FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, January 17, 2013

የጣመ ውይይት


በአቶ ጋሻው አለሙ ተጀምሮ የምናደርገው ውይይት (አንዱ ዓለም ተፈራ)
ከዝግጅት ክፍሉ፤
አቶ ጋሻው ዓለሙ ጀምረውት አቶ አንዱ አለም ተፈራ የቀጠሉትና በማስከተልም አቶ ጋሻው ምላሽ የሰጡበት ውይይት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አቶ ጋሻው ለሰጡት ምላሽ አቶ አንዱ አለም አጸፋውን በሚከተለው መንገድ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ አቶ አንዱ አለም እንደጠቀሱት እኛም አዘጋጆቹ ይህ ውይይት አገራዊ እንደመሆኑ ሌሎቻችሁም የምትሉት ቢኖር የበለጠ ውይይቱ ያዳብረዋል፤ ያሰፋዋል እንዲሁም ፖለቲከኞቻችን ትምህርት ሊወስዱ የሚችሉበትን ሃሳብ ሊያገኙበት ይሆናል፡፡ የበርካታዎች መሳተፍ ጥቅሙ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባለመሆኑ ሌሎቻችሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላችሁን ሃሳብ፤ አስተያየት፤ ድጋፍ እንዲሁም ተቃውሞ በሠለጠነ መልኩ በማቅረብ ውይይቱን እንድታሰፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ለአቶ ጋሻውና ለአቶ አንዱ አለም እጅግ የከበረ ምስጋናችን ይድረሳቸው፡፡
የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች ተቋማዊ ድክመት ወይስ የራዕይና ስትራተጂ ልዩነት?
በአቶ ጋሻው አለሙ ተጀምሮ የምናደርገው ውይይት
ዋናው ቁም ነገር ከሁለታችን ውጪ፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ቢሳተፉበትና ሀገራዊ ስፋት ብንሠጠው ነውና፤ እባካችሁ ተሳተፉ። ሁለታችን ብቻ የጉዳዩ ባለቤቶች እንዳልሆንን ሁላችሁ ታውቃላችሁ። አቶ ጋሻው አለሙ የሚጥሩት፤ ጥሩ ነጥቦች በማራመድ፤ በተለይም የነገዋ ኢትዮጵያ ትክክለኛ ሥርዓት ኖሯት፤ ሰላምና ልማት እንዲከተል በማሰብ መሆኑን አጥብቄ ተረድቻለሁ። እኔም ይኼው ምኞቴ ስለሆነ፤ ባንድነት የምንሄድበትን መንገድ ለማግኘት ነው አቀራረቤ።
ሁለታችንም የተግባባንባቸውን ትቼ፤ አቶ ጋሻው አለሙና እኔ አንድ ያልተግባባንበትና አንድ የተለያየንበት ነጥብ ጎልቶ ታይቶኛል። በርግጥ ሌሎች ካሉና ከዘለልኳቸው አቶ ጋሻው እንደሚያስታውሱኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ያልተግባባንበት ያልኩትን፤ በደንብ ልትገልፀው ይገባል እንዳሉኝ አድርጌ እወስደውና አብራራለሁ። የተለያየንበትን ደግሞ ማስረገጫዬን በማቅረብ ነጥቤን አሰምራለሁ።
ያልተግባባንበት ጉዳይ፤ ሁለታችንም አንድ ነገር እያልን፤ መደማመጡ ላይ ትንሽ የተራራቅን በመሆናችን ብቻ ነው። ይኼን እንዲያስረዳልኝ፤ እስኪ ከአቶ ጋሻው አለሙ ጽሑፍ ትንሽ ጠቅሼ ላስቀምጥ፤
“እንደኔ እስካሁን ድረስ ከገመገምኳቸው 13 የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም አንጻር ስመለከተው መሰባሰብ ያለብን በሃሳብ ዙሪያ ነው ባይ ነኝ።”. . . . . ቀጥለውም፤ . . . . . “ስለዚህ፣ በተቃውሞ ፖለቲካ ልሂቃኖች መካከል ያለውን ግለሰባዊ ቁርሾ ወደ ጎን አድርገን፣ ትልቁን ሃገራዊውን ምስል ተመልክተን፣ አንድ በሚያደርጉን ሃሳቦች ዙሪያ ተደራጅተን በሂደት ልዩነታችንን በማጥበብ፣ የተቃውሞ ሂደቱን ተቋማዊ አድርገን፣ ጠንካራ፣ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበትን አደረጃጀትና አሰራር ዘርግተን ተቃውሞውን መምራት መቻል አለበን።”
አቶ ጋሻው አለሙ፤ አመሰግናለሁ። እኔም እኮ፤ መሰባሰቢያ የሚሆነንን ሃሳብ ነው በአምስት ነጥቦች ያሠፈርኩት። ይህ የአምስት ነጥቦች ሃሳብ እኮ ነው ትልቁ ሀገራዊ ምስል፣ አንድ የሚያደርጉን ሃሳቦች በማለት ያሠፈሩት። መለስ ብዬ ጠለቅ ያለ ትንተና ልስጥ። አምስቱን ነጥቦች አስመልክቶ፤ አቶ ጋሻው ሲጀምሩ፤
“የኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቆምና አንድ ሀገር ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ መያያዝ ያለበት፤ ከግዛት አንድነት ጋር ብቻ ሳይሆን የመንፈስና የህዝቦች አንድነት ጋር ጭምር መሆን ይገባዋል::” ብለዋል።
እስኪ እኔ ያልኩትን ልድገም። በአንድ ቁጥር አንድ ሕዝብ መሆናችንን መቀበል፣ በሁለት ቁጥር አንድ ሀገር እንዳለን መቀበል አስፍሬያለሁ።
እንዲህ አድርጌ፤
፩ኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንድነት በተመለከተ፤ አንድ ሕዝብ ነን ወይንስ አይደለንም?
፪ኛ፤ ሀገራችንን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያ፤ የቆዳ ስፋቷና ክልሏ ተጠብቆላት፤ አንድ ሀገር ናት ወይንስ አይደለችም?
እሳቸው በሶስተኛነት ያስቀመጡት የመንፈስ አንድነት ተደጋጋሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የሕዝቡን አንድነትና የሀገሪቱን አንድነት የተቀበለ፤ የመንፈስ አንድነቱ መደረት ካልሆነ የሚጨምረው አዲስ እውነታ አይታይኝም። መንፈሱ ለኔ፤ የሀገሪቱንና የሕዝቡን አንድነት መቀበል ነውና። ታዲያ ያላልኩት ምን ቀረ? ሁለታችንም አንድ ነገር ነው ያልነው ብዬ አልፈዋለሁ።
እዚህ ላይ አቶ ጋሻው አለሙ ሊያሠምሩበት የፈለጉት፤ “ስለዚህ በመሰረታዊነት በተቃውሞ ኃይሎችና ልሂቃን መታየት ያለበት ጉዳይ እኛ አንድ ህዝብ ነን ወይ የሚለው አስተሳሰብ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት በምን ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት የሚለውን ነው።”
በጣም ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ፤ “በምን ላይ ነው የተመሠረተ” የሚለውን የአንድነት ጉዳይ ለመነጋገር፤ መጀመሪያ አንድነት የሚለውን መቀበሉ አይቀድምም ወይ? አንድነት ብለን ለመነጋገር፤ አንድነት መኖሩን መቀበል ግዴታ ነው።
ቀጥለውም፤ “የህዝቦች አንድነት መገለጽ ያለበት ትላንት በተደረጉ ድርጊቶች ብቻ ሳይሆን በነገ የጋራ ተስፋዎች ጭምር መሆን ይገባዋልና ነው።” ብለዋል። ታዲያ ይኼንን ለማድረግ፤ መጀመሪያ ባንድ ላይ መቀመጥና ለነገ የጋራ ተስፋችን ባንድ ላይ እንነጋገር፣ እንንደፍ፣ አንድ ነን መባባልን አይጠይቅም ወይ? ታዲያ ይኼ ቅድመ ሁኔታውን፤ አንድነት አለን ማስበል ግድ አይልም ወይ? ልቀጥል። በነገራችን ላይ፤ የአሜሪካ ሕዝብ አንድ ነው። የሕገ መንግሥታቸው መንደርደሪያ የሚጀምረው፤ “እኛ የአሜሪካ ሕዝብ . . . ” በማለት ነው።
እንግዲህ መሠረታዊ ለውጥ ማለት፤ ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ነጥቦች ቀጥለው የሠፈሩት ሶስት ነጥቦች ናቸው። አንዱ አቶ ጋሻው አለሙ እንዳሉት በስልጣን ለይ ያለውን ኃይል ከሥልጣን ማውረድ ነው። ይኼ ደግሞ በቀጥር አምስት ሠፍሯል።
፭ኛ፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በተመለከተ፤ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ጠላት ዘረኛው አምባገነን የወያኔ አስተዳደር ነው። ይህ መንግሥት ሊታረም የማይፈልግና የማይችል ነው። ይህ መንግሥት መወገድ አለበት ወይስ የለበትም? መሠረታዊና ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ያሉትን ደግሞ፤ በቁጥር ሶስትና አራት ሠፍሯል። የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት ናቸው።
፫ኛ፤ የዴሞክራሲያዊ መብትን በተመለከተ፤ እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት፤ የግለሰብ መብቷ ተከብሮላት፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ሠርታ የመጠቀም፣ መኖሪያ የማበጀት፣ ሀብት የማፍራት፣ በኢትዮጵያዊነቷ (ከሃይማኖትና የዘር ትውልድ ባልተዛመደና ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በማያገልል መንገድ) ከመሰል የአስተሳሰብ አንድነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ጋር የፖለቲካ ተሳትፎዋን ማድረግ የምትችልበት እንድትሆን ነው ወይ ትግሉ?
፬ኛ፤ የሕግ የበላይነትን በተመለከተ፤ ከግለሰቦችና ድርጅቶች ውጪ፤ በሕገ ደንብና አሠራር ለመገዛትና ለመተማመን ነው ወይ የምንታገለው?
ይኼንን ያልተግባባንበትን ጉዳይ፤ ይኼ ግልፅ ያደርገዋል ብዬ ልለፈው፤ ምክንያቱም ሁለታችንም የምንለው አንድ ነውና። በነዚህ አምስት ነጥቦች ላይ አንድ ነን ብለው በግልፅ፤ አቶ ጋሻው እንዳሉት፤ የሚስማሙት ድርጅቶች በሙሉ ቃላቸውን ካሠፈሩ፤ አብሯቸው ያለው ክፍል ሊጠይቃቸው መንገድ ከፈቱ ማለት ነው። ድክመት አላቸው ማለትም እንችላለን፤ መስፈሪያ አለንና! ታዲያ እኔ እኮ ያልኩት፤ እስኪ በመጀመሪያ በነዚህ አምስት ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ እንድረስ ነው። ተግባብተናል መስሎኛል። ወደ ልዩነታችን አመራለሁ።
አቶ ጋሻው እንዲህ ይላሉ፤
“IV. ከላይ የተጠቀሱትን አላማዎች ለማሳካት ከምንም በላይ ሰላማዊ የትግል ስልት መከተል አስፈላጊና ተገቢ ነው። . . .” ይቀጥሉና ደግሞ . . . “ሌላው ቁም ነገር እስካሁን እኔ እስካለኝ መረጃ ድረስ በትጥቅ ትግል ስልጣን የተቆናጠጡና ዴሞክራሲዊ ስርአትን ያሰፈኑ ኃይሎችን አላቅም። እንደማስበው ከሆነ ግን ይህ የሆነበት ምክንይት ጦርነት በራሱ ግቡ ሁሉንም አሸናፊ የማያረግና ከጦርነት በኃላ እነርሱ ( ጠላት ) እና እኛ የሚል አስተሳሰብ የሚያሰፍን በመሆኑ ነው። ይህም ጸረ- ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲያብብ እድል የሚከፍት ነው።”
ቅሬታዬን በግልፅ ላስቀምጥ። አቶ ጋሻው ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የተገሉትን አስመልክተው እንዲህ ባሉት ላይ፤ “ከፍተኛው የቀኝ ግዛት አስተዳደር ስልጣኖች ለቀኝ ገዢዎቻቸው የተተወ በመሆኑ የስልጣን መሰላሉ ላይ ወደ ላይኛው እርከን ማደግ ባለመቻላቸው ቅር የተሰኙ ሰዎች ናቸው።” ይህ አባባል፤ ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነፃ ለመውጣት ያደረጉትን ትግል የሚያንኳስስ ሆኖ ስላገኘሁት ቅሬታ ተሰምቶኛል። በዕርግጥ አቶ ጋሻው በኋላ የሰዎችን ምግባር ተመልክተው የሠጡት መደምደሚያ እንደሆነ እረዳለሁ፤ ቢሆንም ግን በዚህ መልኩ ይኼ መቀንቀን የለበትም።
በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪቃን ትግል አስመልክቶ እንዲህ ሲሉ አስቀምጠዉታል።
“በሌላ በኩል፣ ጋናን እና ደቡብ አፍሪካን እንዲሁም ዛሬ የተሻለ ዴሞክራሲ አለባቸው የሚባሉ ሃገሮችን የሚመለከት ሰው የሚገነዘበው ነገር ቢኖር ከአንባገነንና ከአፓርታይድ ስርአት ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ያመሩበት መንገድ ስላማዊ ትግል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። ስለዚህም የዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማስፈን የሚደረግ ትግል ከጸረ-ቀኝ ግዛት ትግል ጋር ማመሳሰሉ በጣም አስቸጋሪ ነው:።” በመጀመሪያ ደረጃ የደቡብ አፍሪቃን ነፃነት ከአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ ለይቶ ማስቀመጥ፤ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስን ከኡምክሆንቶ ዊ ሲዚዌ ( Umkhonto we Sizwe – Spear of the Nation) ለይቶ ማየት አይቻልም። የዚህ የኡምክሆንቶ ዊ ሲዚዌ አቅምና ድርጊት ለአፓርታይድ ውድመት ምን ያህል አስተዋፅዖ እንዳደረገ ያጠና፤ የትጥቅ ትግልን ሚና ሊዘነጋ አይችልም። የደቡብ አፍሪቃዊያን ነፃነት በሰላምም ሆነ በውጭ ሀገሮች ተዐቅቦ የተገኘ አይደለም። የቮርስተር መንገስት ሲወጠር የመጨረሻ ምርጫው ሆኖ ስላገኘው ነው።
በርግጥ ከአቶ ጋሻው አለሙ ጋር የምስማማው፤ ይኼ የደቡብ አፍሪቃ ትግል ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የተደረገ ትግል ነው። ለኔ ደግሞ፤ ከአምባገነኖች ጋር የሚደረገው ትግል፤ በሕዝቡና በአምባገነኖች፤ በግልፅ በሁለት መከፈልና ትግሉ መፋፋም አለበት። እዚህ ላይ ላጠብቀው የምፈልገው፤ በምንም ሰዓት ቢሆን፤ ሰላማዊ ትግል ቀደምተኛና የማያቋርጥ መሆን እንዳለበት ነው። በቅኝ ግዛትም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት የሚደረግ ትግል፤ አይለወጤው ስልት ሰላማዊ ትግሉ ነው። የትጥቅ ትግሉ የሚቀነቀነው፤ በገዢዎችና በሕዝቡ መካከል ያለው ቅራኔ ተካሮ፤ የአጥፊና ጠፊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው። የቅኝ ግዛትም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ፈላጊዎች ትግል፤ ተካሮ የመጨረሻው ላይ ሲደርስ፤ ያን ደረጃ ላይ፤ የሕዝቡን ታጥቆ መነሣት ግድ ይላል። እንዴት መታጠቅና መነሣት እንዳለበት፣ ስለ አመራሩና ስለአካሄዱ፤ ከሰላማዊ ትግሉ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት፤ የያንዳንዱ ትግል የራሱ የሆነ መንገድ ይኖረዋል። እዚህ ላይ እኛ የመንወያየው በሃሳብ ደረጃ ነው። በሃሳብ ደረጃ ደግሞ፤ ሌላ ቦታ ተሳካም አልተሳካም፤ በትክክል ተካሄደም አልተካሄደም፤ አማራጭነቱ አይሰረዝም። በርግጥ እንዴት መሆን አለበት? የሚለውን ጉዳይ በሌላ ጊዜ መነጋገር እንችላለን፤ እዚህ ላይ ላሠምረው የምፈልገው፤ አማራጭነቱ መሠረዝ የሌለበት ግዴታ ነው ብዬ ነው።
የሌሎች የትጥቅ ትግሎችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማስገኘትን ወይንም አለማስገኘትን ጉዳይ ወደ ኋላ እንተውና፤ ለምን የትጥቅ አስፈላጊ ነው በሚለው ላይ ሃሳቤን ልሰንዝር። የገዥው ክፍል በሕግና ደንብ የሚመራና፤ ራሱ የሚያወጣቸውንና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚያከብር ሆኖ ሲገኝ፤ ሰላማዊ ትግል አንደኛና ትክክለኛው መንገድ ነው። የተጣመሙና ለሱ የሚረዱ ቢሆኑም እንኳ፤ ሕዝቡ የገዥው ክፍል ራሱ ባወጣቸው ሕጎች ተገዝቶ አቸናፊ ይሆናል። ማኅተመ ጋንዲ እንግሊዞችን ሊያንበረክኩ የቻሉት፤ እንግሊዞቹ የማይደፍሯቸው መሠረታዊ ሕጎች ስለነበሩዋቸው ነው። በሌላ በኩል፤ አምባገነኖች ባሉበት ቦታ፣ ሕግ ትርጉም በሌለው ቦታ፣ ገዥው ክፍል በፈለገው መንገድና ሰዓት ሕጎቹን የሚቀያይርና የማያከብር በሆነበት ቦታ፤ ሰላማዊ ትግሉ ከሮ አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ፤ ከሰላማዊ ትግሉ ጎን፤ ሕዝቡ ራሱን መከላከያ ማዘጋጀቱ ግዴታ ነው።
አንድ ሀቅ በግልፅ መቀመጥ አለበት። በሥልጣን ለይ ያለ ቡድን፤ ራሱን በቋሚ መንግሥትነት አስመስሎ፣ ራሱን በሀገሪቱ ሕልውና አስመስሎ፤ እኔን መንካት ሀገሪቱን መንካት ነው፣ እኔን መንካት የሀገሪቱን መንግሥት ሕልውና መንካት ነው ብሎ እስከመጨረሻው ሕዝቡን እየጨረሰ በሥልጣን ለመቆየት ከወሰነ፤ ያለ አማራጭ ይህ እኛና እነሱ የሚል ክልል ይፈጥራልና፤ ወይ መጥፋት ወይ ማጥፋት የዕለቱ ጨብጥ ሀቅ። እናም በዚህ ሰዓት፤ ሕዝቡ ትጥቅ ማንሳት ግዴታው ይሆናል – ሕልውናውን ለመጠበቅ። ይኼን ካላደረገ፤ ሕዝቡ ጠፊ ይሆናል ማለት ነው። ይኼን የመሰለ ቡድን፤ የትግሉን ምንነት ይቀይረዋል። ከቅኝ ገዥዎች ያልተለዬ ነው። በመሆኑም፤ ትግሉ ራሱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመሆኑ አልፎ፤ የነፃነት ጥያቄ ይሆናል። የነፃነት ጥያቄ ደግሞ በልመና አይፈታም። አሁንም፤ የነፃነት ጥያቄ፤ የተለያዩ ቡድኖች በየራሳቸው የሚያደርጉት ትግል ከሆነ፤ ውጤቱ የጉልቻ መቀያየር ብቻ ይሆናል። ሀገራዊ አንድ ድርጅት አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው።
ይኼን ስል፤ በሀገራችን ሰላማዊ ትግሉ ተሟጦ አልቆለታል ወይንም የትጥቅ ትግሉን የሚያካሂድ ሕዝባዊ ክፍል አለ ከሚል እንዳልሆነ አንባቢ ይረዱልኝ። በኔ እምነት የትጥቅ ትግሉን በሕዝብ ስም ሊያካሂድ የተዘጋጀ ክፍል የለም። ሰላማዊ ትግሉ የትጥቅ ትግል አጋር እያስፈለገው መምጣቱን ግን እቀበላለሁ። ችግራችን ግን፤ ሰላማዊ ትግሉንም በትክክል የሚመራ የሕዝብ የሆነ አንድ አጠቃላይ ማዕከል የለንም። ይኼ በሌለበት የትጥቅ ትግሉን የሚመራ ክፍል ማግኘት ምኞት ነው። አስፈላጊነቱ ግን ጊዜው ነው።
አንዱ ዓለም ተፈራ
ጥር ፮ ቀን ፳፻፭ ዓመተ ምህረት

No comments:

Post a Comment