ህዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ ቀርቦበት የነበረው ክስ እንደገነ ተቀሰቀሰ፤
ትላንት ሃሙስ ህዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ወደ ጋዜጣው ቢሮ የፍርድ ቤት መጥሪያ ይዘው የመጡት የፖሊስ አባላት ጋዜጠኛ ተመስገን ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑ ተነግሯቸው ተመልሰዋል ።
ዓርብ ህዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰሃት በኋላ የፌዴራል ፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ተኛ ወንጀል ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን በሌለበት ችሎት የሰየመ ሲሆን የፍርድ ቤት መጥሪያ ለጋዜጠኛው ሊያደርሱ የሄዱት ፖሊሶች በጊዜው ሊያገኙት አለመቻላቸውንና ለሥራ ባልደረቦቹ ግን መንገራቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የዋስትና መብት የነፈጉት ዳኛ መጥሪያው እንዳልደረሰው ካረጋገጡ በኋላ ዐቃቤ- ሕግን የውሳኔ አስተያየት የጠየቁ ሲሆን ዐቃቤ- ሕግ በበኩሉ በቀጣይ እንዲቀርቡልኝ ማዘዣ ይጣፍልኝና አጭር ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል፡፡
የችሎቱ ዳኛ በበኩላቸው የፍርድ ቤት መጥሪያ ለፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እና ለድርጅቱ ጠበቃ እንዲደርስ ማዘዣ እንዲወጣ አዘው ቀጣይ ቀጠሮውንም ለታህሳስ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከጤናው ጋር በተያያዘ ወደ አዋሳ መጓዙን ተከትሎ መጥሪያ እንደደረሰው ለኢሳት ገልጿል።
የፕሬስ አፈናው በአቶ ሀይለማርያም የስልጣን ዘመንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአዲስ ታይምስ መጽሄት ላይ ሲሰራ የገጠመውን ችግር በመዘርዝር ገልጿል
ተመስገን ፍትህ ጋዜጣን ሲያሳትም በነበረበት ወቅት ከ39 ባላነሱ እንያንዳንዳቸው ከ106 በላይ ዝርዝር ክሶችን በያዙ ወንጀሎች መከሰሱ ይታወቃል።
ከታዋቂው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር በፕሬስና በወቅታዊ የአገራች ፖለቲካ ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ በትኩረት ክፍለ ጊዜ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
No comments:
Post a Comment