- ቤቶቹ ከቤተ መድኃኔዓለም እና ቤተ ዐማኑኤል አጠገብ የተሠሩ ነበሩ
- በልደት ክብረ በዓል የቱሪስቶች ቁጥር መቀነሱ ኅብረተሰቡን አስደንግጧል
በቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም ከዐሥራ አንዱ ውቅር አብያተ መቅደስ ጋር በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት ጥንታውያን ቤቶች በእሳት ቃጠሎ መውደማቸው ተገለጸ፡፡ ባለፈው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ መንሥኤው ባልታወቀ ምክንያት በተነሣው የእሳት ቃጠሎ የወደሙት አራት ቤቶች የሣር ክዳን ያላቸው ፎቅ ቤቶች ሲኾኑ፣ የላሊበላን ጥንታዊ የቤቶች አሠራር የሚያሳዩ በመኾናቸው እየተጠገኑ እንዲጠበቁ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ በቃጠሎው የወደሙት ጥንታውያኑ ቤቶች፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርቶች መካከል በቅኔና ዜማ ትምህርት መስጫነት ሲያገለግሉ እንደቆዩ ተገልጧል፡፡ ገኛ ቦታቸውም ከዐሥራ አንዱ አብያተ መቅደስ መካከል በታላቁ ቤተ መድኃኔዓለም እና በቤተ ዐማኑኤል አጠገብ ከ20 – 30 ሜትር ርቀት ላይ መኾኑ፣ የገዳሙ አስተዳደር ጽ/ቤት ለቅርሶቹ ደኅንነት ትኩረት ሰጥቶ በቂ ጥበቃና ክብካቤ እንደማያደርግ በካህናቱ እና ምእመናኑ የሚነሡበትን ስጋቶችና ተቃውሞዎች ያጠናከረ ነው ተብሏል፡፡ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት÷ የቃጠሎ አደጋው በደረሰበት ዕለት ሌሊት በሁለቱም አብያተ መቅደስ አካባቢ የገዳሙ ጥበቃ አባላት አልነበሩም፡፡
ከሙስና እና ብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ ጥያቄ የሚነሣባቸውና ላለፉት ስምንት ዓመታት በአስተዳዳሪነት የቆዩት የገዳሙ መምህርም ቃጠሎው በደረሰበት ስፍራ የተገኙት ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ቤቶቹ ሰው በማይኖርበትና ‹‹ኮር ዞን›› ተብሎ በዩኔስኮ በሚታወቀው ለቅርሶች የተለየ ስፍራ የሚገኙ ኾነው ሳለ የተከሠተው ይኸው አደጋ፣ ‹‹በአስተዳደሩ ላይ እየተጠናከሩ የመጡትን ተቃውሞዎች ትኩረት ለማስቀየስ የተፈጠረ›› አድርገው እንደሚወስዱት የስፍራው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅ/ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም በአንድ ጊዜ በተደረገው የ160 በመቶ የቱሪስቶች ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ ዘንድሮ በተከበረው የልደተ ክርስቶስ (ቤዛ ኵሉ) እና ጥምቀት በዓላት ላይ የተገኙት የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት ቀንሶ መስተዋሉን የዜናው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የቱሪዝሙ ባለድርሻ አካላት በበቂ ባልመከሩበት ኹኔታ በአንድ ወገን ውሳኔ ገቢን ከፍ ለማድረግ ብቻ ታስቦ ከጥር አንድ ቀን ጀምሮ በተፈጸመው በዚሁ ጭማሪ ብር 350 የነበረው የቱሪስት መግቢያ ብር 1000 እንዲኾን ተደርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት የጥምቀት በዓል ብቻ ከአንድ ሺሕ በላይ የውጭ ቱሪስቶች መገኘታቸውን ያስታወሱት ምንጮቹ፣ በዚህ ዓመት ግን ለቱሪስቱ አስቀድሞ ከተገለጸለት የመግቢያ ዋጋ በተለየና በራቀ አኳኋን ጭማሪ በመደረጉ ምክንያት ቁጥሩ በግማሽ አንሶ መገኘቱን ገልጸዋል፡ ፡ በተለይም ያለቱር ኦፕሬተርስ በግላቸው ለጉብኝት የመጡ ቱሪስቶች ከስፍራው ከደረሱ በኋላ በናረው የመግቢያ ዋጋ ምክንያት ውቅር አብያተ መቅደሱን ሳይጎበኙ የተመለሱ እንዳሉ፣ ከእኒህም መካከል ላሊበላን መጎብኘት አዳጋች መኾኑን ለሚዲያዎች ሐሳብ የሰጡ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡
የቱሪስት ፍሰት መቀነሱ በዋናነት የላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ ያለውን የቱሪስት መስሕብነት ማእከል በማድረግ የተመሠረተውን የአስተዳደሩን የልማት እንቅስቃሴና የኅብረተሰቡን ኑሮ ይጎዳል ያሉት ምንጮቹ፣ በከተማው ነዋሪ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩንም ለዝግጅት ክፍሉ አስረድተዋል፡፡ በልማትና በቅርስ ሀብቱ ተጠቃሚ ከመኾን አኳያ አካባቢው ‹‹ዕድለ ቢስ ነው›› የሚሉት የከተማው ነዋሪዎች፤ ከተማውን ከሌሎች ከተሞች ጋር ከሚያገናኙ መንገዶች አንሥቶ የተሟላ የሆስፒታል መገልገያ ዕቃዎችና የሕክምና ባለሞያዎች ያላገኘውና አገሪቱን በቱሪዝም ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለው ላሊበላ:- ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚያሰማው ጩኽት ሰሚ ያጣ የቁራ ጩኸት እንዳይኾን በድጋሚ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment