FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, December 1, 2012

አሁንም የተሃድሶ ያለህ!!!


(ርዕሰ አንቀጽ)
intellectual reform



“አንድነትን ስንመሰርት በቅንጅት ወቅት ስለሰራነው ጥፋትና የፖለቲካ ስህተት የገመገምነው ነገር የለም” ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም አንድነት ፓርቲን ከቅንጅት ጋር በማነጻጸር ከተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲና ድርጅቶች መዋቅራዊ ጥንካሬና ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው ውጤት ማስመዝገብ ያለመቻላቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው። ተቃውሞ በኢትዮጵያ በፓርቲ መሪዎችና በገዢው ኢህአዴግ መካከል የሚደረግ እሰጥ አገባ ካልሆነ በስተቀር በደጋፊዎች ተሳትፎ ገዢውን ፓርቲ የማስገደድና እጁን የመጠምዘዝ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊታይ አልቻለም።  ከቅንጅት መፈራረስና ልዕልናው መክሰም ጋር የህዝብ ስሜትም አብሮ ተዳፍኗል የሚለው አስተያየት ሚዛን የደፋ የሚሆንባቸው የበዙት ለዚሁ ነው። በድርጅት ደረጃ ችግሩን ተመልክተው ስለመታደስ የሚያስቡ ስለመኖራቸው ግን ለረዥም ጊዜ አልሰማንም።
በኢትዮጵያ ህዝብን ለትግልና ለእምቢተኝነት የሚያነሳሱ ጉዳዮች ሞልተው የፈሰሱ ቢሆንም ህዝብ በስርዓቱ ከመበሳጨት የዘለለ እንቅስቃሴ አለማድረጉ ስርዓቱ ከዘረጋው የአፈና መዋቅር ጋር የሚያገናኙት ቢኖሩም በዋናነት የተቃዋሚዎች ድክመት ጎልቶ እንደሚታይ አሁን አሁን ይፋ እየሆነ ነው። በተለይም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሰሞኑን “የግል አስተያየቴ ነው” በማለት ያቀረቡት ጽሁፍ የችግሩ ቁልፍ ነውና ሁሉም ወገኖች አሰራራቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባ ይሰማናል – አሁን!!
“ከኔ አመለካከት ጋር የማይስማሙ እንዳሉም እገነዘባለሁ፡፡ በበኩሌ ከኔ ጋር የማይስማሙትን አከብራለሁ፡፡ ሃሳባቸውንና አመለካከታቸውን ባልጋራና ባልስማማባቸውም እነሱንም ሆነ ሃሳባቸውን፣ አመለካከታቸውንና አቋማቸውን አዳምጣለሁ። አከብራለሁ፡፡ የመረጃ ስህተት ካለ ስህተቴን ለመቀበልና ለማረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የኔን ሃሳብ፣ አመለካከትና አቋም የማይጋሩት ግን እንዲያዳምጡኝና እንዲያከብሩልኝ አደራ እላለሁ” ሲሉ የወቅቱን የአገራችንን ሁኔታና የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ በተመለከተ ለመወያየት በተጠራ ስብሰባ ላይ የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ባቀረቡት ንግግር የተናገሩት ነው። ሌላስ ምን አሉ?
“ኅብረሰባችንን ስናይ ብሶተኛና የማጉረመርም ደረጃ ላይ እንጂ ተናድዶ ንዴቱን በእንቅስቃሴ ለማሳየት ዝግጁ የሆነበት ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስልም፡፡ ብዙ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች አሉበት፡፡ ይህንን ሰቆቃውንና ብሶቱን ያማርራል፡፡ በይፋና በአደባባይ አይገልጽም፡፡ ብሶቱ በማጉረምረም ደረጃ የሚገልጽ ነው እንጂ በአጠቃላይ ወደ ኅብረተሰባዊ ንዴት አልተለወጠም፡፡ የተናጠል ንዴቶች አልፎ አልፎ ቢገለፁም ሠፊና የአጠቃላይ የኅብረተሰቡ አልሆኑም፡፡ እነዚህ የተናጠልና ትናንሽ ንዴቶች ወደ ተደራጀና የተቀናጀ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች አልተለወጡም፡፡ በሌሎች አገሮች በዳቦ ወይም በነዳጅ ዋጋ ላይ ትንሽ ጭማሪ ከታየ የኅብረተሰቡ ንዴት ይገነፍላል፡፡ በኛ ህዝብ ዘንድ ግን ይህ አይታይም፡፡ ምልክት ከታየም ጥቂት፣ የተናጠል፣ ያልተደራጁና ያልተቀናጁ ናቸው” ነበር ያሉት።
አዎ!! ያለመደራጀት ችግር፣ የግንዛቤ ችግር፣ ደጋፊን አሳምኖ የመምራት ችግር፣ ከስህተትና ከውድቀት ያለመማር ችግር፣ የተሃድሶ ችግር፣ የእውቀት ተሃድሶ ችግር፣ የራዕይ ችግር፣ በስድብና ተቃውሞ ላይ ያተኮረ ትግል፣ ፍረጃና ማግለል ላይ የተንጠለጠለ የትግል ጉዞ፣ ካለፈው ያለመማርና ይሉኝታን ያዘለ ትግል፣ በግልጽ ራስንና ተሞክሮን ያለመገምገም ችግር፣ የተድበሰበሰ አቅጣጫ የመከተል ችግር፣ እንደኔ አስብ የሚል አባዜ፣ ድርጅትህን አፍርሰህ እኔ ጋር ተጠቃለል የሚል ሌላውን ያለማክበር ችግር፣ እኛ ያልባረክነው የተቃውሞ መንገድ ውግዝ ነው የሚል የትምክህት ስሜት፣ በተመሳሳይ አጀንዳ እየተመሩ መቧደን፣ ማነስ፣ ትንንሽ መሆን፣ ከትግልና ከትግሉ መስመር ይልቅ ወንበርና ስልጣን መናፈቅ፣ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ከማስወገድ ይልቅ በሃሜትና በማሳጣት መስመር መረባረብ … የሚጠቀሱት በሽታዎች ናቸው። በተግባር እንደታየውና ሁሉም እንደሚመሰክሩት እነዚህ ችግሮች የተቃዋሚውን ጎራ ጨረቃ ላይ ጥለውታል። ባለበት እንዲረግጥ አድርገውታል። በዚህም ሳቢያ አብዛኞች ከየትኛው ወገን እንደሚሆኑ መወሰን አቅቷቸዋል። በኛ እምነት ይህኛው የኅብረተሰብ ክፍል ታላቅና ሃይል ያለው ስለሆነ በእውቀት ተሃድሶ ወደ ትግሉ የሚገባበት መንገድ መቀየስ አለበት። የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ!!
“እውቀት የሌለው፣ መረጃ የማያገኝ ህዝብ፣ የተደራጀና የተቀናጀ አደረጃጀቶች የሌለው ሕዝብ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠየቀውና የሚጠበቀው የተናደደ ኅብረተሰብን መፍጠር ሳይሆን መረጃ የሚያገኝ፣ እውቀት ያለው፣ የተደራጀና ድርጅቶቹ የተቀናጁ ኅብረተሰብ መፍጠር ነው” ሲሉ አሰተያየታቸውን ያሰፈሩት ዶ/ር ነጋሶ ደግ ብለዋልና ጆሮ ላላቸው ታላቅ መልዕክት ነው።
ስለሆነም የወደፊት የትግል አቅጣጫችንን የማሳወቅ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የማደራጀትና፣ ድርጅቶችን የማቀናጀት ሥራን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ልምዳቸውንና በግልጽ የተመለከቱትን አስታከው ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ በስፋት መድረክ ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለን እናምናለን። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል እንደገለባ መንሽ በተመለከተ ቁጥር አይቦንም፤ እውቀቱም ቀላል ነው። በየወቅቱ የሰለቸንን የመቡነን አደጋና ከድርጅት ወደ ድርጅት የመገላበጥ እንዲሁም ስም እየቀየሩ ብቻ ለቁጥር የሚያዳግት ድርጅት መመስረት የሚቆመው ይኸው የእውቀት ተሃድሶ ተግባራዊ ሲሆን ነው። እውቀቱ በኮሌጅ ወይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰጥ አይደለም። በእውነተኛነትና በቅንነት ላይ የተመሠረት እውቀት ነው፡፡ ከራስ በራስ የሚቸር ቀናነትን መሰረት ያደረገ ለራስ የመታመን ጥያቄ ነው። ሰው ምን ይለኛልን አውሎቆ የጣለ እውቀት ነው፡፡ በጥቅምና በወዳጅነት የሚደለል ሳይሆን በሐቀኝነት ዓለት ላይ በመተማመን ጸንቶ የቆመ እውቀት ማለት ነው፡፡ ለራሱ የሚታመን የትግል መስመርና ታጋይ ራዕይ አለው። ለለውጥ ንቅናቄ መሪውን አይጠብቅም፡፡ ያነገበው ራዕይ እያንደረደረ የድሉ በር ላይ ያደርሰዋል። ከሁሉም በላይ የነቃና በመረጃ የታጠቀ ህዝብ ድርሻውን ያውቃል። መብቱን ለማስከበር የትኛውንም ወገን የማስገደድ አቅም ያዳብራል። እንዲህ ያለ ህዝብ በተፈጠረ ቁጥር የአምባገነኖች ጡንቻ እየሰለለ ይሄዳል። ልባቸውም ይርዳል። እንዲህ ያለው የእውቀት ተሐድሶ ከድርጅት ወይም ከፓርቲ አይመጣም፡፡ በስብሰባ ብዛትና በጥናትና ምርምር ምጥቀት አይከሰትም፡፡ ግንኙነት ማድረግ በሚቻልበት አጋጣሚ ሁሉ ወሬ በመውቀጥ በተዓምር ብቅ አይልም፡፡ እንዲያውም ይህንን ዓይነቱ አካሄድ በሙሉ የራስ ማንነትን በማጥፋት በአጀብ፣ በቡድን ተግበስብሶ ለመመራት ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ተሃድሶው ከራስና በራስ መጀመር አለበት፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን በደመነፍስ ሳይሆን በእርግጠኝነት ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ከመምራትም ሆነ ከመመራት፤ ከመደራጀትም ሆነ ከማደራጀት በፊት እውቀት ይቀድማል! ለዚህ ደግሞ ተሃድሶ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም አሁንም ደግመን የምንለው ቅድሚያ ከራስ የሚጀመር ተሃድሶ ባስቸኳይ!!

SOURCE: http://www.goolgule.com

No comments:

Post a Comment