FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, December 25, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ዲ/ን ዓባይነህ ካሴን ከሓላፊነት አነሣ



  • ውሳኔው ጥቂት አመራሮች ለጳጳሳቱና ለመንግሥት የገቡትን ቃል ያረጋገጡበት ነው
    • የዕርቀ ሰላም ደጋፊ አባቶችና አገልጋዮች በከፍተኛ የደኅንነት ወከባ ውስጥ ናቸው
    • ወከባው ወደ አገር የሚመለሱቱን የዕርቀ ሰላም ልኡካንንም ይመለከታል ተብሏል
    • ‹‹ደኅንነቱ›› በመባል የሚታወቁት አቡነ ቀሌምንጦስ ዋነኛ ጠቋሚና አስጠቂ ኾነዋል
    • ‹‹ደኅንነቱ›› ጳጳስ የማኅበሩ አመራሮች ሚናቸውን እንዲለዩ አስጠንቅቀዋል
    • ጦማሪዎች ለእውነትና ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለርካሽ ወገንተኝነት ሊሠሩ አይገባቸውም !!
‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚለውን የማኅበረ ቅዱሳን መፈክር ‹‹ቅድሚያ ለምርጫው›› ወደ ማለት የቀየሩት ጥቂት የማኅበሩ ሽንፍ እና ግዝ አመራሮች÷ ከዕርቀ ሰላሙ በፊት ፍቅርና አንድነት እንዲቀድም፣ የምእመናኑም ድምፅ እንዲደመጥ ጥሪ ያስተላለፈው የማኅበሩ አንጋፋ አመራርና አባል ዲ/ን ኢንጂነር ዓባይነህ ካሴ ከሓላፊነቱ ተነሥቶ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ወሰነ፡፡
የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ለሐራ ዘተዋሕዶ እንደገለጹት÷ የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ውሳኔውን ያሳለፈው ትላንት፣ ታኅሣሥ 14 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት በተጀመረና እስከ እኵለ ሌሊት በዘለቀ ስብሰባ ነው፡፡ የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ የነበረው ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት፣በዳላስ ቴክሳስ በተካሄደው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ስለወጣው የጋራ መግለጫ እና ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰላም ኹኔታአስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ ለውሳኔው መሠረት ናቸው የተባሉ ክሦችም ‹‹በማኅበሩ ያለህን ሓላፊነት አላግባብ ተጠቅመኻል››፣ ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ ብለኻል››፣ ‹‹ቀኖና ተጥሷል ብለኻል››፣ ‹‹በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብ ያለው ሕዝብ እንዲነሣሣ ቀስቅሰኻል›› የሚሉትና የመሳሰሉት እንደነበሩ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ
ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ
የዲ/ን ዓባይነህን የሬዲዮ ቃለ ምልልስ በአመዛኙ ከዐውዳቸው ውጭ የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት ክሣቸውን ያጠናቀሩት ጥቂት ሽንፍ እና ግዝ የማኅበሩ አመራሮች÷ ዲ/ን ዓባይነህ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡና ከማኅበሩ አባልነትም እንዲታገዱ ወይም እንዲወገዱ መሟገታቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ የጥቂት ሽንፍና ግዝ አመራሮች ሙግት ማኅበሩ በስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ለመሳተፍና ቅድሚያ ሰጥቶ ለመሥራት የደረሰበትን ውሳኔ በሚቃወሙና በግብታዊ የአቋም ለውጡ ላይ ማብራሪያ በሚጠይቁ የአመራር አባላቱ ጠንካራ ተግዳሮት እንደገጠመው ተነግሯል፡፡
ውሳኔው ዲ/ን ዓባይነህ በሚያገለግሉበት በኤዲቶሪያል ቦርድ ጽ/ቤትም ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው ሲኾን ውሳኔውን ሊደግፍ የሚችል ምንም ዐይነት መነሻ ከጽ/ቤቱ አለመቅረቡም ተገልጧል፡፡ ይህም የችግሩ ዋነኛ መነሻ በኾነውና ማኅበሩ ራሱን – የአብዛኛውን አመራሩንና መላው አባላቱን አቋም – በመፃረር ከዕርቀ ሰላሙ ይልቅ በምርጫው ላይ አተኩሮ ለመሥራት ያሳለፈው ውሳኔ÷ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ ከመቆም አንጻር በማኅበሩ አመራር ውስጥ ወሳኝ ልዩነት ለመፍጠሩ ጉልሕ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
በጥቂት ሽንፍና ግዝ የማኅበሩ አመራሮች በተገፋው በዚህ ውሳኔ ‹‹ርምጃ ወስደን ውጤቱን እናሳውቃችኋለን››የሚል ቃል የተገባላቸው ለፓትርያሪክ ምርጫ የተደራጁ ሊቃነ ጳጳሳትና ሂደቱን በቅርበት የሚከታተለው የመንግሥት አካል ይደሰቱ ይኾናል፡፡ የውሳኔው መንፈስ ግን
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የማኅበሩ ትጉሃን አባላትና አጋር አካላት ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን በመሠዋት ለዕርቀ ሰላሙ ሥምረት የደከሙትን ድካም በማኅበሩ ህልውና ስም በሚነግዱ ጥቂት የማኅበሩ ሽንፍና ግዝ አመራሮች ዘንድ ሚዛን እንደማይሰጠው የተረጋገጠበት ነውና ከፍተኛ ቁጣ ሊቀሰቅስ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ ዲ/ን ዓባይነህ የኤዲቶሪያል ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ኾነው የተመረጡት ማኅበረ ቅዱሳን ፲ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነው፡፡ከትላንቱ የሥራ አመራር ጉባኤው ስብሰባ በፊት የማኅበሩ ሥራ አመራር ጽ/ቤት አባላት ባለፈው ሳምንት ዐርብ ምሽት ዲ/ን ዓባይነህን እንዳነጋገሯቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በንግግሩም ‹‹በማኅበሩ ያለህን ሓላፊነት አላግባብ ተጠቅመኻል›› ለሚለው ክሥ ዲ/ን ዓባይነህ÷ ከማኅበሩ አሠራር አንጻር ይቅርታ ሊጠይቁበት እንደሚችሉ ነገር ግን በማኅበሩ ያላቸውን ሓላፊነት እየጠቀሱ በተለያዩ ሚዲያዎች ጽሑፎችን የሚያበረክቱና ቃለ ምልልሶችን የሚሰጡ የማኅበሩ ሓላፊዎች በዝምታ የታለፉበትን ኹኔታ በመጥቀስ፣ በእርሳቸው ላይ ይህ ክሥ መጠናቀሩ ከቅንነት የመነጨ ስለመኾኑ አጠያያቂ እንደሚያደርገው አሳስበዋል፡፡
የተጣሰው ቀኖና እንዲታረም፣ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ ዲ/ን ዓባይነህ እንደ አንድ አማራጭ ያቀረቡት ‹‹የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበር መመለስ›› ለቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ የተነሣሣውን የተደራጀ የጳጳሳት ቡድን ይኹን ጉዳዩን የሚከታተለውን የመንግሥት አካል አላስደሰተም ተብሏል፡፡ ይኸውም ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበር ይመለሱ›› በሚለውና ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይፈጸም›› በሚለው መካከል ልዩነት የሚያደርገው የማኅበሩ አቋም÷ ‹‹ዕርቀ ሰላሙን እንጂ አራተኛው ፓትርያሪክ ወደ መንበር ይመለሱ የሚለውን አልደገፍም›› በማለት ለጳጳሳቱ እና ለመንግሥት አካል ሲሰጥ የቆየው ገለጻ የማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ ምክትል ሓላፊ ከሰጡት አስተያየት ጋራ ተጋጭቷል በሚል ነው፡፡ የማኅበሩ አቋምና የኤዲቶሪያል ቦርዱ ምክትል ሓላፊ ዲ/ን ዓባይነህ አስተያየት መጋጨት በተደራጁት ጳጳሳትና በመንግሥት ዘንድ ማኅበሩ ‹‹እንዳመቺነቱ የሚያንጸባርቀው የተደበቀ እና የአደባባይ አቋም›› እንዳለው፣ ይህም በ‹‹አታላይነት፣ ከፋፋይነት›› እንዳስቆጠረው ተገልጧል፡፡
ዲ/ን ዓባይነህ በአስተያየታቸው÷ ‹‹ሁለታችንም አጥፍተናል፤ ቀኖናውን የጣስነው በጋራ ነው›› በሚል ከተሰራጩት መረጃዎችበመነሣት የቀኖና ጥሰትና ጥፋት በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ካለ ‹‹ሁለቱም በጋራ ለሠበሩት ቀኖና የጋራ ሓላፊነት ወስደው በጋራ መጠገን እንደሚችሉ›› ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቀኖና ተጥሷል ብለኻል›› በሚለው ጥቂት የማኅበሩ አመራሮች ሪፖርት መሠረት ግን÷ በአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ከዕርቀ ሰላሙ በፊት ለቀጣይ ፓትርያሪክ ምርጫ የሚተጉት የተደራጁ ጳጳሳት፣ ‹‹ቀኖና ተጥሷል ከተባለ የእኛ ሢመት (ጵጵስና) ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ ዋጋ (ተቀባይነት) አይኖረውም›› በሚል የተነገራቸውን ክሥ አጉልተው አቅርበዋል፡፡ ከዚህም በመነሣት ‹‹ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ይሰጥ›› እያለ የሚጠይቀው ሕዝብ ድምፅ እንዲደመጥ፣ ሕዝቡም ከማንም ተጽዕኖ ይመጣል ብሎ ሳይሰጋ እንቅስቃሴውን በመግባባት፣ በመነጋገር እንዲያጠናክር በዲ/ን ዓባይነህ ጥሪ መተላለፉ ‹‹ለዐመፅ እንደማነሣሣት ተቆጥሯል፡፡››
በማኅበሩ ጥቂት አመራሮች የተገፋው የሥራ አመራር ጉባኤው ውሳኔ መነሻ ከኾኑት ጳጳሳት መካከል የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምንጦስ አንዱ ሲኾኑ የአስመራጭ ጉባኤው አባልም ናቸው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በኾኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ‹‹ደኅንነቱ›› በሚል የሚታወቁት አቡነ ቀሌምንጦስ ከኢሕአዴግ አራት ድርጅቶች አንዱ የኾነው ብአዴን አባል እንደኾኑና ከድርጅቱም ከፍተኛ ካድሬዎች መመሪያ እንደሚቀበሉ ይነገርባቸዋል፡፡
አቡነ ቀሌምንጦስ ከአቡነ ጎርጎሬዎስ እና አቡነ ሳዊሮስ ጋራ በመተባበር ‹‹ከምርጫው ይልቅ ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› በሚል የሚታወቁትን ብፁዓን አባቶችና አገልጋዮች በመጠቆምና በማስጠቆም በከፍተኛ የደኅንነት ጫና ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በፓትርያሪክ ምርጫውና በዕርቀ ሰላሙ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ በተዘገበበት ወቅት የማኅበሩን ሁለት አመራሮች አስጠርተው ‹‹አንዴ ምርጫ አንዴ ዕርቅ አትበሉ፤ አቋማችኹን ለዩ›› በማለት እንዳሳሰቧቸውም ተነግሯል፡፡ ‹‹ስሜን በብሎግ ልታጠፉ ተዘጋጅታችኋል›› በማለትም እንዳስጠነቀቋቸው ተገልጧል፡፡ ‹‹አባቶቻችን በሚያሰጋ ኹኔታ ተከፋፍለዋል፤ ልናግዛቸው ይገባል፤ ምርጫውን ደግፈን ይበጃል የምንለውን ሐሳብ እንሰጣለን›› በሚል ገለጻ የታጀበው የማኅበሩ ግብታዊ የአቋም ለውጥ የተሰማውም ከዚህ የአቡነ ቀሌምንጦስና መሰሎቻቸው ዛቻና ማስፈራሪያ በኋላ ነው ይላሉ የማኅበሩ ምንጮች፡፡
አቡነ ቀሌምንጦስ በዚህ ሳያበቁ የዕርቀ ሰላም ልኡኩን በመወከል በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ መግለጫ የሰጡትን ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስንም ማጣጣላቸውና በብፁዕነታቸውም ‹‹ቆይ÷ እዚያ ኾነው እንደሚደነፉት መስሏቸዋል›› በሚል መዛታቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚህ በመነሣት ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ሰዓት ከአሜሪካ ወደ አገር ቤት በመልስ ጉዞ ላይ ስለመኾናቸው የተነገረው የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ አዲስ አበባ እንደደረሱ ከመንግሥት አካላት ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሊገጥማቸው እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ አቡነ ቀሌምንጦስና የእርሳቸው መሰል አሰላለፍ የያዙ ጳጳሳት ያሻቸውን ቢሉም በአቋማቸው በጸኑት ብፁዓን አባቶች ዘንድ በከፍተኛ የመንፈስ ጽናት የተያዘው ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ የመስጠት ዝንባሌ አለመለወጡን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
መርገፍ፡- የማለዳ ያህል በሚቆጠረው የጡመራ ልምዳችን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ለእውነትና ለቤተ ክርስቲያን ሲሉ ብቻ መጦመር ምን ያህል ድካምና መሥዋዕትነት እንደሚጠይቅ በተጨባጭ እንረዳለን፡፡ ተቋሙ መንፈሳዊነት የራቀው፣ ያረጀና ያፈጀ አሠራር የተጠናወተው ከእኒህም የሚወለደው ሙስና እና ጎጠኝነት የተንሰራፋበት መኾኑ በመሠረታዊ ምክንያትነት ቢጠቀስም የዘርፈ ብዙ ሀብት ምንጭ የኾነው አገልጋዩና ምእመኑ ባይተዋርነት ግን ቀዳሚ ሓላፊነቱን ይወስዳል ብለን እናምናለን፡፡
ከባይተዋርነቱ በላይ የሚያመው ግን ለእውነት አለመተባበር በፈንታውም ‹‹እገሌ ደጋፊው ብዙ ነው፤›› በሚል ብቻ ስሕተቱ ከተራራ ገዝፎ የሚታየውን አካል ከትችት ነጻ ለማድረግ የሚፈጸመው የማሞላቀቅ አያያዝ ነው፡፡ ይኸው አያያዝ ከመንገደኛው ሰው የተለየ መረጃና ዕውቀት ይዞ የማሳወቅን፣ የማጋለጥን፣ የማሳመንና የማስተማርን ሥራ መሥራት በሚገባቸው ሚዲያዎች ላይ ሲታይ ደግሞ ሕመሙ ይጸናል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑን ዕውቀትና ክህሎት የያዘው ትውልድ ቤተ ክርስቲያኑን በዕውቀቱ፣ በገንዘቡና በሞያው ለማገልገል ያስችለው ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ዕውቅና የተሰጠው ማኅበር መኾኑን ሐራውያንእናውቃለን፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋት ዓምድና መሠረት የኾኑ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ የአገልግሎት ፍሬዎች ማበርከቱንና በማበርከት ላይ መኾኑንም ምናልባትም ለማኅበሩ እንቆረቆራለን ከሚሉት በተሻለ ሐራውያን በቅርበት እንገነዘባለን፡፡
ግና÷ ማኅበሩ ከተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ፣ ከሚሸፍነው የአገልግሎት አድማስ እና ከሚያቅፋቸው አባላቱ ሞያዊ ስብጥርና አቅም አኳያ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ ችግር በመሠረታዊነት ለመለወጥ በቂ ሥራ እንዳልሠራ – ከሌላ ከማንም ሳይኾን ከገዛ አመራሮቹና አባላቱ – የሚነሣው ምሬት ደግሞ ይሰማናል፤ በቂ ሥራ አለመሥራት ብቻ ሳይኾን ቀደም ሲል በተሠሩ ሥራዎች ማኅበሩ ያዘመራቸውን የአገልግሎት ፍሬዎች (ውጤቶች) ወደኋላ የሚመለሱ የማኅበሩ የውስጥ ድክመቶችም እንዳሉ ስንገነዘብ ደግሞ ዕረፍት የሚሰጠን አይኾንም – በተለይም በከፍተኛ አመራሩ የሚፈጸሙ ስሕተቶች፡፡
በ2003 ዓ.ም መጋቢት ወር በተላለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ ቃለ ጉባኤ መሠረት በመካሄድ ላይ የሚገኘው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ÷ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚጠበቅበት፣ የሰላም ወዳዱ ሕዝበ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት ነው፤›› ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ በኅትመቶቹ ርእሰ አንቀጾች፣ መልእክቶችና ትምህርቶች ሲያስታውቅ፣ ሲያስገነዝብ ቀጥተኛ የተግባር እንቅስቃሴ ሲያደርግም መቆየቱን እናውቃለን፡፡
ባለፈው ሳምንት ዐርብ ዕለት ከቀትር በኋላ እንዳረጋገጥነው ግን ሽንፍ እና ግዝ (conformist and subservient) ብለን በምንጠራቸው ጥቂት የማኅበሩ አመራር አባላት ግፊትና ውሳኔ ማኅበሩ ከቀደመ አቋሙና ውሳኔው ጋራ በሚጋጭ አኳኋን ቅድሚያ ለምርጫው ሰጥቶ እንደሚሠራ መግለጹ ታውቋል፡፡ ሰላምን በምትሰጠው የሰላም ባለቤት በኾነችው ቤተ ክርስቲያን ‹‹ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ›› በሚል ከተመደቡ የመንግሥት ሹም ጋራም የምትሠራ የማኅበሩ አመራርም መመደቧ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡
ይህም ብቻ ሳይኾን በዕርቀ ሰላሙ ዙሪያ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት የሞከሩ ዘጋቢዎችም ምን ያህል እንዲሸማቀቁ እንደተደረጉ ሰምተናል፤ ‹‹ታሪካዊ ስሕተት መሥራት የለብንም፤ ቤተ ክርስቲያን መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት፤ እንድረስላት፤ አመራሩ ይህን በአግባቡ አልተረዳውም፤ ለሕዝቡ የኾነ ነገር ማለት አለብን፤›› ያሉ የአመራር አባላት የሚያዳምጣቸው አለመኖሩ ያሳዝናል፡፡ ከዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ በፊት ሂደቱን የሚያሰናክል ምንም ነገር እንዳይደረግ ገዳማውያን አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን እንዲያሳስቡና ገዳማውያኑም ስለዚህ ጉዳይ እንዲያዝኑና እንዲጸልዩ ማሳሰቢያ በተሰጠበት ማግሥት የአቋም ለውጡ መታየቱ የጤና ነው ወይ አያሰኝምን?
ሐቁና የሐራውያን ዘገባ መንፈስ ይኸው ነው፡፡ በቀረበው መረጃ ርግጠኝነት ላይ ማንም ጥርጣሬ ሊገባው አያስፈልግም፡፡ የዘገባው ዓላማ ግብ ማኅበሩ ከጊዜው በፊት ታሪካዊ ስሕተት እንዳይፈጽም ማንቃት፣ ጉዳዩ ከአባሉም ባሻገር የሰፊው አገልጋይና ምእመንም በመኾኑ ለአደባባይ ፈተና (public scrutiny) እንዲጋለጥ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በማኅበሩ ግብታዊ የአቋም ለውጥ የተደናገጠውና ግራ የተጋባው አባል የአመራሩን አቋም እንዲጠይቅና አመራሩ ከስሕተቱ በጊዜው እንዲታረም ከማበረታታት ይልቅ ለማኅበር በማሰብ ስም የሚካሄድብን ስም ማጥፋትና የእነማን ይኾኑ አሠሣ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡
ታሪካዊ አቋም በወሰድንበት ዐቢይ አጀንዳ የተፈጠረን ልዩነት አንድ የሚያደርግ አዲስ/የረባ መረጃ ሳይዙ የሰነበተ/የተቃረመ ዜና እየደጋገሙ ርካሽ ወገንተኝነትን ለማሳየት መሞከርም ትርፉ ትዝብት ነው፡፡ ‹‹እንደወረደ የመዘገቡ›› እና ‹‹የልምድ ማነሱ››፣ ‹‹የእናሳስባለን››፣ ‹‹ግለሰብን ማእከል ያደረገ›› ገለመኔ ‹‹የጨቡ አራድነት›› /geezonlineእንዳለው/ እንኳ ይቆየን፤

No comments:

Post a Comment