርማሪ ሠራተኛ ድረስ ያሉት አንድ ላይ ሆነው ልብሴን ሙሉ በሙሉ አስወልቀው ውሃ እየደፉብኝ ለ23 ቀናት አሰቃይተውኛል፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን እንድናገር ጠይቀውኝ አልናገርም በማለቴ 7 ቀን ምግብ እንዳልበላ፣ እነሱ የሚሉኝን የማልናገር ከሆነ አትቀመጥም አትተኛም ብለው በቁም እንድሰቃይ አድርገውኛል፡፡ እጄን ወደ ኋላ አስረው አሰቃይተውኛል። ድብደባና ግርፋት ደርሶብኛል….. በደልና ግፍ ተፈፅሞብኛል…..” በማለት ቤተሰብና ህዝብ ታዛቢ በሆነበት ችሎት ላይ አቤቱታ እየቀረበ…..
የዓቃቤ ህግ ምስክር “…. እንዲህ ብለህ ተናገር ተብዬ ነዉ የመጣሁት… ፖሊስ እንዲህ ብለህ መስክር አለኝ…. አሳየኝ፡ ጠቆመኝ…” በማለት …. ቅን ህሊና ያስገደደዉ ወጣት፤አዛዉንት፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ፤ የልጆች እናት የከበዱና ምራቃቸዉን የዋጡ በእድሜ የገፉ አረጋዊ፤ የተማረ፡ በሃላፊነት ላይ የነበረ፤ ለአገር ህልዉና የተሰለፈ የጦር መኮንን፡…… የገጠመዉንና የደረሰበትን እዉነት በአደባባይ ሲናገር፤ ሲመሰክር… በፍትህ መንበር ላይ ተቀምጦ በችሎቱ አዳራሽ ሁሉንም እያየና ጆሮዉ እየሰማ ለቀረበዉ አቤቱታም ሆነ ለተፈፀመዉ ህገ ወጥ ተግባርና ምስክርነት ህሊናዉ ኮርኩሮት አንዳች እልባት ካልሰጠ እሱ ከአምባገነን አዛዦቹ በከፋ መልኩ ህግ እያወቀ ፍትህን በመርገጥ ላይ እንደሚገኝ በድፍረት መናገር ይቻላል።
“ ክሱ የወንጀሉን አፈፃፀም፡ ቦታና ጊዜ አያመለክትም፡ ህገ መንግስታዊ መብትንና አገሪቱ የተቀበለችዉን አለም አቀፍ ድንጋጌ ይፃረራል” በማለት የተከሳሽ ጠበቆች ለሚያቀርቧቸዉ የክስ መቃወሚያዎች ምንም አይነት ግንዛቤ የማይሰጥ ዳኛ አካሉ እንጂ ህሊናዉ በችሎት ወንበሩ ላይ ተሰይሟል ለማለት አስቸጋሪ ነዉ።
ባለፈዉ ወር ዉስጥ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት የአገሪቱን የግዛትና የፖለቲካ ሉአላዊነት በመጣስና በአሸባሪነት ለተፈረጀው ኦብነግ ድጋፍ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ በመሰረተባቸው 2 ስዊዲናውያን ጋዜጠኞች ላይ የ11ዓመት ፅኑ እስራት መፍረዱ ይታወቃል።
ህወሃት በአለምአቀፍ ሽብርተኝነት ዝርዝር ዉስጥ እስካሁን ስሙ ተመዝግቦ የተቀመጠ ፡በሽብር ያደገና አሁንም በሸብር ተግባር የተሰማራ መንግሰታዊ ስልጣን የተቆናጠጠ ቡድን መሆኑን በነአንዷለም አራጌ በተከፈተዉ የክስ መዝገብ በሌለበት “ በአሸባሪነት “ ክሱ በመታየት ላይ ያለዉ የአዲስ ቮይስ ድረገፅ አዘጋጅና የኢሣት ጋዜጠኛ አበበ ገላዉ ከአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማግኘት ይፋ ያደረገዉ ማስረጃ ይገልፃል። በሌላ በኩል በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ቀራንዮ አካባቢ በተፈፀመ ወንጀል የጠ/ሚር መለስ መንግሰት እጅ እንዳለበት ከአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ ያገኘዉን የኬብል ግንኙነት መረጃ ዊኪ ሊክስ በተጨባጭ በመላዉ አለም እንዳሰራጨዉ ይታወቃል።
በጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌና በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር በነአንዷለም አራጌ ላይ የተመሰረተዉን ክስ በተመለከተ በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አፈቀላጤ ሆድ አደሮቻቸዉ በረከት ስምኦንና ሽመልስ ከማል ተከሳሾቹ ጥፋተኛ እንደሆኑና በቂ ማስረጃ እንደተገኘባቸዉ ባደባባይ ምሰክርነት መስጠታቸዉ በፍትህ ስርኣት አፈፃፀም ተገቢ እንዳልሆነ ድምፃቸዉን በቅድሚያ ማሰማት የነበረባቸዉ ከተራዉ ዜጋና ጋዜጠኛ ይልቅ የህግ ባለሙያዎቻችን ናቸዉ።
የሙያ ስነምግባር የሚሰማዉ ዳኛ ቢሆን ክሱን ከመስማት ይልቅ ከችሎቱ ለመነሳት በገዛ ፈቃዱ ጥያቄ ባቀረበ ነበር።
በግንቦት 97 የተካሄደዉን ምርጫ ተከትሎ የጠ/ሚር መለስ መንግስት ድምፃቸዉን ለማስከበር የወጡ 193 ዜጎችን በአደባባይ ገድሎ፤ የቅንጅት አባላትን፤ ጋዜጠኞችንና የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ሰላማዊ ዜጎችን በወንጀል የከሰሰበትና የእድሜ ልክ እስራት የወሰነበትን ችሎት በመሃል ዳኝነት የመሩት አዲል አህመድ በዚያ ችሎት ከመሰየማቸዉ በፊት በነበረባቸዉ የስነ ምግባር ድክመት ምክንያት በዳኞች ጉባዔ ዉሳኔ መሰረት ከዳኝነት ተግባር ታግደዉ እንደነበር የተደረሰበት ታሪካቸዉ የሚጠቁመን ሀቅ አለ። ህወሀት/ኢህአዴግ በፓርቲ አባልነት፤ በገዢዉ ጎሳ ተወላጅነት፡ አሊያም ዳኝነቱ በይግባኝ መገልበጡ ላይቀር ከተሰጠዉ መመሪያ ዝንፍ ካለ እራሱ በገመዱ እንዲገባ በአንገቱ ሸምቀቆ የገባለት – ያለ ታማኝነት ወይንም ያለ ዉርደት የሃሰት የወንጀል ችሎት የዳኝነት መመዘኛ እንደሆነ አስገንዝቦናል።
ምንም ይሁን ምን ለህሊናዉ ያላደረ ዳኛ ግዑዝ መገልገያ ከመሆን ባለፈ ለራሱም ለህብረተሰብም የሚሰጠዉ ጥቅም የለም።
ቀሰሙት የሙያ እዉቀት በቃለ መሃላ የተቀበሉትን ክቡር ሙያ አዋርደዉና ረግጠዉ ከህዝብ ዳኝነትና ከህሊና ወቀሳ ሳያመልጡ ከመኖር የከፋ ፍርድ በሰዉ ልጆች ላይ ሊደርስ አይችልም።
በፍትህ ስርኣቱ ላይ በመንግሰትና በአገሪቱ የህግ ባለሙያዎች ከሚፈፀመዉ ወንጀል አልፎ ተርፎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢ.ቲ.ቪ.) ጣቢያ አማካይነት የሙያ ስነ ምግባር በጎደላቸዉ ጥቂት ጋዜጠኞችና የመንግሰት ሆድ አደሮች የተፈፀመዉ ተግባር በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተፈፀመ ሌላ ወንጀል ነበር። ከድጡ ወደማጡ ይሉትን አይነት መንግስታዊ ዝቅጠትም ነዉ።
“አኬልዳማ” በሚል ርእስ በሶስት ክፍል ተቀናብሮ የቀረበዉ ፊልም በተለያየ ወቅት ሲቀርቡ ከነበሩ መረጃዎች በስርቆት ተቆርጠዉ የተቀጠሉ የትዕይንቶች ቅጥፈት ሲሆን የፍትህ ስርኣቱን እስከመጨረሻዉ ያዋረደ የመሃይማን ስራ ነበር።
ቀጥተኛ የርእሱ ትርጉም “ የደም መሬት “ የሆነዉ ይህ ሁዋላ ቀር የፊልም ስራ መለስ፡ ፓርቲያቸዉና መንግስታቸዉ የአንድ ጠባብ ዘረኛ አምባገነን ቡድንን የበላይነት ቅዠት በሃይል ለማስፈፀም ባለፉት ሃያ አመታት ዉስጥ አገሪቱን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በዜጎች ደም እንዳጨቀዩዋት በግልፅ የሚያሳይ በመሆኑ ለተካሄደዉ መንግስታዊ ሽብር ሁሉ ተአሚኒ የሆነ ጠቃሚ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።
”አኬልዳማ” ጊዜ ሲፈቅድ የስርኣቱን ቁንጮዎችና ተንበርካኪዎች በህግ እንድንጠይቃቸዉ ይረዳናል። የክስ ቻርጁን አቃቤ ህጉ በንፁሃኑ ላይ ያቀረበዉን ወንጀለኛ ወደሆኑ የአገሪቱ መሪዎች ለዉጠን እንደሚከተለዉ ልናነበዉ የምንችልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
“አኬልዳማ” ወይንም ” የደም መሬት” ሕወሃት/ ኢህአዴግ በአገር ዉስጥ ህገ መንግስቱን በመርገጥ፤ በመንግስትነት የያዘዉን ስልጣን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ ከግንቦት 1983 ዓ.ም ጀምሮ አምባገነኑንሥርዓት በተደራጀ መንግስታዊ የሽብር ድርጊት ለማቆየት ሰላማዊ የሆኑ አገራዊ ራዕይ ያላቸዉን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለማጥፋት የተለያዩ የሽብር እቅዶችን በመንደፍ በአገር ዉስጥ በሕቡእ እና በግልፅ ባቋቋማቸዉ የፖሊስ፤ የመከላከያ፡ የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮችና ተቋማት አማካይነት ፡ በቀጥታ የመራ፣ ለሽብር ሥራ የመንግስት ሃይሎችን ያሰማራ፣ በተለያዩ ዘዴዎች የተለያዩ የሽብር ቅስቀሳዎች በማድረግ፣ ህግ በማዉጣትና ዉሳኔዎችን በማስተላለፍ አገርንና ንፁሃን ዜጎችን የጨፈጨፈ፡ ምድሪቱን በደም ያጠበና ወደፊትም ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ የቂም፤ የመጠፋፋትና የአፍራሽ ተግባር የፈፀመ ወንጀለኛ ድርጅት ነዉ። የፈጠራ ተዉኔቱ በራሱ በህወሃት/እሀአዴግ ላይ በሀሰት ሳይሆን በተጨባጭ በህዝብ ላይ የተፈፀመ ወንጀል የቪዲዮ ማስረጃ ሆኖ በነመለስ ዜናዊ የወንጀል ክስ መዝገብ ላይ የሚቀርብ ነዉ።
ይኸዉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት በነኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በአሸባሪነት ተጠርጥረው የተከሰሱትን፤ የEthiopian Review ድረ ገፅ ዋና አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌን በዕድሜ ልክ፤ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዕዮት ዓለሙን በ14 አመት እስራትና በ36 ሺህ ብር ቅጣት፤ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረዉን ውብሸት ታዬን በ14 አመት እስራትና በ33ሺህ ብር ቅጣት፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪ የሆኑትን አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሄርን በ17 አመት እስራትና በ50 ሺህ ብር ቅጣት፤ ሂሩት ክፍሌን በ19 አመት እስራት እንዲቀጡ ፤ እንዲሁም አምስቱም ተከሳሾች ለአምስት አመት ያህል ከህዝባዊ መብቶቻቸዉ (የቶቹ መብቶች?) እንዲታገዱ ፈርዷል።
አሁን የሚጠበቀዉ በግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ውስጥ አመራርና አባል በመሆን የአገሪቱን ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን በኃይል ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው በሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው፣ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ ስምንት በአገር ያሉ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሸዋስ ይሁንዓለም፣ ክንፈ ሚካኤል አበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው እና በሌሉበት ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉት እንዲከላከሉ የጥፋተኛነት ብይን በተሰጠባቸዉ ተከሳሾች ላይ የጠ/ሚር መለስ ዜናዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት የሚሰጠዉ ፍርድ ነዉ።
ብይን የተሰጠበት የዚህ ክስ የችሎት ሂደት ፍትህ ማላገጫ የሆነበት እንደነበር አይዘነጋም። ጠ/ሚኒስትሩ ታህሳስ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በፓርላማ ተገኝተዉ “አሉን” ያሏቸዉ ክምር የሰው፣ የሰነድ፣ የምስልና የድምፅ ማስረጃዎች የችሎቱን ተኣሚኒነት ከገለባ ያቀለሉት ነበር። አበል ተከፍሏቸዉ፡ ሆቴል ተይዞላቸዉ፡ በመደለያ፤ በምክርና በስልጠና የቀረቡት የአቃቤ ህግ ምስክሮች፡ በቀረቡላቸዉ መስቀለኛ ጥያቄዎች፤ ከህሊናቸዉ ሙግት ሲገጥሙ፤ ላብ ሲያጠምቃቸዉ፡ በሙሉ አይናቸዉ የችሎቱን ታዳሚ ለማየት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ከገጠማቸዉ ጭንቀትና መረበሽ የተነሳ ከአይናቸዉ የእልህ እንባ ሲፈስ፤ መመልከት ለፍትህ ስርኣታችን ከፍተኛ ዉርደት ነዉ፡፡
በህገወጥ መንገድ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት የተጠርጣሪ ተከሳሾቹን ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ፖስታና የመሳሰሉ መገናኛዎችን በመጥለፍ ተቀናብረዉ የቀረቡት የድምፅ ማስረጃዎች የክሱን ጭብጥ በግልፅ ያላገናዘቡ፡ ባዶ ጫጫታዎች ከመሆን ሌላ በፅሁፍ ተገልብጠዉ ከተሰጡት ጋር ልዩነት የታየባቸዉ ነበሩ።
በመላዉ አለም በአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ያላሰለሰ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትና መዋጮ ሚዛናዊ መረጃ ለማቅረብ የሚተጋዉን ብቸኛና ገለልተኛ የህዝብ ልሳን የሆነዉን የኢሳት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የግንቦት ሰባት ልሳን ናቸዉ ብሎ በመፈረጅ በምትኩ ‘አኬል ዳማ” በሚል የፈጠራ ተዉኔት በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኘዉን ክስ ለህዝብ የተሳሳተ ዳኝነት ያቀረበዉን የኢትዮጵያ ቴሌቪዢንን የፈጠራ ተዉኔት “ የችሎት ጉዳይ ዘገባ ሆኖ አላገኘነውም” በማለት በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን መስጠት አገራችን በየደረጃዉ ፍትህና ርትእ ወደጎደለዉ ብልሹ ስርአት በማዝገም ላይ እንዳለች ገሃድ ምሰክር ነዉ።
አቃቤ ህግ ያቀረበበትን ማስረጃ ተመልክቶ ፍርድ ቤቱ ክሱን ዉድቅ ያደረገለት ክንፈ ሚካኤል አበበ ዉድቅ በተደረገ ማስረጃ የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ስሙን በማጉደፍ ላይ እንዳለ አቤቱታ ቢያቀርብም ሰሚ አላገኘም።
“ አቃቤ ህግና የደህንነት ሰዎች በጓደኞችሽ ላይ ብትመሰክሪ በነፃ ትለቀቂያለሽ” ብለዉኛል በማለት ወጣት ሴት ልጅ በድፍረት ያቀረበችዉን አቤቱታ በዝምታ ለማለፍ ያስቻለዉ፡ የራሱን ማንነቱንና ምን እየሰራ እንደሆን ህሊናዉ የማያስገድደዉ ዳኛና የፍትህ ስርአት በራሳቸዉ ሕጋዊ ሰዉነት የሌላቸዉ ከመሆን አያልፉም።
ዉሳኔ ያላገኘን በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ለተዛባ የህዝብ ዳኝነት “ አኬልዳማ” የተሰኘዉን የፈጠራ ስራ በማቅረብ ድፍረት ለፈፀመዉ መንግስታዊ የቴሌቪዢን ጣቢያ ጥብቅና በመቆም “ፍርድ ቤቱን እየደፈርህ ነዉ፡ይህ ድርጊትህ ሊያስቀጣህ ስለሚችል ብትጠነቀቅ ጥሩ ነው፤” በማለት የፍርድ ቤቱ መብት እንዲከበር አቤቱታ ላቀረበ ተከሳሽ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ዳኛ በእዉነት ህግን በንፁህ ህሊና ለመተርጎም የተቀመጠ ነዉ? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።
የፍርድ ቤቱ ሥልጣን እየተጣሰ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለፍትሕ በእውነት የሚሠራ ከሆነ ዕርምጃ እንዲወስድ አንዱአለም አራጌ ያቀረበዉ ጥያቄና የችሎቱ መልስ በእዉነትም ፍርድ ቤቱ ለማን እንደቆመና እንዴት እንደሚሰራ ሀቁን መስክሯል። ከዚህ በላይ የፍትህ ስርኣታችን ሲዋረድ፤ የህግ ባለሙያዎቻችንም የተከበረ አገራዊ ሙያቸዉን ለጊዜያዊ ጥቅም ሽጠዉ ሲንበረከኩ የምንመለከትበት ጊዜ አይኖርም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሽብርተኝነት ክሱንና የፍርድ ቤቱን ሂደት “ በንግግር ነፃነት ላይ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ስድብና ጀብደኝነት“ በሚል ባወጣዉ መግለጫ ተከሳሾቹ የህሊና እስረኞች መሆናቸውን ገልጿል። ጥፋተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይኖራል ብሎ እንደማያምን አስታዉቋል።
በድርጅቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተመራማሪ ክሌይር ቤስተን “ በተከሳሾቹ ላይ የቀረቡት አብዛኛዎቹ የክስ ማስረጃዎች በመንግስት ላይ ሰላማዊ ተቃዉሞ ለማካሄድ የተደረጉ ጥሪዎች ናቸዉ። ሌሎች ማስረጃዎች ደግሞ ተከሳሾቹ የጻፏቸዉ ፅሁፎችና ሌሎች ግለሰቦች የላኩላቸዉ ናቸዉ። ይህ የሚገልፀዉ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በችሎቱ ላይ እንደተወነጀለና በመንግሰት ላይ ትችት ማቅረብ ወንጀል መሆኑን ነዉ። ሂደቱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ሰዎች፤ የተለየ ሃሳብ ያላቸዉ ግለሰቦች፡ወይም በፖለቲካዉ ሂደት ላይ ገለልተኛ የሆነ ትችት ለመሰንዘር የሚሞክሩ ሰዎች በኢትዮጵያ ዉስጥ ስፍራ እንደሌላቸዉ ያመለክታል።” ብለዋል።
ሌስሊ ሌፍኮው በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪ በበኩላቸዉ “ኢትዮጵያ የፀረ ሽብሩን ህግ ፣ ነፃ ዘገባንና ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄድን ለማፈን እንደምትጠቀምበት ያረጋግጣል” ብለዋል። “ዛሬ በፖለቲካ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሚዛናዊ ፍርድ የማይቻል ነዉ፡ ክስ ሳይመሰረትና ለፍርድ ሳይቀርቡ ተጠርጣዎች እስከ 4 ወር ለሚደርስ ረዢም ጊዜ በእስር የሚቆዩበት ከአለም የመጀመሪያዉ ፀረ ሽብር ህግ ሲሆን ህጉ በኢትዮጵያም ሆነ በአለም አቀፍ ህግ የተረጋገጠዉን የሰዉ ልጆች መብት የሚፃረር ነዉ። ወደፊትም ህጉ አላግባብ መጠቀሚያ እንዳይሆንና ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር የተጣጣመ ደረጃ እንዲኖረዉ በህጉ ላይ የተጠቀሱ እጅግ መጥፎ አንቀፆች በአስቸኳይ መስተካከል ይኖርባቸዋል” በማለት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪ አስገንዝበዋል።
ለቱም አለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችና ሌሎች ማህበራትና ድርጅቶች ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተቃዋሚ የሆኑት የህሊና እስረኞች የተከሰሱት ህጋዊና ሰላማዊ የሆነ ተግባራቸዉን በማከናወናቸዉ በመሆኑ ሊፈቱ እንደሚገባ ድምፃቸዉን ከማሰማት አልተቆጠቡም። ለጊዜያዊ ጥቅም የተንበረከኩ የህግ ባለሙያዎቻችንና የገዢዉን ጠባብ ቡድን ፍላጎት ለማስጠበቅ ዘብ የቆመዉ የፍትህ ስርአታችን እዉነቱን መስማትና መቀበል ቢገዳቸዉም። ከህወሃት /ኢህአዴግ መሪዎች ጋር የህግ ባለሙያዎቻችንም ፍትህ ስትረገጥና ማላገጫ ስትሆን በዝምታ በማየታቸዉ ብቻ ሳይሆን ለህግ የበላይነት ድምፃቸዉን ባለማሰማታቸዉ በጋራ ሊጠየቁ እንደሚገባ ሳንጠቅስ ማለፍ አይቻለንም።
የዛሬዋ ኢትየጵያ የዘመናት አኩሪ ታሪኳና የፍትህ ስርዓቷ በጎሰኛ አምባገነን መሪዎችና ተንበርካኪ ሃይሎች የሚዋረድባት፡ ታሪክ ይቅር የማይለዉ ወንጀል የሚፈፀምባት፤ ፤ ….በተቃራኒዉ ለህግ የበላይነት የሚታገሉ እዉነተኛ ዜጎች ህግ ለማስከበር ሙያዊ ግዴታና አደራ በተጣለባቸዉ፤ ….ነገር ግን ጊዜያዊ ስልጣን፤ ጥቅም፤ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ጠባብ የዘረኝነት አመለካከት የህሊና ነፃነት በነፈጋቸዉ የህግ ባለሙያዎች በፍትህ አደባባይ ወከባና በደል እንዲደርስባቸዉ የሚደረግባት ያልታደለች አገር ናት።
“አዉጫጪኝ” “አፈርሳታ”ን የመሳሰሉት በላ ልበልሀ የምንባባልባቸዉ ባህላዊ የማህበረሰብ አኩሪ የፍትህ መድረኮች የነበሩን ብቻ ሳይሆን የክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሚያድርብን ፈሪሃ እግዜአብሄር “የተናገሩት ከሚጠፋ፤ የወለዱት ይጥፋ” በሚል ይትብሃል ለፍትህና ለህግ ትልቅ ክብርና ግምት የነበረን ሰዎች እንደሆንን ግልፅ ነዉ።
በዚህም ምክንያት የፍትህ ስርኣቱ ሲዋረድና፤ አልፎ ተርፎ የሕግ አዋቂዎቻችን ለፍትህ ስርኣቱ ዘብ በመቆም ፈንታ ደንታ ቢስ ሲሆኑ መመልከት እጅግ ያሳስበናል። ነገ የሚያስተዛዝበን ሌላ ቀን እንደሆን እናዉቃለንና…
ንጉሴ ጋማ
Ethiopiazare.com
No comments:
Post a Comment