FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, December 15, 2012

ቀዩ መስመር በጨቋኝ በኩል ሲታይና በተጨቋኝ በኩል ሲታይ


መንግስታችን እርሱ ሲፈልገው ካልሆነ በስተቀር የማያከብረውን ሕገ-መንግስት መብት አላችሁ ብሎ ማሳመን ከባድ ሥራ ይመስለኛል፡፡ ከሕገ መንግስቱም ባሻገር አገራችን የተፈራረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ስምምነቶች መብታችንን ደጋግመው ያስታውሱናል፤ እኛም ወግ ደረሰን ብለን ስንጠቀምባቸው ከበስተኋላችን የማናውቀው ታርጋ ተለጥፎብን እናገኛለን፡፡ በዚህ ጊዜ እና ‹‹አይደለሁም›› ብንልም (ከመንግስት ያወቀ ቡዳ ነው እንዲል መሐመድ ሰልማን ‹‹ፒያሳ፤ መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ›› ባሰኘው መጣጥፉ) ‹‹አዋቂዎቹ›› ነህ ብለዋልና ‹‹መግባት ወይም መውጣት››፣ አልያም ‹‹ጥምር አገልጋይ›› መሆን የሚባል ቁርጥ ምርጫ ይሰጡናል፡፡
አሁን ደግሞ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም የቀድሞ አለቃቸው ቃና በሚመስል መልኩ፣ሁለት ኮፍያ አድርገን እንደምንጫወት ይነግሩን ጀምረዋል፡፡ የአንድ ዜጋ መብቱን ተጠቅሞ መጻፍ፥ መጻፍ ሳይሆን አሸባሪነት መሆኑ አሁንም ከቀጠለ ዴሞክራሲ ከስሙ በቀር በተግባር የታለ ለሚል ጠያቂ መልሱ ምንድነው የሚሆነው?
ቀዩ መስመር በጨቋኝ በኩል ሲታይና በተጨቋኝ በኩል ሲታይ ቦታው የተለያየ ነው፡፡ ለጨቋኝ፤ ስልጣኑን፣ ገመናውን፣ ባዶነቱን፣ ሙስናውን የሚሳብቅበት፣ ይህም ሥራውን ተአማኒነት አሳጥቶ ስልጣን የሚነሳው መስሎ ከታየውና፤ ያገባኛል ባዮች ተደማጭነትን ካገኙ ያ ‹ቀይ መስመር› ማለፍ ነው፡፡
ለተጨቋኝ፤ መብቱ – ሕገመንግስቱ ላይ የተቀመጠለት፣ ገደቡ – አገሩ እንጂ ባለስልጣን ወይም ፓርቲ አይደለም፡፡ ያገሩንም ጥቅም አሳልፎ አይሰጥም፡፡ የአገራችን ሕጎች ሆን ተብለው ለብዙ ትርጉም ተጋላጭ እንዲሆኑ ተደርጓል፣ በስህተት ያልተደረጉ ካሉም በስህተት እንዲተረጎሙ ይደረጋሉ እንጂ ተቃዋሚዎችን ከማስከሰስ አይመለሱም፡፡ ይህ ደግሞ ሆነ ተብሎ – ለስልጣን ጥብቅና ሲባል የተደረገ እንጂ፣ የቃላት ድህነት ኖሮብን የተፈጠረ እንከን አይደለም፡፡
የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 9፣ የሕገ መንግሥት የበላይነት በሚለው ስር ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ፡- ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፤ ይላል (መስመር የኔ)፡፡ በሕገ መንግሥቱ ከላይ የተጠቀሰውን ይዘን አንቀጽ 10 ደግሞ ስለ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲህ ይላል፡-
1.   ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፣
2.   የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡
በዚህ ሐሳባችንን ካጠናከርን ዘንዳ አንቀጽ 29 የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት ስር ደግሞ፡-
1.   ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡ (የእኔ አስተያየት፡-እውነታው ስንይዝ እንፈረጃለን የሚለው ነው)
2.   ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡ (የእኔ አስተያየት፡- አለ ብለው ቢተነፍሱ እንደማስረጃ ተቆጥሮባቸው የተለጠጠ ትርጉም ባለው ‹እንዳበጁሽ› በሆነው ሕጋችን ዜጎች ለስደትና ለእስር ተዳርገዋል)
መብቴን በቴሌቪዥን ብቻ ማየት አልፈልግም ወረቀት ላይ የተጻፈው ብቻውን ምንም አያደርግልኝም የምንፈልገው መብታችን ወደመሬት ይወርድ ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆንና ሕግ እንዲከበር ነው፡፡ እናስቀጥላለን የተባለው ‹ልማት› ይቀጥል፣ ፍረጃውና ዜጎችን ማግለሉ ግን አያግባባንምና ይቁምልን፡፡ መቼም የማንግባባበትን ቀይ መስመር ማስመሩ የተሻለ ጨቋኝ ለመሆን መጣጣር ካልሆነ በቀር የትም አያደርሰንም፡፡

No comments:

Post a Comment