FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, December 31, 2012

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰሙ


ታህሳስ  ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ተማሪዎቹ ባለፈው አርብ ምሽት በጀመሩት ተቃውሞ የመማሪያ ክፍሎች መስኮቶች መሰባበራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
አርብ ምሽትና ቅዳሜ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዩኒቨርስቲውን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን ገሚሶቹ በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ተጠልለው እንደነበር ታውቋል።
ተማሪዎቹ ተቃውሞአቸውን ያሰሙት አዲሱን የውጤት አሰጣጥ ፖሊሲ በመቃወም እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስላልተሟሉላቸው ነው። በግቢው ውስጥ 2 ሺ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የውሀና የመጸዳጃ እጥረት አለ። አብዛኞቹ ተማሪዎች የሀይላንድ ውሀ እየገዙ እንደሚጠቀሙና በየጫካው ለመጸዳዳት እንደተገደዱ ታውቋል።
ዩኒቨርስቲው አንድ ቤተመጽሀፍት ብቻ ያለው ሲሆን፣ በቂ መጽሀፎችም እንደሌሉት ተማሪዎች ይናገራሉ። 95 በመቶና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ብቻ “ኤ” እንዲያገኙ የሚያስገድደው አዲሱ መመሪያ ተማሪዎችን አስቆጥቶ ወደ አደባባይ እንዳስወጣቸው ታውቋል።
ከ300 በላይ ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ አንማርም በማለት ዩኒቨርስቲውን ጥለው ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በትናንትናው እለት ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት በተገባላቸው ቃል መሰረት ወደ ግቢያቸው መመለሳቸው ታውቋል። ይሁን እንጅ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ትምህርት አለመጀመራቸው ታውቋል።
ከሳምንት በፊት አዲሱን የውጤት አሰጣጥ መመሪያ በመቃወም  የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ለማሰማት ውስጥ ለውስጥ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ መንግስት መመሪያውን ተግባራዊ እንዳማያደርገው ቃል በመግባቱ እንቅስቃሴው ሊቆም እንደቻለ ታውቋል።
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ በቦረና ዞን እንደሚገኝ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment