በዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነጋዴ ወይስ ለወገን ደራሽ?
በዱባይ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ፓስፖርታቸው በአሰሪዎቻቸው አማካይነት ለተመለሰላቸው ወገኖች የፓስፖርት እድሳት በሚል አንድ ሺህ አንድ መቶ ድራም እንደሚያስከፍል ተሰማ። ለጎልጉል በስልክ መረጃ የሰጠች አንድ የዱባይ ነዋሪ ኤምባሲው አገልግሎቱን መጀመሩ እንደሚያስመሰግነው ጠቁማ፣ ክፍያው ግን የተጋነነ ንግድ እንደሚመስል አስታውቃለች።
ዘጠና ከመቶ የዱባይ ነዋሪዎች ፓስፖርታቸው ጊዜው ያለፈበትና በአሰሪዎቻቸው በመያዣነት የተያዘ እንደሆነ የጠቀሰችው ይህች ወጣት “በችግር ላይ ካሉ ዜጎች ላይ ከስድሰት ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር መቀበል አግባብ አይደለም። ኤምባሲው ፓስፖርታቸው ለተወሰደባቸውም መላ ይፈልግ” ስትል ጠይቃለች። አሰሪዎቻቸው በሚያደርሱባቸው በደል ተማረው የሚጠፋ ወገኖች ፓስፖርታቸው በመያዣነት አሰሪዎቻቸው ዘንድ ስለሚቀር የጉዞ ሰነድ የላቸውም። ወደ አገራቸው መመለስ ሲፈልጉ ሆን ብለው እጅ በመስጠት እስከ አንድ ወር ታስረው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል። አንዳንድ አሰሪዎች ሰራተኞቹ ሲጠፉ ፓስፖርታቸውን ለኤምባሲ እንደሚመልሱ የገለጸችው ስደተኛ አሁን በኤምባሲው የተጀመረው አገልግሎት ፓስፖርታቸው ኤምባሲ የተመለሰላቸውን ብቻ የሚመለከት ነው ብላለች።
ምደባው “የህግ ተቃርኖ ያለው” ነው
ሰሞኑን አቶ ሃይለማርያም ስላካሄዱት ምደባ ጠንካራ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር አሁን ካለው ህግ ጋር በቀጥታ ተጻራሪ እንደሆነ ዘግቧል፡፡ “ነሐሴ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. የተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ክፍል ሁለት አንቀጽ 3(4) የብሔራዊ ባንክ ተጠሪነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል በማለት ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በአዲሱ የካቢኔ መወቅር መሠረት የፋይናንስና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን እንዲከታተሉ ዶ/ር ደብረፅዮን በመሾማቸው፣ ከተጠቀሰው አንቀጽ ጋር የሚቃረንና ብሔራዊ ባንክም ከተቋቋመበት አዋጅ ውጭ ለዶ/ር ደብረፅዮን ሪፖርት እንዲያደርግ ያስገደድዋል” በማለት ኢህአዴግ የራሱን ሕግ በአዲሱ ምደባ መቃወሙን ዘግቧል፡፡
በመቀጠልም የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ከተቋቋመበት አዋጅ አንጻር ምደባው የፈጠረውን የህግ መፋለስ ሲያብራራ በአዋጁ መሠረት ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠ/ሚ/ሩ ቢሆንም በምደባው መሠረት “ኮሚሽኑ ለአቶ ሙክታር ከድር ሪፖርት እንዲያደርግ” መደረጉን በመግለጽ የሥልጣን ጉዳይ ከተነሣ ህወሃት/ኢህአዴግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የማይቆፍረው ጉድጓድ እንዲሁም የማያፈርሰው ህግ እንደሌለ በሚያጋልጥ መልኩ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
መለስ ራስ አሉላን ተኩ ተባለ
በጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ስም የሚጠራው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስያሜው ተሰርዞ በአቶ መለስ ስም እንዲጠራ መወሰኑንና የራስ <አሉላ ስም ተሰርዞ “መለስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” በሚል መተካቱን ኢየሩሳሌም አርአያ በሚል ስም የሚታወቁት ጸሃፊ በተለያዩ ድረ ገጾች ባሰራጩት ዜና አመልክተዋል። ትምህርት ቤቱ በቀድሞው መንግስት የተሰራ ሲሆን፣በ2002 ዓ ም አቅሙን ለማሳደግ የአካባቢው ተወላጆች ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ገንዘብ በማሰባሰብ ያስጀመሩት ግንባታ ባለፈው ነሃሴ ምረቃ ለማካሄድ ተያዘው እቅድ በመለስ ሞት ምክንያት እንዲራዘም ተደርጎ ነበር። በቅርቡ ከሁለት ሳምንት በፊት ምረቃው ሲካሄድ የተገኙት ባለስልጣናት የትምህርት ቤቱ ስም መቀየሩን ይፋ እንዳደረጉ የኢየሩሳሌም አርአያ ዜና ያስረዳል።
ውሳኔውን ተከትሎ በውጪና ባገር ውስጥ የሚገኙ የክልሉና የአካባቢው ተወላጆች ድርጊቱን አጥብቀው እኮነኑት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ታሪክን የማጥፋት ዘመቻ አካል እንደሆነ ተመልክቷል። ተንቤን አብዩአዲ የሚገኘውን ትምህርት ቤት አስመልክቶ ክልሉም ሆነ የሚታወቅ የመንግስት አካል እስካሁን ማስተባበያ አልሰጡም።
የኤርትራ ኢኮኖሚ ዕመርታ
“አምባገነንነት ተቀባይነት እንዲያገኝ የሞከሩ” በማለት በሞቱ ማግስት ሰፋ ያለ ዘገባ የሰጠው የኢኮኖሚስት መጽሔትን በሚያስተዳድረው ድርጅት ሥር የሚገኘው “ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት” (Economist Intelligence Unit) የተሰኘው ቡድን ኤርትራ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እመርታ እንደምታሳይ ተነበየ፡፡ ቡድኑ ከዓለምአቀፉ የገንዘብ እና ሌሎች ድርጅቶች ያገኘውን መረጃ በማገናዘብ ባወጣው ዘገባ መሠረት በመጪው የአውሮጳውያን አዲስ ዓመት (2013) የኤርትራ ኢኮኖሚ በ8.5 በመቶ እንደሚያድግ ዘግቧል፡፡ ይህም እድገት ኤርትራን በምስራቅ አፍሪካ ካሉት አገራት መካከል የቀዳሚውን ስፍራ እንደሚያጎናጽፋት ገልጾዋል፡፡ የዕድገቱ ዋንኛ መሠረት የአገሪቱ ከፍተኛ የግብርና ምርት እንዲሁም ሌሎች የማዕድን ሥራዎች እንደሚሆኑ ጨምሮ ተናግሯል፡፡
ቡድኑ ያወጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ለ21ዓመታት በአቶ ኢሳያስ የሚመራው የሻዕቢያ አገዛዝ ኤርትራ ከ2012 – 2015 ድረስ ባሉት ዓመታት ከ 7 – 10 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ታሳያለች ብሎ ከተነበየው ጋር እንዲመሳሰል አድርጎታል፡፡ ቡድኑ ባወጣው አጠቃላይ ዘገባ መሠረት በዚሁ በመጪው 2013ዓም ህወሓት/ኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በድርብ አኻዝ ሳይሆን በ5.5በመቶ ብቻ እንደሚያድግ አስታውቋል፡፡
መለስ በመንደራቸው ምስላቸው መቀደዱ ተሰማ
በአድዋ ከተማ አደባባይ ላይ ተሰቅሎ የነበረ የመለስ ፖስተር ተቀዳዶ እንደተጣለ ምንጮች በመጥቀስ ኢየሩሳሌም አርአያ በመባል የሚታወቁት ጸሃፊ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ባሰራጩት ጽሁፍ አስታወቁ። ድርጊቱ ያናደዳቸው የክልሉ ካድሬዎች “የመድረክ ተለጣፊ የሆነው አረና ፓርቲ ነው ይህን የፈፀመው” በማለት ያልተጨበጠ የፈጠራ ወሬ እያሰራጩና እየዛቱ ነው ያሉት ምንጮች፣ ድርጊቱን የፈፀመው የአካባቢው ህዝብ እንጂ የየትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳልሆነ አቶ ኢየሩሳሌም ገልጸዋል።
አረና በተለያዩ ጊዚያት በህወሃት ካድሬዎችና ታጣቂዎች አመራሮቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ እንደሚንገላቱበትና እንደሚታሰሩበት በተደጋጋሚ መግለጹ የሚታወስ ነው። የመለስን ምስል ተቀዶ መጣል አስመልክቶ ከመንግስትም ሆነ ከክልሉ ማስተባበያ አልቀረበም።
ኦሮምያ “ስደት አሳሰበኝ” አለ
የኦሮሚያ ክልል ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር ባዘጋጀው ውይይት ላይ ስደት በተለይም በኦሮሞ ልጆች ላይ መብዛቱ እንዳሳሰበው አስታወቀ። የክልሉ መንግስት የቢሮ ሃላፊ እንዳስታወቁት በህገወጥ ደላሎችና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጪ አገር በመሄድ ለመከራ ከሚዳረጉት ወገኖች መካከል የኦሮሞ ተወላጆች መብዛታቸው ክልሉን እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሆኗል። በዚሁ ሳቢያ የተጠራው ውይይት ሲጠናቀቅ በክልሉ ሰዎች ገንዘብ እናገኛለን ብለው ስደትን እንዳይመርጡ ልክ እንደ ጤና ኤክስቴንሽን የቤት ለቤት ትምህርት ለማስጀመር መወሰኑን ተናግረዋል።
በስብሰባው ላይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርን በመወከል የተናገሩ ባለስልጣን እንዳሉት ከብቶቻቸውንና መለወጥ የማይቻለውን መሬታቸውን በመሸጥ፣ ለፍተው ያፈሩትን ንብረታቸውን በዕዳ በማስያዝ፣ ቤቶቻቸውን አሳልፎ በመስጠትና በብድር ካገራቸው ከወጡ በኋላ ለመከራ የሚዳረጉ ዜጎች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል።
ተማም አባ ቡልጉ “አሸንፋለሁ” አሉ
ደንበኞቼ የተከበሩ የሃገር ሽማግሌዎች፣ በጣም የተማሩ ሰዎች፣ በሃይማኖትም በአለማዊም ባህሪያቸው ጨዋ የተባሉ ደንበኛ ሀበሻ የሚባሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በተፈጥሮ ብዙዎቹ ከአንድና ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን የሚረዳ እርዳታ ድርጅት ያላቸው፣ ትልልቅ መፅሃፍት የፃፉ፣ ጋዜጠኞች፣ ሌሎቹም የህግ ባለሙያዎች፣ የተሳካለቸው ነጋዴዎች፣ በባህሪ ደግሞ በወንጀል ላይ ይሰማራሉ የምትላቸው ሰዎች አይነት አይደሉም ሲሉ ስለሚከራከሩላቸው ተጠርጣሪዎች አቶ ተማም አባ ቡልጉ ተናገሩ። የሙስሊም ማህበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዋና ጠበቃ ከኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ተጠርጣሪዎቹ ሊታሰሩ የማይገባቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።
የቀረቡባቸው ማስረጃዎች ባብዛኛው የማያስከስሱ፣ ብዙዎቹ ንግግሮች የማያስጠይቁ፣ እያንዳንዱ ጉዳይ ማስረጃ ያለውና ባግባቡ ተያዘ በመሆኑ ተከራክረው እንደሚሸንፉ ለቅንጣትም ጥርጣሬ እንደሌላቸው አቶ ተማም አባቡልጉ በቃለ ምልልሳቸው አስታውቀዋል።
ታዳጊዎች ናሳን የመጎብኘት አድል አገኙ
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ዘርፍ ተወዳድረው ከፍተኛ ውጤት ያገኙ ስድስት ተማሪዎች ናሳን የመጎብኘት እድል ማግኘታቸው ታወቀ። ሪፖርተር ባለው ሳምንት የረቡዕ እትሙ እንዳስታወቀው እድሉን ያመቻቸው አይከን ኢትዮጵያ የውድድር ማዕከል ሲሆን የተመረጡት ተማሪዎች አድሜያቸው ከ13 በታች ነው።
ከአዲስ አበባ የተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውድድር አካሂደው በየዓመቱ ፍሎሪዳ የሚገኘውን የናሳን ኬኔዲ ስፔስ /ጠፈር/ ማዕከል የመጎብኘት እድል ለማግኘት ችለዋል። ሶስት ሴትና ሶስት ወንድ ተማሪዎች ባገኙት በዚህ ታላቅ እድል የማዕከሉን ልዩ ልዩ ክፍሎች ይጎበኛሉ። ከታወቁ ጠፈርተኞች ጋር እንደነሱ ለብሰው ስለ ሳይንስ የመወያየትና መረጃ የሚለዋወጡበት እድል ተመቻችቶላቸዋል። ይህ ዕድል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እንደሚያበረታታቸውና ወደፊትም በስፋት እንደሚቀጥል የማዕከሉን ሃላፊ ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል።
SOURCE: http://www.goolgule.com
No comments:
Post a Comment