FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, January 18, 2013

በውጪ ያለው ሲኖዶስ በአገር ውስጥ የሚደረግን የፓትርያርክ ምርጫ አወገዘ


ጥር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እርቀ-ሰላሙ ያልተሳካውም ሆነ የፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው የመመለስ ጉዳይ ተቀባይነት ያላገኘው ቤተ-ክርስቲያንን ለማጥፋት ቆርጦ በተነሳው ኢህአዴግ የተባለ ሀይል ምክንያት ነው ሲል በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ አስታውቋል።
“ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ”በሚል ርዕስ በስደት ያለው ሲኖዶስ ባወጣው ባለ 7 ገጽ መግለጫ ላይ፤ አራተኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ በከፍተኛ ባለስልጣናትና ትዕዛዝ በወታደሮች ተገደው እንዴት ከቦታቸው እንዲነሱ እንደተደረጉ በስፋትና በጥልቀት አብራርቷል።
ሀቁ ይህ በሆነበት ሁኔታ የአገር ቤቱ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አራተኛው ፓትርያርክ፦”ስላመመኝ ስልጣኔን ተረከቡኝ ብለዋል" ማለቱ ፈጽሞ ውሸት መሆኑን ያመለከተው በስደት ያለው ሲኖዶስ፤አንዲትም የድምጽ ፣ የወረቀትም ሆነ የምስል ማስረጃ ማቅረብ በማይቻልበት ሁኔታ ህዝብን በሀሰት ማደናገሩ አግባብ እንዳልሆነ መክሯል።
የ አዲስ አበባዎቹ አባቶች፦"ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን አራተኛው ፓትርያርክ በራሳቸው አንደበት ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ያደረገበት ምክንያት የራሱ የሆነ ምስጢር ይኖረዋል"ማለታቸውን ያወሳው በስደት ያለው ሲኖዶስ፤ ምስጢሩ ምንም እንኳን ለ እውነተኛዋ የቤተክርስቲያን ልጆች ግልጥ ቢሆንም እንደገና እንገልጠዋለን" በማለት  ፓትርያርኩ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ታምራት ላይኔ ትዕዛዝ እንዴት በግፍ ከመንበራቸው ተገፍተው እንደወረዱ፣ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ደብዳቤ ጽፈው ተቀባይነት እንዳላገኙ፣ ከዚያ በማስከተል ቀናኖ ቤተ-ክርስቲያን ተጥሶ አቡነ ጳውሎስ እንዴት እንደተመረጡ እና እርሳቸው በእንጦጦ ቤተክርስቲያን እንዴት በናይሮቢ በኩል እንደተሰደዱ በስፋት አብራርቷል።
ከሁሉም በላይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቁርጥ ቀን ልጆችን ከዳር በተስፋ ያነሳሳው የእርቀ-ሰላም ሂደት ለመጨናገፉ ዋነኛ ተጠያቂዎቹ የአዲስ አበባዎቹ አባቶች መሆናቸውን የገለጠው በስደት ያለው ሲኖዶስ፤ የእርቁ ሂደት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በስደት ያለው ሲኖዶስ እና ከአዲስ አበባ ተወክለው የመጡት ልዑካን  ድርድሩ እንዲሳካ በሙሉ ፍላጎትና ትጋት ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም የአዲስ አበባዎቹ አባቶች ሰሞኑን ያወጡት መግለጫ አሳዛኝ ሆኗል ብሏል።
ከአዲስ አበባ የተወከለው ተደራዳሪ ልዑክ እንደ መደራደሪያ ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ፦”በታሪክ አጋጣሚ የተከሰተውን የቀኖና ችግር ለማስተካከል የሁለቱም ፓትርያርኮች መዋዕለ ዘመን እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን በህይወት ያሉት ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው በክብር ተመልሰው መዋዕለ ዘመናቸውን ይፈጽሙ"የሚል እንደሚገኝበት ያወሳው የህጋዊው ሲኖዶስ መግለጫ፤"አሁን ግን ከ አዲስ አበባ በወጣው መግለጫ ላይ “ አምስት ብለን አራት አንልም የሚል”የቁጥር ጨዋታ ውስጥ መገባቱን አመልክቷል።
መግለጫው በማያያዝም፤የአገር ቤቶቹ አባቶች እየተከተሉት ያለው ሰፊውን ምዕመን ያሳዘነ አሠራር፤ ከቀኖና እና ከህገ ቤተክርስቲያን አኳያም ከመጀመሪያው አንስቶ እስካሁን ድረስ ስህተት እንደሆነ የነ ቅዱስ አትናቴዎስን፣የነ  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እና የነ ቅዱስ ዲዮስቆርዮስን ህይወት ዋቢ በማድረግ በስፋት አስረድቷል።
"ይህ ሁሉ የሆነው ለምንድነው ብለን ስንጠይቅ የወያኔ-ኢህአዴግን አመራር ለማስፈጸም በገሀድ የፓርቲው አባላት የሆኑና ፦"እኛ ብንሾምስ "ብለው ደፋ ቀና የሚሉ ከአምስት ያልበለጡ ጳጳሳት ከመጀመሪያው አንስቶ እርቀ-ሰላሙን በመቃወማቸው ነው ብሏል-ህጋዊው ሲኖዶስ።
እነዚህ ነጥቦች የሚያረጋግጡት አቢይ ጉዳይ ደግሞ ቀደም ሲል ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መፋለስ ምክንያት የሆነውና ቅዱስ ፓትርያርኩን በግፍ ከመንበራቸው ያሳደዳቸው ሀይል፤አሁንም ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋትና ትውልዱንም ከመንፈሳዊ ህይወቱ ለማዳከም ቆርጦ በመነሳቱ ነው ሲልም ሲኖዶሱ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ላይ እየሆነ ላለው ነገር ገዥውን ፓርቲ ዋነኛ ተጠያቂ አድርጓል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የ ኢትዮጵያ ፓትርያርክ እስከሆኑ ድረስ ይህን እውነት በመሰረዝ እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ የሚደረግን ማንኛውንም የሐዋርያዊ ወንበር ሽሚያ እንደማይቀበለውና እውቅና እንደማይሰጠው ያስታወቀው ሲኖዶሱ፤"ከዚህም በላይ በአባቶቻችን ቀኖና መሰረት ድርጊቱን አጥብቆ ያወግዛል” ብሏል።
እርቀ ሰላሙ እንዲሳካ ላለፉት ሶስት ዓመታት በራሳቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ለቆዩት የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ጥልቅ ምስጋናውን ያቀረበው ሲኖዶሱ፤አሁንም የ ቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ከአገር ጉዳይ ተለይቶ የማይታይ በመሆኑ ሀገርን የምትወዱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከሲኖዶሱ ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል።
የብዙሀንን ድምጽ በማፈን ሊካሄድ የታሰበው ህገ-ወጥ የፓትርያርክ ምርጫ ተገትቶ ለሰላሙ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ህጋዊው ሲኖዶስ በሩን ከፍቶ እጁን ዘርግቶ በማለት አጠቃሏል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው ሲኖዶስ የያዘውን አቋም በተመለከተ የተለያዩ የህዝብ አስተያየቶችን ማቅረባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment