ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በ12ኛው ክፍለ ዘመን ከአለት ተፈልፍለው የተሠሩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ
የመሰንጠቅ አደጋ ላይ መሆናቸውንና አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኙም ሊፈርሱ እንደሚችሉ
ቅርሶችን የተመለከተው የፓርላማ
ቡድን ማመልከቱን ሪፖርተር
ዘገበ።
የቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ ጐለጐታ፣
ቤተ መርቆርዮስና ቤተ ደናግል አብያተ ክርስቲያናት
በከፍተኛ ደረጃ መጎዳታቸው
ተገልጿል። ታሪካዊዎቹ ህንጻዎች
እየተሰነጠቁ መሆናቸውም በዘገባው
ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ተቋማቸው
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ
መሆኑን፣ አብያተ ቤተ ክርስቲያናቱ የተሠሩት ከአለት ተፈልፍለው በመሆኑ እንደሌሎቹ
ዓይነቶች ቅርሶች በቀላሉ ጥገና በማድረግ የገጠማቸውን
የመሰንጠቅ አደጋ ለማቆም በአገር ውስጥ ባለው የአቅም ደረጃ የሚቻል አለመሆኑን ገልጸው ፣ ችግሩን መፍትሔም ሊያጣ የሚችልበት
ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል
አካባቢውን ተዘዋውሮ ለተመለከተው
የፓርላማ አባላት ቡድን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ በዚህ መሰል ቅርሶች ጥገና ላይ ልምድ ካለውና ከጣሊያን
ወደ አገሩ ተቆራርጦ
የገባውን የአክሱም ሐውልት በማያያዝ በአክሱም የተከለው
ድርጅት፣ በላሊበላ ቅርሶች ላይ የተፈጠረውን ችግር በመመርመር መፍትሔ እንዲያመጣ
ሀላፊነት መሰጠቱን ባለስልጣኑ
ተናግረዋል።
በላሊበላ ቅርሶች ላይ የታየው አደጋ የቆየ ቢሆንም መንግስት እስካሁን በቂ ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።
የአካባቢው ባለስልጣናት የአለም ህዝብ ቅርሶችን እንዲታደጋቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ታዋቂ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያ ለኢሳት እንደገለጡት
የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም
በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ
የኢትዮጵያ ቅርሶች በሰበብ አስባቡ ሲወድሙ ዝም ብሎ መመልከት እንደሌለበት
ገልጸዋል። ጉዳዩን ከመንግስት
ይልቅ በአገሪቱ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ፋውንዴሽን
በማቋቋም ቅርሶቹ እንዲጠገኑ
ሀላፊነት ቢወስዱ የተሻለ መሆኑንም ግለሰቡ መክረዋል።
No comments:
Post a Comment