አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አልዋሉም
በታምሩ ጽጌ
የተሰጣቸውን ሥልጣን ያላግባብ በመጠቀምና በመመሳጠር ለመንግሥት ገቢ መሆን የሚገባውን ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል በተጠረጠሩ ስድስት የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምርያ ኃላፊዎች ላይ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ መመሥረቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት በቦሌ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምርያ ዋና ገንዘብ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዘውድነሽ ተሰማ፣ የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለ ሥላሴ ጌታቸው፣ የበጀትና የገቢዎች ሒሳብ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ፍፁም ብርሃን ምትኩ፣ የሒሳብ ክፍል ኅላፊ ገነት በቀለ፣ ገንዘብ ተረካቢና ሰብሳቢ ወ/ት ይዘሽዋል ካሳና የሒሳብና በጀት ሠራተኛ አቶ ሽመልስ ጓዋለ አበበ ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን ሥልጣን በግልጽ ያላግባብ በመገልገል፣ ከተሰጣቸው ሥልጣን በላይ አልፈው በመሥራትና እርስ በርስ በመመሳጠር፣ የማይገባ ጥቅም በግላቸውና በጋራ ለማግኘት አስበው ድርጊቱን መፈጸማቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር ማስረዳቱ ታውቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ እንዳብራራው፣ ተጠርጣሪዎቹ ከሕግና መመርያ ውጪ ዋና ገንዘብ ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ዘውድነሽ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የትራንዚት ክፍያ እንዲሰበስቡ ከአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊው የተሰጣቸውን ውክልና ተጠቅመው 200,100 ዶላር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዋ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትራንዚት የተሰበሰበ 468,600 ዶላር ከወ/ሮ ፈለቀች ጌታሁን ከሚባሉ የአየር መንገዱ ሠራተኛ መቀበላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ መስጠተቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ወ/ሮ ዘውድነሽ ዶላሩን መቀበላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ከሰጡ በኋላ፣ 268,600 ዶላር ብቻ እንደተቀበሉ በማስመሰልና በቀሪ ሰነድ ላይ በማስፈር፣ በተለያዩ ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጋቸውን በክሱ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ማለትም እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 25 ቀን 2006 ከኢትዮጵያ አየር መንገድ 327,100 ዶላር ከሰበሰቡ በኋላ፣ 327 ሺሕ ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ በማድረግ፣ 100 የአሜሪካ ዶላር ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውም በክሱ ተካቷል፡፡ ግለሰቧ በድምሩ 200,100 ዶላር ወይም በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ 1,738,510 ብር ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ሲገባቸው ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምርያ የአስተዳደርና የፋይናንስ ኃላፊው አቶ ኃይለ ሥላሴ ጌታቸው፣ መምርያው የሚፈጽማቸውን ልዩ ልዩ ገቢዎችና ክፍያዎች በወጡ ደንቦችና መመርያዎች መሠረት አለማከናወናቸውን ክሱ ያመለክታል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪና የመንግሥት ገንዘብ በባንክ በኩል እንዲሰበሰብ ማድረግ ሲገባቸው፣ ከፋይናንስ አሠራርና ደንብ ውጪ አንደኛ ተከሳሽ ገንዘቡን እንዲሰበስቡ ውክልና መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡
ሁሉም ተከሳሾች እንደኃላፊነታቸው የተሰጣቸውን ሥልጣን በአግባቡ መጠቀም ሲገባቸው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የፋይናንስ ደንብ ቁጥር 17/1997 አንቀጽ 35 እና 36 ተራ ቁጥር 2 እና በመንግሥት ገንዘብ አያያዝ አዋጅ አንቀጽ 32 መሠረት ገቢ ማድረግ ሲገባቸው፣ እርስ በርስ በመመሳጠር ለግል ጥቅማቸው በማዋልና መንግሥት 1,738,510 ብር ገቢ እንዲያጣ በማድረጋቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ወ/ሮ ዘውድነሽ ተሰማ፣ ገነት በቀለ፣ ወ/ት ይዘሽዋል ካሳና አቶ ሽመልስ ጓዋላ በአድራሻቸው ሊገኙ ባለመቻላቸው በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸው ታውቋል፡፡ በመምርያው የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊው አቶ ኃይለ ሥላሴ ጌታቸውና የበጀትና የገቢዎች ሒሳብ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ፍጹም ብርሃን ምትኩ ዋስትና ተከልክለው ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰጠቱ ታውቋል፡፡
www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment