FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, December 22, 2012

የመንግሥት ሌቦች ካልተወገዱ ‹‹የሌቦች መንግሥት›› ያቋቁማሉ!


በአገራችን የሙስና አደጋ  በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሥርም እየሰደደ ነው፡፡ እየተስፋፋም ነው፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ብሔራዊ ባህልነት እየተቀየረ ያለ ይመስላል፡፡
የተወገዘ የነበረው የተለመደ ሆኗል፡፡ ጉቦ መውሰድ ኃጢአትና ወንጀል መባሉ ቀርቶ ጉቦ አለመቀበል ጅልነትና ሞኝነት እየተባለ ነው፡፡
ይህ የእኛ አባባልና የእኛ ማስተዋል ብቻ ሳይሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም አደጋውን በግልጽ ገልጸውታል፡፡ የመንግሥት ሌቦች አሉ ብለዋል፡፡ መልካም አስተዳደርን እያደናቀፈ ነው ብለዋል፡፡ ልማትን ይገታል ብለዋል፡፡ መወገድ አለበትም ብለዋል፡፡
ትልቁ ጥያቄ ተግባሩ የት አለ? የሚል ነው፡፡ የመንግሥት ሌቦች ተራ ሌቦች አይደሉም፡፡ አደገኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በገንዘብ የታጀቡ ናቸው፡፡ በሥልጣንም የተደገፉ ናቸው፡፡ ምግባረ ብልሹነት የተጠናወታቸው ስለሆኑ ሕገወጥ ገንዘብና ሥልጣናቸውን ላለማጣት ሕግን ከመጣስና ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም፡፡ ሌላውን አስወግደው እነሱ ብቻ የሚቆጣጠሩትና የእነሱን ፍላጎት ብቻ የሚያረካ መንግሥት ከማቋቋም ወደኋላ አይሉም፡፡ የመንግሥት ሌቦች ካልተወገዱ የሌቦች መንግሥት ያቋቁማሉ ያልነውም ለዚህ ነው፡፡
በአገራችን ሁለት ዓይነት ባለሥልጣናት አሉ፡፡ በግልጽና በማያሻማ መንገድ ልናስቀምጠው እንወዳለን፡፡ ከሙስና የፀዱ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ ሕዝቡን ለማገልገል የሚፈልጉ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ አቅምና ችሎታ ያላቸው ቅድሚያ ለአገርና ለወገን የሚሰጡ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ የሕዝብ ወገን የሆኑ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ ሁሉንም ሌባ ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም ፀረ ሕዝብ አይደሉም፡፡ ሀቀኛ፣ ብቁና ሕዝባዊ ባለሥልጣናት እንዳሉ አንጠራጠርም፡፡
በተፃራሪው ደግሞ ፀረ ሕዝብ፣ ስስታም፣ ስግብግብና በሙስና የተጨማለቁ አሉ፡፡ ለግል ጥቅምና ክብር ሲሉ አገርንና ወገንን ከመሸጥ፣ ከመለወጥ፣ ከመካድና ከመርገጥ ወደኋላ የማይሉ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ በሥልጣን ላይ መቀመጥ የሌለባቸው፣ መሾምና መከበር የማይገባቸው ባለሥልጣናት አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት በሁለት ጎራ የተከፈሉ ባለሥልጣናትና ሹሞችን ይዞ አገርን ከአደጋ ማዳን፣ ሕዝብን ከድህነት ማላቀቅና ፍትሕና ዴሞክራሲን ማስፈን አይቻልም፡፡
ይህን ሕዝብ ከድህነት ማላቀቅና ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የማድረግና የማጠናከር ራዕይ እውን የሚሆነውና በተግባር የሚታየው፣ ሀቀኖቹ በሌቦቹ ላይ የበላይነት ሲያረጋግጡ ብቻ ነው፡፡ በተግባር፡፡
በተግባር ሀቀኞች በሌቦች ላይ የበላይነት ሊኖራቸው የሚችለው ደግሞ ሲታገሉና በትግሉም ዋጋ መክፈል ሊኖርባቸው እንደሚገባ አምነው ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው፡፡
በቃል፣ በንድፈ ሐሳብ፣ በመግለጫና በቃለ መጠይቅ የመንግሥት ሌቦች እንዳሉ መናገሩና ማውገዙ ብቻ የትም አያደርስም፡፡ እንቅፋት ናቸው ብሎ መግለጹ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የመንግሥት ሌቦች ካልተወገዱ የሌቦች መንግሥት ይመሠርታሉ ብሎ ማመን፣ ይህ የሌቦች መንግሥት እውን እንዳይሆን ለመቅጣት፣ ለማስወገድና ለመጠራረግ ቆራጥ ትግል ያስፈልጋል፡፡
የሕዝብ ወገን የሆኑ ሹማምንት በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ውስጥ ያሉትን ሌቦች ከልብ ለመታገል የሚፈልጉ ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው ይሰለፋል፡፡ የሌቦች መወገድ ለሕዝብ ጥቅም ነውና፡፡ ሕዝብ ከጎናቸው ስለሚሆንም ሌቦቹን ለማስወገድ በቂ አቅም ይኖራቸዋል፡፡ በቂ ድጋፍም ይኖራቸዋል፡፡
በመሆኑም ሀቀኞች ሌቦችን ለማስወገድ ተቸገርን ብለው ሊያማርሩ አይገባም፡፡ ሊጨነቁ አይገባም፡፡ ሕዝቡን ከጎናቸው ካሰለፉ ጉዳዩ ቀላል ነው፡፡ ከሕዝብ ከራቁ ግን የሌቦቹ መጫወቻና በሌቦቹ በቀላሉ የሚገፉና የሚገፈተሩ ይሆናሉ፡፡
እኔ’ኮ አልሰርቅም፣ እኔ’ኮ አልዘርፍም፣ እኔ’ኮ ጉቦ አልቀበልም፣ እኔ’ኮ ለገንዘብና ለንብረት አልስገበገብም፣ እኔ’ኮ ሕገወጥ ገንዘብና ንብረት የለኝም በማለትና ከደሙ ንፁህ ነኝ ብሎ ጥግ ይዞ መቆም አይፈቀድም፡፡ በኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ባለሥልጣን የራሱን ንፁህ መሆን ብቻ ሳይሆን ሌቦቹንና ወንጀሎችን የመታገል ግዴታና ኃላፊነትም አለበት፡፡ ሲሾም ቃለ መሃላ የፈጸመውና የተቀመጠበት ወንበር ያሸከመው ግዴታ ሕገወጦችን ለመታገልና ለማስወገድ ነውና፡፡
ችግር የለም ነገ ከነገ ወዲያ እናስወግዳቸዋለን ተብሎ የሚተው ጉዳይም አይደለም፡፡ ሀቀኛው በተዝናና ቁጥር ሌባው እየተጠናከረ ይመጣል፡፡ በገንዘብ ተከታዩን ይገዛል፡፡ በገንዘብ ኔትወርክ ይዘረጋል፡፡ በገንዘብ ከውጭ ጠላት ጋርም ሊተሳሰር ይችላል (ሌብነት ድንበር የለሽ ነውና)፡፡ በገንዘብ ሀቀኞችን የሚያስወግዱ ኃይሎችን በማሰማራት ሊያሸንፍ ይችላል፡፡ በገንዘብ የመገናኛ ብዙኀንን ሊቆጣጠር ይችላል፡፡
አሁን ጊዜ የለም፡፡ መዝናናት አይቻልም፡፡ ቸልተኝነት ያስጠይቃል፡፡ ከደሙ ንፁህ ነኝ ብሎ ጥግ መያዝ የሌብነቱ አካል መሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ሕግ የሚጠይቀው ማድረግን ብቻ ሳይሆን አለማድረግን ጭምር ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ነው፡፡ አንደ ፓርቲም እንደ መንግሥትም የመጀመሪያው ሥራው በጠንካራ ግምገማ በከፍተኛ የአገር ኃላፊነት በመንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ ሌቦችን ማጥራት ነው፡፡ የሕዝብ፣ የአገር፣ የመንግሥት፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የሰላም ጠላቶችን ማስወገድ ነው፡፡
አቅም ያጣውን፣ ዕውቀትና ልምድ ያነሰውን በትምህርትና በሥልጠና ማጠናከር ይቻላል፡፡ ሌባና ወንጀለኛን ግን የሥልጠና፣ የሴሚናርና የውይይት ብዛትና ዓይነት አይለውጠውም፡፡ ሕጋዊ ዕርምጃ ብቻ ነው መፍትሔው፡፡
ኢሕአዴግም መንግሥትም መስቀለኛ መንገድ ላይ ናቸው፡፡ የቱ አቅጣጫ ይሻለናል ብለው መርጠው ሊጓዙ ይገባል፡፡ ከሌቦችና ከሙሰኞች፣ ከከሃዲዎችና ከወንጀለኞች ጋር አብረን እንጓዝ ካሉ ጉዞው ወደ ገደልና ወደ ውድቀት ነው፡፡ ጉዞው ሌቦች የበላይነት የሚይዙበትና የሌቦች መንግሥት የሚያቋቁመበት ይሆናል፡፡
ፓርቲውና መንግሥት እየፀዱ ከሆነ ደግሞ በልማት፣ በፍትሕ፣ በዴሞክራሲ፣ በሰላም፣ በደኅንነት መጓዝ ይቻላል፡፡ አዲስና ጠንካራ ኢትዮጵያን በመፍጠር ከሕዝብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ይቻላል፡፡
በሌቦች፣ በሙሰኞችና በወንጀለኞች ባለሥልጣናት ላይ ኢሕአዴግና መንግሥት አስቸኳይ ሕጋዊ ዕርምጃ ይውሰዱ፡፡ ቆራጥ ውሳኔ በተግባር ያሳዩ፡፡
የመንግሥት ሌቦች ካልተወገዱ የሌቦችን መንግሥት ያቋቁማሉና!
http://mail.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8932-2012-12-22-09-23-40.html

No comments:

Post a Comment