FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, December 24, 2012

የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች


ኢህአዴግን በኃይል ለማስወገድ ጥሪ ቀረበ
በኢትዮጵያ ያለውን አገዛዝ ለመጣል ይቻል ዘንድ ለቀድሞው ሰራዊት፣ አሁን በስራ ላይ ላሉት የመከላከያ አባላትና በአገር ውስጥና በውጪ ስደት ላይ ላሉ ዜጎች ሁሉ የትግል ጥሪ ቀረበ። “የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” በሚል ስያሜ ጥሪውን ያስተላለፈው ክፍል ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከሚመሩት ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳለው ለማጣራት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት ኢሳት ዘወትር እሁድ በሚያቀርበው የሳምንቱ ዜናዎች ላይ አስታውቋል።
ኢሳት በሰበር ዜና ያቀረበው ይህ ዜና ከዋናው የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር ግንኙነት እንዳለውና እንደሌለው ለማጣራት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው ባይሳካለትም፣ በቅርቡ ግን መረጃዎችን በማሰባሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሚያቀርብ መረጃ ለመስጠት እንደሚተጋ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያለ ህዝብ ይሁንታ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በሃይል መንበሩን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ ከስልጣን ሊወገድ የሚችለው በትጥቅ ትግል ብቻ እንደሆነ ያመለከተው የጥሪ መልዕክት የወያኔ ትዕቢት ሊተነፍስ የሚችለው በህዝባዊ ትግል በትጥቅ ብቻ እንደሆነ አስምሮበታል።
ለቀድሞው ሰራዊት አባላት፣ አሁን በስራ ላይ ያሉ የመከላከያ አባላትና ለሁሉም ወገኖች ጥሪ ሲያቀርብ ክብሩ ያልተነካ፣ ያልተዋረደ አትዮጵያዊ እንደሌለ አመልክቷል። በኢትዮጵያ እስር፣ ግድያና ስቃይ የሚወገደው ሙሉ በሙሉ ስርዓቱ ሲወገድ ብቻ እንደሆነ አስታውቋል።
መድረክ ግንባር ሆነ
ዓረና፣ ኦፌዴን፣ ኦሕኮ፣ አንድነት፣ ኢሶዴፓና የደቡብ ኅብረት ፓርቲን አካቶ የያዘው መድረክ ግንባር ለመሆን ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ። የምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ የሺ ፈቃደ ቦርዱ የግንባርነት ዕውቅና መድረክ ላቀረበው ጥያቄ መስጠቱን ለሪፖርተር አስታውቋል።
የፖለቲካ አጀንዳውንና የገንዘብ አቅሙን በመገምገም ብቁ ሆኖ በመገኘት መድረክ ያቀረበው ጥያቄ በቦርዱ ተቀባይነት ማግኘቱን ወ/ሮ የሺ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል በመድረክ ሥር የነበሩ ፓርቲዎች ስምንት ሲሆኑ ሁለቱ ባለመስማማት በመውጣታቸው ወደ ግንባር ለመሸጋገር የወሰኑት ስድስቱ ፓርቲዎች ናቸው፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 እና መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ይሆናል በሚሉት ጉዳዮች አባል ፓርቲዎቹ የማይግባቡባቸው ቢሆኑም፣ እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን ነፃና ሰላማዊ ምርጫ በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ ያለ ልዩነት ለመሥራት ስምምነት መድረሱን ዶ/ር ነጋሶ ገልጸዋል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተፈጠረ የተለያዩባቸው ነጥቦች ሕዝብ የሚያነሳቸው ጉዳዮች በመሆናቸው፣ ወደ ሕዝብ በማውረድ ወደፊት መነጋገር ይቻላል ብለዋል፡፡ ስምምነት ከተደረሰም ግንባሩ ተዋህዶ አንድ ፓርቲ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ኖርዌይ በኤርትራ ኤምባሲዋን እንደምትዘጋ አስጠነቀቀች
የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስፔን ባዛር ኢድን ሰሞኑን ኢትዮጵያ ነበሩ። ሚኒስትሩ ከጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ከአዲሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መምከራቸውን የኢህአዴግ የዜና አውታር ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ዜናው እንዳስረዳው ኖርዌይ ኢትዮጵያን ለመርዳት መማሏን ይገልጽና በተመሳሳይ ኤርትራ ያለውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት በዝግጅት ላይ መሆኗን ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም መንገሯን ያመለክታል።
የኖርዌዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጠቅሶ ዜናው እንደዘገበው በሱማሊያ ያለው ወቅታዊ መረጋጋት ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኝና ኢትዮጵያ በአደራዳሪነት እየተከታተለች ያለውን የሁለቱን ሱዳን ጉዳይ ሀገራቸው ለመደገፍ “ቁርጠኛ” መሆኖን አስታውቋል። በመጨረሻም ኤርትራን በቀጠናው በማካሄድ ላይ ያለችውን የማተራመስ ድርጊት የማታቆም ከሆነ ሀገራቸው ኤምባሲዋን ዘግታ እንደምታወጣ ማስጠንቀቋን አመልክቷል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ኤርትራ ሄደው ኢሳያስ አፈወርቂን ለማነጋገር እንደሚፈልጉ ባስታወቁበት ማግስት የመንግስት መገናኛ ይህንን ጉዳይ ርዕሰ ዜና ማድረጉ የጠ/ሚኒስትሩ የድርድር ጥያቄ የቀልድ ለመሆኑ አመላካች ነው።
አንድነት አዲስ የህዝብ ግንኙነት ሾመ
መሰረታዊ ለውጥ ያካሂዳል የተባለው አንድነት የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ቋሚ ሰብሳቢ የነበሩትን ዶ/ር ሃይሉ አርአያን በአዲስ አመራር በመተካትና አቶ ስዬ አብርሃ አሜሪካ ያላቸውን ጉዳይ ሲጨርሱ ወደ ፓርቲው መመለስ እንደሚችሉ በመጥቀስ ሰንደቅ ጋዜጣ የፓርቲው ምንጮቼ ነገሩኝ በማለት ስዬ ከፓርቲው ሊታገዱ ይችላሉ ሲል ያሰራጨውን ዜና አስተባብሏል።የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን በመጥቀስ ሪፖርተር ይፋ ባደረገው ዜና ከፓርቲው የተነሳ አመራር የለም።
ከፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ስራ ጋር ለረዥም ጊዜ ቁርኝት የነበራቸው ዶ/ር ሃይሉ በሃኪም ምክር ምክንያት ረፍት ማድረግ ስላለባቸው በአቶ ዳንኤል ተፈራ መተካታቸውን ታውቋል።አዲሱ የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ወጣት፣ ትኩስ ሃይልና በሳል መሆናቸውን ዶ/ር ነጋሶ መስክረዋል። የድርጅቱ ምክር ቤት ይህንኑ ተቀብሎ ለአቶ ዳንኤል  ይሁንታውን ሰጥቷል። የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ መሆናቸው ይታወሳል። እስር ላይ ያሉት አቶ አንዷለም ጠንካራ አቋም ያላቸው ኢህአዴግ አብዝቶ ከሚፈራቸው መካከል በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ፖለቲከኛ ናቸው።
አንዷለም አራጌ ስቃይ ላይ ናቸው
አቶ አንዷለም አራጌ በጨለማ ቤት ውስጥ መታሰራቸውና ወለል ላይ እንዲተኙ መደረጉ ቅዝቃዜው ጤናቸውን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ለፍርድ ቤት አስታወቁ።  የመተንፈሻ ችግር እንዳለባቸው የገለጹት አቶ አንዷለም አራጌ በጠባብ ክፍል ውስጥ ስድስት ሆነው በመታጎራቸው፣  ከባለቤታቸውና ጥቂት ቤተሰባቸው ውጪ ሌሎች ጓደኞቻቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው እንዳይጎበኟቸው መደረጉን በቅሬታ አቅርበዋል።
አቶ አንዷለም ጠበቆቻቸው የማነጋገር እድል መከልከላቸውን የገለጹ ሲሆን ዳኛው የስነስርዓት ጥያቄ በማንሳት አስቁመዋቸዋል። ጠበቃቸው የይግባኝ የፍርድ ሂደት ሳይቋጭ ከፍተኛው ፍርድ ቤት  የተከሳሾችን ንብረት ለመውረስ መጣደፉን በመጠቆም ያቀረቡትን መቃወሚያ ሳይጨርሱ ፍርድ ቤቱ “በጽሑፍ ያቅርቡ” ሲል አስቁሟቸዋል፡፡ ጠበቃ አበበ ጉታ በበኩላቸው ደንበኞቻችን በአንድ የክስ መዝገብ ቢከሰሱም ቃሊቲ እና ቂሊንጦ ተበትነው በመታሰራቸው ለጠበቆች ጥየቃ እንዳልተመቻቸውና በበቂ መጎብኘትና ማነጋገር አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤት አሳውቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ለውሳኔ ለጥር 10 ቀን 2005 ዓ.ም በጊዜ ቀጠሮ ያሻገረ ሲሆን ክርክሩ በጽሑፍ ተገልብጦ እንዲቀርብለት አዟል፡፡ (ዘገባውን ያጠናቀረው ኢሳት ነው።)
አለቆቻቸውን ያጋለጡት ሚኒስትር ከስልጣን ወረዱ
ሰንደቅ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዘገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ዳውድ መሐመድ ም/ጠ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት በተደረገ ግምገማ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን አስታውቋል። ሚኒስትር ዴኤታው የተነሱት በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ያለውን ብልሹ አሰራር እና ሙስና አስመልክቶ ከሳምንታት በፊት ዜናውን በዘገበው ጋዜጣ ላይ በግልጽ አስተያየት በመስጠታቸው ነው።
አቶ ዳውድ ህዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር እና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ግንባር በመፍጠር በመ/ቤቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን አድርገዋል በማለት ቅሬታቸውን ይፋ አድርገው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አለ ያሉትን አሳሳቢ ችግር ለከፍተኛ ሃላፊዎች ቢያቀርቡም መፍትሄ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል። ይሀንኑ አስተያየታቸውን ተከትሎ በተደረገ ግምገማ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል። የሚኒስትር ዴኤታው ባልተጠበቀ ሁኔታ መነሳት ሌሎች ሙስናን ደፍረው እንዳይዋጉ ፍርሀትን ያነግሳል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል። መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ቆርጦ መነሳቱን በተደጋጋሚ እየገለጸ ባለበት ሁኔታ ይህ መከናወኑ አስገራሚ እንደሆነም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያዉን ሠራተኞች እሮሮ በሳዑዲ
በኮንትራት ሠራተኝነት ወደአረብ ሀገሮች የሚሄዱ ኢትዮጵያዉያን የሚደርስባቸዉ በደል ከጊዜ ወደጊዜ መባባሱ ይሰማል። በቅርቡ ስዑዲ አረቢያ ዉስጥ ህይወታቸዉን ያጡና የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ እህቶች ጉዳይ የችግሩን አስከፊነት ያመለክታል።
ባሳለፍነዉ አንድ ዓመት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉን ከስራ ጋር በተያያዘና በአሰሪዎች በሚደርስባቸዉ ጥቃት ከአካል መጉደል እስከህልፈተ ህይወት ለሚያደርስ ከፍተኛ አደጋ እንደተጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነብዩ ሲራክ ከጄዳ የላከው ዘገባ እንደሚያስረዳዉ ሁለት ኢትዮጵያዉያን የኮንትራት ሰራተኞች በአሰሪያቸዉ ጥቃት እንደተፈጸመባቸዉ ታዋቂ የሳዉዲ ጋዜጦች ሳይቀሩ በዝርዝር ዘግበዉታል። ግለሰቡ በስለት በሰነዘረዉ ጥቃት የአንዲቱን ህይወት ቀጥፏል፤ ሌላዋን ለጉዳት ዳርጓል ሲል የጀርመን ሬዲዮ ዘግቧል።
የመናገር ነፃነት ሽልማት ለኢትዮጵያውያን
አራት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሄልማን ሃሜት የተባለው የአለም ዓቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሂዩመን ራይትስ ዋች ሽልማት ተሰጣቸው ። በእስራት ላይ ያሉት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ ውብሸት ታዮ እና ርዕዮት አለሙ እንዲሁም ከሃገር የተሰደደው ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ድርጅቱ ዘንድሮ ይህን ሽልማት ከሰጣቸው 41 ፀሃፊዎች መካከል ይገኙበታል።
የሸላሚው የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የሂዩመን ራይትስ ዋች የአፍሪቃ ጉዳዮች ተመራማሪ ላቲሻ ቤደ እንዳሉት የሄልማን ሃሜት ሽልማት የሚሰጠው በየሃገሩ የመናገር ነፃነትን በማራመድ በግል ጥረት ላደረጉና ተምሳሌት ለሆኑ ፀሃፊዎች ነው። ሽልማቱም እንደ ተሸላሚው የሚለያይ የገንዘብ ስጦታን ያካትታል። በየአመቱ የሚበረከትው ይህ ሽልማት ዘንድሮ በአለም ዙሪያ ለሚገኙ 41 ፀሃፍት ተሰጥቷል። ድርጅቱ እነዚህን ጋዜጠኞች የሸለመበትን ምክንያት ላቲሻ ቤደ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። «ሽልማቱ የተሰጣቸው በኢትዮጵያ የነፃ ጋዜጠኞችን እጣ ፈንታ አጉልቶ ለማሳየት ነው። 4ቱ ግለሰቦች በግልፅ እንደሚታወቀው የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት እጅግ በተገደበበት ሃገር የመናገር ነፃነትን በማራመድ በግላቸው ብዙ ስቃይ ደርሶባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ገፅታም አጉልቶ ለማሳየትም» መሆኑን የጀርመን ሬዲዮ ቅንብር ያስረዳል።

No comments:

Post a Comment