FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, December 30, 2012

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ላይ ሚስጥራዊ ያሉዋቸውን ሰነዶች ይፋ አደረጉ


የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የኢሕአዴግ ዕጩ ሆነው የተወዳደሩበትን ሰነድ አቀረቡ
- የምርጫ አስፈጻሚዎች ለኢሕአዴግ የአባልነት መዋጮ የከፈሉበት ሰነድ አለን ይላሉ
- አንድ ለአምስት አደረጃጀት ለምርጫ ቅስቀሳ እየዋለ ነው በማለት ኮነኑ
በየማነ ናግሽ
መድረክንና መኢአድን ጨምሮ ዋነኛ ተቃዋሚዎች የተሰባሰቡበት 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቋቋሙት ጊዜያዊ ኮሚቴ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለፓርላማው አፈ ጉባዔ ክስ እንደመሠረቱበት ገልጸው፣ አገኘናቸው ያሉዋቸውን አንዳንድ ሚስጥራዊ ሰነዶች ይፋ አደረጉ፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ግንባር (መድረክ) ጽሕፈት ቤት የፓርቲዎቹ ጊዜያዊ ኮሚቴ ባለፈው ሐሙስ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አንዳንድ ሚስጥራዊ ያላቸውን ሾልከው የወጡ ሰነዶችን ይፋ በማድረግ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት ለቅሬታቸው ማስረጃ የላቸውም ማለቱን አስተባብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላቀረብናቸው 18 ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ ቦርዱ የገዥው ፓርቲ ወገንተኛና ጉዳይ አስፈጻሚ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፤” በሚል ርዕሰ ጊዜያዊ ኮሚቴው ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቀጣዩ ምርጫ ፍትሐዊ እንዲሆን እንነጋገርበት በሚል ለቦርዱ 18 የቅሬታ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም፣ “አንዳቸውም በማስረጃ የተደገፉ አይደለም” በሚል በተሰጣቸው ምላሽ ውድቅ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበለትን ቅሬታ ለአንድ ወር ያህል ከገመገምኩ በኋላ በሚል የሰጠው ምላሽ አሳፋሪና ነገ በሕዝብ የሚያስጠይቅ ነው ያሉ ሲሆን፣ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ሳይጠይቃቸውና ተወካዮቻቸውን ሳያነጋግር ውሳኔውን ያሳወቃቸው ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጠበት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በምርጫ ቦርድ ምላሽና በምላሽ አሰጣጡ አግባብነት የተበሳጨው የ33 ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ፣ ቦርዱን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማ አፈ ጉባዔው ላይ ክስ እንደመሠረተበት አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ማስረጃ ያላቸውን ለጋዜጠኞች ይፋ አድርጓል፡፡ “በታሪክም በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊትም የሚያስተዛዝብና የሚያስጠይቅ ነው፤” ባለበት በዚሁ መግለጫ፣ “ለመሆኑ መቼ መድረኩ ተከፍቶ ተወያይተን? ማስረጃ ለማቅረብ ተጠይቀን ማቅረብ አለመቻላችን ታየና ነው እንዲህ ሊባል የተቻለው?” በማለት በጥያቄ ለተነሳው ጉዳይ የኮሚቴው አባላት ምላሽ የሰጡት ማስረጃ ያሉትን በማቅረብ ነበር፡፡
የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ አቶ ግርማ በቀለ መግለጫውን አንብበው ከጨረሱ በኋላ፣ “ማስረጃችሁ ምንድን ነው? ምን አዲስ ነገር ይዛችኋል?” በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀድመው ምላሽ የሰጡት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ፣ “አንድም ማስረጃ የሌለው ቅሬታ አላቀረብንም፡፡ ቦርዱ ግን የኢሕአዴግ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኗል፡፡ ፈጽሞ አላነጋገረንም፤ ማስረጃ እንድናቀርብም አልጠየቀንም፤” ብለዋል፡፡
የኮሚቴው አባልና የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ ገብረማርያም በበኩላቸው፣ ለእያንዳንዱ ቅሬታ ማስረጃ መያዛቸውን ያረጋገጡት፣ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ የሺ ፈቃደ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደ ኢሕአዴግ ሆነው ሲከራከሩዋቸው ቆይተው አሁን የኢሕአዴግ አባል የሆኑበት ማስረጃ መገኘቱን በማሳወቅ ነበር፡፡
“በወይዘሮ የሺ ላይ ግላዊ ጥላቻ ኖሮን አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢሕአዴግ አባላት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑበት ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ ምርጫ ማከናወን አይችልም፤” ብለዋል፡፡ በኃላፊዋ ላይ ለምን እንዳተኮሩ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ማስረጃውን ይዘዋል የተባሉት የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ወንድማገኝ ደነቀ ንግግራቸውን የጀመሩት በእጃቸው አንድ ሰነድ ከፍ አድርገው በማመልከት ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ “የክልል ምክር ቤት አባላት የምርጫ ጣቢያ የድምፅ ቆጠራ ውጤት መተማመኛ” በሚል የምርጫ ቦርድ ዓርማ ያለበት ሰነድ የዕጩ ተወዳዳሪዋ የወይዘሮዋ የሺ ፈቃደ ስም የሚገኝበት፣ በብአዴን ፓርቲ በንብ ምልክት ያገኙት የድምፅ ብዛትና ደረጃቸው የሰፈረበትና ለአማራ ክልል ምክር ቤት የደብረ ብርሃን ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ወይዘሮ የሺ በቀረበው ማስረጃ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ “ይህ ማስረጃ ለምርጫ ቦርድ አልቀረበም፡፡ የምሠራው ለቦርዱ ነው፡፡ ቦርዱ ይህ ማስረጃ ቀርቦለት ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ብቻ ምላሽ የምሰጥበት ይሆናል፤” በማለት የቀረበው ማስረጃ እውነተኛ ነው አይደለም ሳይሉ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ሌላ የኮሚቴው አባል አቶ ለገሠ ላንቃም የሲዳማ ዓርነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ተወካይ ሲሆኑ፣ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በደቡብ ክልል የቦርባ ምርጫ ክልል ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሠሩ የቆዩት አቶ ዮሐንስ አብርሃም የተባሉ ግለሰብ፣ የደኢሕዴን (ኢሕአዴግ) አባልነት መዋጮ የከፈሉበት ሰነድ ይገኝበታል፡፡ ብዙዎቹ ምርጫ አስፈጻሚዎች የፓርቲ አባላት መሆናቸውን ማሳያ ነው በማለት ነበር ያቀረቡት፡፡ ሌሎች ማስረጃዎች እንዳሏቸው በመጠቆም ጭምር፡፡ በምርጫ 2002 የነበረው ሁኔታ ምንም አለመቀየሩንና በተመሳሳይ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ለገሠ፣ በተለይ “በወቅቱ የአርቤጎና ወረዳ ምርጫ ሥራን ለማሳካት የወጣ አጭር ማስፈጸሚያ ቼክ ሊስት” በሚለው ሰነድ፣ የክልሉ ገዥው ፓርቲ ከወረዳ ማዕከል እስከ ቀበሌ የሚሠሩ ተግባራትን ያካተተ ነው፡፡ “ለልማት የፈጠርነውን የልማት ሠራዊት ወደ ምርጫ ተግባር አንድ ለአምስት በማዟዟር” በሚል የአንድ ሳምንት አደረጃጀት እንዴት ለቅስቀሳና ለምርጫ እንደሚውል፣ የሴቶችና የወጣቶችን የቀበሌ አደረጃጀቶች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ ትምህርት ቤቶችንና የሃይማኖት ተቋማት እንዴት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል የሚያብራራ ጽሑፍም አሳይተዋል፡፡ ይኼው ሰነድ ፓርቲውን ሳያወላውል የሚመርጠውን “A” አቋሙ ተለይቶ ያልታወቀውን “B” በማለት፣ ፈጽሞ የለየለትን ተቃዋሚ ደግሞ “C” እንደሰጠ ገልጸው፣ ወደ “A” ለማምጣት ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያመለክታል ካሉ በኋላ፣ የማይመርጡትን ምን እንደሚሠሩ “በዓይነ ቁራኛ” የቅርብ ክትትል ማድረግ ይጠይቃል በማለት አስረድተዋል፡፡
ሌሎች አባላትም ባለፈው ምርጫ ቤታቸው የተቃጠለባቸውን፣ ተገደሉ ያሉዋቸውን ሰዎችና ለእስር የተዳረጉትን ስም እየጠቀሱ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይኼም እስካሁን በግልጽ እየተሠራበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“መንግሥት አንድ ፓርቲ አንድ አገር ብሎ ያውጅና ቁርጣችንን እንወቅ፤” ያሉት አቶ ገብሩ ገብረማርያም፣ “ጥያቄያችን ከ80 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ኢሕአዴጋዊያን ያልሆኑ ለምርጫ ቦርድ ይሥሩ የሚል ነው፤” በማለት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይኼንን የተበላሸ የምርጫ ሥርዓትና አምባገነንነት በመቃወም ከጐናቸው እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው አቤቱታዎችም ሆኑ ቅሬታዎች በማስረጃ ያልተደገፉና ብዙዎችም በ2002 ምርጫ ማግስት በፍርድ ቤት ሳይቀር መልስ የተሰጠባቸው ናቸው ይላል፡፡ ቦርዱ አሁንም የቀረቡለትን ቅሬታዎች በዝርዝር ካየ በኋላ ማጣራቱን ገልጾ፣ ፓርቲዎቹ አላነጋገረንም የሚሉት ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል፡፡
ቦርዱ ሁሉንም ፓርቲዎች እኩል እያገለገለ እንደሚገኝ አስረድቶ፣ የሚተዳደርባቸው ደንቦችና መመርያዎች በፓርቲዎች ተሳትፎ የወጡ በመሆናቸው ወገንተኛ አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም በማለት አስረድቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ከማንም ፓርቲ ጋር የመወገን ዓላማ እንደሌለውና ሕጉም እንደማይፈቅድለት እየተናገረ ነው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት “ምርጫ ለመድረክ ግንባርነት ዕውቅና ሰጠ” በሚል ርዕስ በወጣው ዜና “… መድረክን የፖለቲካ አጀንዳውንና የገንዘብ አቅሙን በመገምገም ብቁ ሆኖ በመገኘቱ ያቀረበው ጥያቄ በቦርዱ ተቀባይነት ማግኘቱን ወይዘሮ የሺ ገልጸዋል፤” የሚለው ዓረፍተ ነገር ከቦርዱ ሥልጣንና ኃላፊነት ውጪ በመሆኑ በዚህ መሠረት ተስተካክሎ እንዲነበብ እንጠይቃለን፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/9048-2012-12-29-11-06-05.html

No comments:

Post a Comment