የአዲስ አበባና የአካባቢያዊ ምርጫን በተመለከተ ለደጋፊዎቹ ለማስረዳት የግማሽ ቀን ስብሰባ ለማድረግ አስተዳደሩን ጠይቆ ከመከልከሉም በተጨማሪ፣ አመራሮቹ ለደኅንነታቸው እንደሚያሰጋቸውና የሕግ ከለላ እንዲደረግላቸው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጻፈ፡፡
በፕሬዚዳንቱ አቶ ተሻለ ሰብሮ ተፈርሞ የወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ ፓርቲው በ2005 ዓ.ም. የአካባቢና የከተሞች ምርጫ ቅድመ ዝግጅትን በሚመለከት የአዲስ አበባ አባላቱንና ደጋፊዎቹን፣ በአዋጅ ቁጥር 662/2002 መንፈስ ለማስረዳትና በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የግማሽ ቀን ስብሰባ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህል መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ አስተዳደሩም አዳራሹ ነፃ መሆኑን ገልጾለታል፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ግን ለማስተናገድ የማይችል መሆኑን አስተዳደሩ በማስታወቁ፣ ስብሰባውን በኢራፓ ቢሮ ለማድረግ መገደዳቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው በራሱ ቢሮ ስብሰባውን ከማድረጉ በፊት በሌሎች ቦታዎች አዳራሽ ለመከራየት ያደረገው ጥረት ‹‹ከስብሰባ ፈቃድ ሰጭ አካል ፈቃድ ይዛችሁ ኑ›› በመባሉ እንዳልተሳካላቸው አቶ ተሻለ ገልጸዋል፡፡ የተለመደውን የቅብብሎሽ ታክቲክ በመጠቀም ለሕገ መንግሥታዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታና ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጭ ጤናማ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ማድረጋቸው አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ኢራፓ ሰባት የአመራር አባላት የሚገኙበት በአዲስ አበባ ኮሚቴ እንደ አዲስ መልክ ማደራጀቱን፣ መዋቅሩን ከክፍላተ ከተሞች እስከ ወረዳዎች የመዘርጋቱ ክንውኖች እንዲፋጠኑ መወሰኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፣ በምርጫ ሥነ ምግባሩ አዋጅ 662/2002 እና የአካባቢ ምርጫ 2005 በተመለከተ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥራቸውን እንዳያከናውኑ፣ የስብሰባ ፈቃድ ለማግኘትና ስብሰባ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት በአንዳንድ የድርጅት ኃላፊዎች አማካይነት ውስጥ ለውስጥ ጫናዎች እንደሚደረጉባቸው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ድርጊቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነና በሕገ መንግሥቱ የተፈቀዱትን የመደራጀት የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ የእኩልነት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው የማይከበር ከሆነና ሌሎች የምርጫና የሥነ ምግባር አዋጆች የሚፈቅዱት የማይተገበሩላቸው ከሆነ በምርጫው እንደማይሳተፉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ደኅንነታቸው በአገሪቱ ሕግ መሠረት ከለላና ጥበቃ የሚያስፈልገው መሆኑን አቶ ተሻለ በደብዳቤው አክለዋል፡፡
www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment