የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት መተማ ወረዳ አለንጌ በተባለ ቦታ ጥቃት ፈፀመ
ታህሳስ ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ታህሳስ 18 ቀን 2005.ዓ.ም በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ አለንጌ በተባለው አካባቢ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በተካሄደው ውጊያ 8 የጠላት ወታደሮችን ገድሎ 11 በማቁሰል ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ኪሳራ ማድረሱን ግንባሩ ገልጿል።
ግንባሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን መማረኩንም ገልጿል።
መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው መልስ የለም። ዜናውንም ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልተቻለም።
የባለራእይ ወጣቶች ማህበር አባላት ጉባኤ እንዳናካሂድ ተከለከልን አሉ
ታህሳስ ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት ብርሀኑ ተግባረእድ እና ምክትል ሊቀመንበሩ ወጣት ሚካኤል አለማየሁ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ጉባኤያቸውን ለማዘጋጀት አዳራሽ ፍለጋ ቢንከራተቱም የጸጥታ ሀይሎች በሚያደርሱባቸው ተጽእኖ ለመከራየት አልቻሉም።
ወጣቶቹ በመጪው እሁድ ጉባኤ ለማካሄድ የተከራዩትን አዳራሽ፣ የጸጥታ ሀይሎች ባሳረፉት ጫና ሆቴሉ ፈቃደኝነቱን እንደሰረዘባቸው ገልጸዋል።
ሀሳባችንን በነጻነት መግለጽ አልቻልንም የሚሉት ወጣቶቹ፣ ለማን አቤት እንደሚባልም ግራ እንደገባቸው ገልጸዋል
ከወጣቶቹ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለምልልስ በትኩረት ዝግጅታችን መከታተል ትችላለችሁ።
No comments:
Post a Comment