FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, December 24, 2012

ሰበር ዜና – ማኅበረ ቅዱሳን ራሱንና የአባላቱን አቋም በመፃረር በፓትርያሪክ ምርጫው ለመሳተፍ ወሰነ


 ሐራ ዘተዋሕዶ
  • ማኅበሩ ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የሰጡትን አስተያየት አስተባብሏል
  • የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ ከመንግሥት ለተመደቡት ባለሥልጣን እገዛ ትሰጣለች
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በማኅበሩ ጥቂት አመራሮች አቋም ግራ ተጋብተዋል
  • የማኅበሩ የሰሜን አሜሪካ ማእከል ሰብሳቢ የአቋም ለውጡን በመቃወም ‹‹ውሳኔው አያስማማንም፤ የማስቀድመው ዕርቀ ሰላሙን ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ አንድነት የሚያመጣ ዕርቀ ሰላም መፈጸም ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር አንጻር፣ ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ከማሰብ አንጻር፣ መንጋውን ከማነጽና ሐዋርያዊ
Uganda, Kampala Ethiopian Orthodox Church
Uganda, Kampala Ethiopian Orthodox Church
አገልግሎትን ከማቅናት አንጻር ለአባቶቻችን ግዴታ ይኾንባቸዋል፡፡ የሚፈለገው ዕርቀ ሰላም እውን እንዲሆንም ለእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ለእውነት፣ ለኅሊና ምስክርነት መገዛት አግባብ ይሆናል›› – ይህ መልእክት በሐመር መጽሔት፣ 20 ዓመት ቁጥር 8፣ ታኅሣሥ 2005 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የወጣ፣ በድረ ገጹም የተደገመ የማኅበረ ቅዱሳን አቋም ነው፡፡ ይህ የማኅበረ ቅዱሳን መልእክት‹‹ከምርጫው ይልቅ ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም››ከሚለውና ማኅበሩ የበለጠ ከሚታወቅበት አቋሙ የመነጨ ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በመልእክቱ ዕርቅ÷ ‹‹በቤተ መቅደሱ ዕለት ዕለት መሥዋዕት ለሚያቀርቡ፣ ብዙዎችን በጸጋ እግዚአብሔር ባዕለጸጋ ለሚያደርጉ፣ ምስጢራትንም ሁሉ ለሚፈጽሙ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ምልክት ለሆኑ ከሁለቱም ወገን ያሉ ብፁዐን አባቶች የሚያስተምሩት ብቻ ሳይሆን ዘወትር እንዲኖሩት የሚጠበቅ ክርስቲያናዊ ሕይወት›› መኾኑን መክሮ ነበር፡፡ መምከር ብቻ ሳይሆን÷ ቤተ ክርስቲያን ለኻያ ዓመታት ያሳለፈቻቸው አሳዘኝ ኹኔታዎች እንዳይቀጥሉ ዛሬ ላይ መደረግ የሚገባው ሁሉ መደረግ ይኖርበታል ብሎ እንደሚያምን፣ ለዚህም እንደሚሠራ አቋሙን አስታውቆ ነበር፡፡
ዛሬ፣ ታኅሣሥ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ከመንበረ ፓትርያሪኩ የተሰማው ዜና ግን ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉዳይ ማድረግ ከሚችለው አስተዋፅኦ አንጻር በውጭም በውስጥም፣ በቅርብም በሩቅም ተስፋ ለሚያደርጉት ወገኖች ሁሉ አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ የማኅበሩ ጥቂት አመራሮች በወሰኑት ውሳኔ ማኅበሩ ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› ሲለው የነበረው መፈክር ‹‹ቅድሚያ ለምርጫው›› ወደሚለው ተለውጧል!!
የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ አባል የኾነውና በነሐሴው የማኅበሩ 10 ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአወዛጋቢ አኳኋን የተመረጠው አቶ ባያብል ሙላቴ የአስመራጭ ኮሚቴው አባልነቱን የተቀበለ ሲኾን ዛሬ በተሰማው የማኅበሩ የአቋም ለውጥ ደግሞ የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱን እንድትከታተል የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሪት ዳግማዊት ኀይሌ መመደቧ ተነግሯል፡፡ አቶ ባያብል ሙላቴ ከሲኖዶሱ በተመደቡ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳት አማካይነት ተቋቁሞ ያለበቂ ትችትና ውይይት በቀጥታ በጸደቀው 13 አባላት ባሉት አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ አንዱ አባል መኾ ናቸው ቢታወቅም ማኅበሩን ይወክላሉ በሚል የተመረጡበት መንገድ ግን ለብዙዎች ግልጽ አይደለም፡፡
የምክትል ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ዳግማዊት የዛሬው ምደባ የአቶ ባያብል በአስመራጭ ኮሚቴ መካተት በማኅበሩ ላይ የፈጠረው አጣብቂኝ አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚችል የሚስማሙ ተቺዎች÷ ከመንግሥት ከፍተኛ አካላት ጋራ በዕርቀ ሰላሙና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ መርቆሬዎስ አመላለስ መካከል ስለመለየት እንዲሁም ስለ ተተኪ ፓትርያሪክ ምርጫ በተደጋጋሚ የተደረገው ውይይት ቀጥተኛ ጫና ሳያሳድር እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡ ዕርቀ ሰላሙ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ ቀኖናዊ ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት፣ ተቀባይነት የሌላቸውን ቅደመ ኹኔታዎች በማስወገድ መፈጸም እንደሚገባው የሚገልጸው ማኅበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበር ይመለሱ የሚለውን በመቃወም የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ መፈጸም ይኖርበታል ብሎ እንደሚያምን ተመልክቷል፡፡
ይኸው የማኅበሩ አቋም በተለይም የማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ የኾኑት ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን የሰላም ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ ወዲህ ተግዳሮት እንደገጠመው ይነገራል፡፡ ዲ/ን ዓባይነህ በማኅበሩ ያላቸውን ሓላፊነት ጠቅሰው ሲያበቁ÷ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበር መመለስ የተጣሰው ቀኖና የሚቃናበት አንድ አማራጭ መኾኑን ማስቀመጣቸው፣ ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ በማለት አሰምቶ የሚጮኸው በአራቱም ማእዝናት የሚገኝ ምእመን ድምፅ ሊደመጥ እንደሚገባው ማሳሰባቸው፤ ከማንም ተጽዕኖ ይመጣል ብሎ ሳይፈራ በመግባባት፣ መወያየት፣ መንቀሳቀስና መነጋገር እንደሚያስፈልገው መጠቆማቸው፤ የሁለቱ ወገኖች የሰላም ልኡካን አብረው መጸለያቸውና መቀደሳቸው ‹‹ታላቅ ርምጃ›› መኾኑን መናገራቸው የማኅበሩን የቀደመ አቋም የለወጡትን ጥቂት አመራሮች አለማስደሰቱ ተገልጧል፡፡
ይህን በተመለከተ የማኅበሩ አራት አመራሮች በትላንትናው ዕለት ምሽት ዲ/ን ዓባይነህን ያነጋገሩ ሲኾን በዛሬው ዕለት ማምሻውን ደግሞ ዲ/ን ዓባይነህ ለቪ.ኦ.ኤ የሰጡት ቃለ ምልልስ ማኅበሩን እንደማይወክልና የግላቸው መኾኑን በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡ ዲ/ን ዓባይነህ በሬዲዮው ቃለ ምልልሳቸው የሰጡት አስተያየት የማኅበሩ አመራሮች ከመንግሥት ከፍተኛ አካላት ባደረጉት ውይይት ካስቀመጡት አቋምና በየጊዜው ለሊቃነ ጳጳሳቱ ከሚሰጡት ማብራሪያ ጋራ ‹‹የተጋጨ ነው፤ አባቶችን የሚከፋፍል ነው›› መባሉ የማኅበሩን ጥቂት አመራሮች ዛሬ የተሰማውን ዐይነት ግልጽ ነገር ግን በታሪክ አሳዛኝ የኾነ አካሄድ ውስጥ እንዲገቡ እንዳስገደዳቸው ተተችቷል፡፡ ወዲያውም ደግሞ ‹‹ርምጃ ወስደን እናሳውቃችኋለን›› ላሏቸው እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ላሉት ሊቃነ ጳጳሳት የተግባር ምላሽ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
ወ/ሪት ዳግማዊት በተመደበችበት ሓላፊነት ‹‹የፓትርያሪክ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ›› በሚል ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለተመደቡት አቶ ትእዛዙ ደሳለኝ መረጃዎች በመስጠትና ከአባቶች ጋራ በማቀራረብ እንደምትረዳ ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን የማኅበሩ ጽ/ቤት ሓላፊዎች የማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት ልዩ ልዩ ክፍሎች÷ ማኅበሩ በምርጫው ላይ በማተኮር ለሚሠራው ሥራ እንዲዘጋጁ መመሪያና ማሳሰቢያ ሲሰጡ መዋላቸው ተዘግቧል፡፡
ይኹንና ውሳኔው የማኅበሩ ከፍተኛ አመራር ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጠውና በትኩረት እንዲሠራበት በሙሉ ድምፅ ሊባል በሚችል መልኩ ያሳለፈውን መመሪያ የሚፃረር መኾኑን የገለጹ ወገኖች በአቋም ለውጡ ‹‹ራሱንና ለረጅም ጊዜ በጋራ ሲሠራበት የነበረውን የአባላቱን አቋም ተፃሯል›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ የቀድሞው የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም÷ ዕርቅ ሳይፈጸም ምንም ዐይነት እንቀስቃሴ እንዳይደረግ አበው መነኰሳቱ ለአባቶች እንዲመክሩና ኹኔታውንም በጸሎት እንዲያስቡ የተማፀኑት በትላንትናው ዕለት ምሽት አምስት ብፁዓን አባቶች በተገኙበት በተዘጋውና ለስድስት ቀናት የቆየው 70 የገዳማት አበምኔቶች ከ61 ገዳማት በተገኙበት ዐውደ ጉባኤ እንደነበር ተወስቷል፡፡
የማኅበሩ የሰሜን አሜሪካ ማእከል ሰብሳቢ የኾኑት ቀሲስ በላቸው ወርቁ ከዋናው ጽ/ቤት ሓላፊዎች ጋራ በስልክ አድርገውታል በተባለ ውይይት÷ ‹‹የተወሰነው ውሳኔ ፈጽሞ አያስማማንም፤ እኛ የምናስቀድመው ዕርቀ ሰላሙን ነው፤ ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን በምሰጠው አገልግሎት ከዚህ የማኅበሩ አቋም እለያለኹ›› በሚል ተቃውሟቸውን መግለጻቸው ተገልጧል፡፡
ለሁለት ዐሥርት ዓመታት መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎት በመፈጸም የትውልድ ግዴታውን እየተወጣ የሚገኘውን የማኅበረ ቅዱሳንን ክፉ መስማትም ማየትም አንሻም፡፡ ነገር ግን÷ ከቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም የሚቀድም ነገር ደግሞ የለም፡፡ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እስከቆመ ድረስ ሁሉም ከጎኑ ይቆማል፤ አሰላለፉ፣ ስልቱ ይህን ሲቃረን ደግሞ ብቻውን ይቀራል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት እንደሚያረጋግጥ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አገልጋዮችና ምእመናን ታምኖበት እየተደከመበት የሚገኘው ‹‹የዕርቀ ሰላም ይቅደም›› ጥያቄ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊሸጋገር ባለበት ዋዜማ ማኅበሩ የወሰደው አቋም ክፉኛ ያሳስበናል፡፡ ማኅበሩ በርግጥም ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ድምፁን ከፍ አድርጎ ለማሰማት ከተዘጋጀው ምእመን ጋራ ለመሰለፍ የተዘጋጁ ብዙኀን አመራሩና አባላቱ ማኅበር ከኾነ ጊዜው ከማለፉ በፊት የዛሬውን አቋሙን ያጢን፣ ይመርምር እንላለን!

No comments:

Post a Comment