FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, January 24, 2013

ለመጪው የአካባቢ ምርጫ የተመዘገበው ህዝብ ከ30 በመቶ ከፍ ሊል አልቻለም


ጥር ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢሳት ከምርጫ ቦርድ የውስጥ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሰረት በምርጫው ለመሳተፍ የተመዘገበው ሰው ቁጥር ድርጅቱ በይፋ ከተገለጠው በእጅጉ ያነሰ ነው።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከ89 በመቶ በላይ መራጭ ህዝብ እንደተመዘገ በይፋ ቢያስታውቅም፣ እስካሁን በትክክል የተመዘገበው ግን 33 በመቶ ብቻ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
በህዝቡ የምርጫ ፍላጎት ማጣት ግራ የተጋባው ኢህአዴግ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አመራሮችን ” ቀይ መብራት ውስጥ ናችሁ” የሚል ማስፈራሪያ ልኳል። የወረዳ ባለስልጣናቱም በደረጃው ላሉ አባላት አስፈላጊው ነገር ተደርጎ መራጩ ህዝብ ወጥቶ እንዲመዘገብ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የኢህአዴግ አባላት  የቤት ለቤት ቅስቀሳ እንዲካሄድ በመወሰን  ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩ ቢሆንም፣ ህዝቡ ግን ወጥቶ ለመመዝገብ ፍላጎት አለማሳየቱ ታውቋል።
አባላቱ በግለሰቦች ቤት በመሄድ ከመቀስቀስ አልፈው ወደ ማስፈራራት ደረጃ መድረሳቸውን የጠቀሱት ምንጮች፣ በተለይ እናቶችን በምርጫ ካልተመዘገባችሁ ከአሸባሪዎች ጎን እንደቆማችሁ ይቆጠራል  በማለት እያስፈራሩዋቸው ይገኛሉ።
ከሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ የመጣው እና ለምርጫ ቦርድ የደረሰው ሪፖርት አስደንጋጭ መሆኑ ከታወቀ በሁዋላ፣ የህዝብ ግንኙነቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ነዋሪዎች ፣ በምርጫው ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባይሆኑም የኢህአዴግ አባላት እንዲመዘገቡ እንደጠየቁዋቸው ካልተመዘገቡ ግን ችግር እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።
የመራጮች ምዝገባ ቀናት ከሳምንት በሁዋላ የሚጠናቀቅ ሲሆን ምርጫ ቦርድ ጊዜውን ያረዝማል ተብሎ ይጠበቃል። በምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት 28 ሚሊዮን ህዝብ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
33 የተቃዋሚ ድርጅቶች በምርጫው ላለመሳተፍ መወሰናቸው ይታወሳል። ተቃዋሚዎች መሰረታዊ የሚባሉት የመብት ጥያቄዎች በቅድሚያ ካልተመለሱ በምርጫው አንሳተፍም የሚል አቋም መያዛቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment