ታህሳስ ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ሀላፊ የኢህአዴግ አባል ሆነው ለክልል ምክር ቤት አባልነት ምርጫ መወዳደራቸውንም አጋልጧል::
ጊዜያዊ ኮሚቴው ለምርጫ ቦርድ ባቀረበው 18 ጥያቄዎች ማስረጃ ያላቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን ምርጫ ቦርድን ለፓርላማ አፈጉባኤ እንደሚከስ አስታውቋል::
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአስተባባሪ ኮሚቴው የቀረቡት 18 ጥያቄዎች ማስረጃ የላቸውም ብሎ ጥያቄዎቹን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው ወሳኝ ያላቸው ማስረጃዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ኮሚቴው ይፋ ያደረገው:፡
ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚዎች የቀረቡትን ቅሬታዎች ለወር ያህል ከገመገምኩ በኋላ ሰጠሁ ያለው ምላሽ አሳፋሪና ነገ በህዝብ ዘንድ የሚያስወቅስ መሆኑን ያመለከተው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስረጃ እንድናቀርብ ሳይጠይቀንና ሳያነጋግረን ውሳኔውን በመንግስት ሚዲያ ማወጁ አሳዝኖናል ብለዋል::
የጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴው አባልና የቦርድ አመራር አቶ ገብሩ ገብረማሪያም ከጋዜጠኞች ምን ማስረጃ አላችሁ ተብለው ለቀረበ ጥያቄ ለሁሉም በቂ ማስረጃ አለን በማለት የምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሬት ዳይሪክተር ወ/ሮ የሺ ፍቃደ የኢህአዴግ አባል ሆነው ለምርጫ የተወዳደሩበት ማስረጃ አቅርበዋል::
የክልል ም/ቤት አባላት ምርጫ ጣቢያ የድምጽ ቆጠራ ውጤት መተማመኜ በሚለውና የምርጫ የምርጫ ቦርድ አርማ ባለበት በዚህ ሰነድ የእጩ ተወዳዳሪዋ የወ/ሮ የሺ ፍቃደ ስም የሚገኝበት፡ በብአዴን ፓርቲ በንብ ምልክት ፡ እየታዩ ያመጡት የድምጽ ብዛትና ደረጃቸው የሰፈረበት ፡ ለአማራ ክልል ምክር ቤት የደብረ ብርሀን እጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸውን ያሳያል::
የጊዜያዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ አንድም ማስረጃ የሌለው ጥያቄ አላቀረብንም ፡ ካሉ በኋላ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግ ጉዳይ አስፈጸሚ በመሆኑና ሊያነጋግረንም ፡ ማስረጃ እንድናቀርብ ሳይጠይቀንም ጥያቄያችሁን ውድቅ አድርጌያለሁ ማለቱ እንዳሳዘናቸው ገልጠዋል::
No comments:
Post a Comment