በዘመናዊው የስፖርት ታሪካችን ውስጥ በእግር ኳስ ዓለም እንደ ትናንቱ አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት የሄድን አይመስለኝም፡፡ ለካስ እንችላለን፤ ለካስ ከሠራን የማንሆነው የለም፣ ለካስ ጥረት ካለ ለእኛ ያልተፈቀደ ነገር የለም፤ ለካስ ትብብር ካለ እንዳንወጣው የተከለከለ ተራራ፣ እንዳንሻገርም የታጠረ ገደል የለም፤ ለካስ ‹እችላለሁ› ብሎ ማሰብ ከተቻለ የማይቻል ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ብራዚል ስትጫወት፣ እንደ ጣልያን ስትከላከል፣ እንደ ስፔን ስታጠቃ ከማየት በላይ ምን መታደል አለ፡፡ ልጆቹ ከባርሴሎና ማሠልጠኛ የወጡ ናቸው እንዴ? የአፍሪካ ዋንጫ የተጀመረው ዛሬ ነው እንዴ? እያሉ እነ ቢቢሲና ሲኤንኤን፣ አልጄዚራና ሱፐር ስፖርት ውዳሴ ሲያዘንቡ መስማት መታደል ነው፡፡
ምርጥ ደራሲ ደርሶት፣ ምርጥ ዳይሬክተር አዘጋጅቶት፣ ምርጥ ተዋንያን እንደተወኑት ምርጥ ድራማ፤ የተጠና፣ የተቀናበረ፣ ምት ያለው፣ የተሠናሰለ፣ ምርጥ ጨዋታ ነበር ልጆቻችን ያሳዩን፡፡ በዚህኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያውን ቀይ ካርድ አይተን፣ በዐሥር ተጨዋች ተጫውተን፣ አስቀድሞ ግብ ገብቶብን በሙሉ መተማመንና፣ በኢትዮጵያዊ ወኔ መጨዋት፣ መረበሽን ተቋቁሞ ከመከላከል ወደ ማጥቃት መዞር፣ በራስ የግብ ክልል እንኳን ተረጋግቶ ኳስ መቀባበል፣ ይህ ነው መጀመርያ የተሸነፈው ቡድን፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሀገሩ ወጥቶ ሲጫወት ብዙዎቻችን የምንፈራው ብዙ ግብ አስተናግዶ እንዳይመጣ ነበር፡፡ ሽንፈቱ ቀለል ያለና አጥንት የሚሰብር እንዳይሆን ነበር፡፡ ዛሬ ይህ አስተሳሰብ ተሸንፏል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ መጀመርያ ያሸነፈው ዛምቢያን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያንን ነው፡፡ ‹ድብልቅልቃቸው ወጥቶ፣ ደርዘን ግብ አስተናግደው፣ የሌሎች የነጥብ መሰብሰቢያ ሆነው፣ አንገታችንን አስደፍተው ይመጣሉ፤ እኛ ሩጫ እንጂ እግር ኳስ አይሆነንም፤ እንዲያውም ሳናልፍ በቀረብን› የሚሉ የሀገር ቤት ቡድኖችን ነው ያሸነፉት፡፡ ሳላህዲን በዛምቢያ ላይ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ስቶታል፡፡ በደካማ አስተሳሰቦች ላይ፣ አይሆንም፣ አይሳካም፣ አይቻልም፣ የትም አንደርስም በሚሉ ቀድመው የሚሸነፉ ስሜቶች ላይ የመታውን ፍጹም ቅጣት ምት ግን በሚገባ አስቆጥሮታል፡፡
በጨዋታው አጋማሽና በጨዋታው መጨረሻ በዲኤስ ቲቪ ሱፐር ስፖርት ጨዋታውን ይተነትኑ የነበሩት ባለሞያዎች በኢትዮጵያውያኑ አጨዋወት፣ በራስ መተማመን፣ መናበብ፣ ታክቲክና ጥንካሬ ላይ አስደናቂ የሆኑ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነበር፡፡ ያውም ከብራዚል ጋር እያነጣጠሩ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይተላለፉ ከነበሩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በአንዱ የተገኙ አንድ የእግር ኳስ አሠልጣኝም ‹የእኔም ሥጋት ዛሬ ተቀርፏል›› ብለው ነበር የተናገሩት፡፡ ከዚህ በላይ ምን ድል አለ?
አስቀድሞ ሳላህዲን ሰኢዲ ፍጹም ቅጣት ምት ሲስት፣ በኋላም ኢትዮጵያዊው ግብ ጠባቂ በቀይ ሲወጣ የተከፈተው የተስፋ መስኮት ገርበብ ያለ መስሎ ነበር፡፡ በወቅቱ በፌስ ቡክ አስተያየታቸውን ይሰጡ የነበሩ ኢትዮጵያውያንም ‹‹አይይይ›› ‹‹ኡፍፍፍ›› ‹‹ውይይይ›› የሚሉ የንዴት፣ የተስፋ መቁረጥና የቁጭት ድምጾችን ያሰሙ ነበር፡፡ ልጆቹ ግን የነበረውን እንዳልነበረ፣ የተደረገውን እንዳልተደረገ ቆጥረው ግብ እንዳገባ ተጨዋች ነበር የሚጫወቱት፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያስመዘገበው አዲስ ድል ይህ ነው፡፡ ዳኛው በግብ ጠባቂው ላይ ቀይ ካርድ ቢመዙም፣ ተጨዋቾቹ ግን በመደናገጥና በመረበሽ፣ ተስፋ በመቁረጥና ከንግዲህ አለቀልን በሚለው ስሜት ላይ፣ ከፊሽካ በፊት በመሸነፍና ከፍጻሜው በፊት በመጨረስ ድክመት ላይ ነበር ቀይ ካርዳቸውን የመዘዙት፡፡
እውነታቸውን ነው ዓለም እንደሆነ ምንጊዜም አትሞላም፡፡ ‹‹ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ›› የሚሆነው ለማስታወቂያ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ጉዞ ሲሞላ ሲጎድል ነው፡፡ ታድያ ለምን ያለንን እንጂ የጎደለንን እናስባለን፡፡ ዓይን ላይኖረን ይችላል፤ ግን አእምሮ አለን፤ እጅ ላይኖረን ይችላል፤ ግን ዓይን አለን፤ ሥራ ላይኖረን ይችላል፤ መሥራት የሚችል ሙሉ ጤና ግን አለን፤ እናት ላይኖረን ይችላል፤ ከእናት የሚመረጥ አባት ግን አለን፤ አባት ላይኖረን ይችላል፤ እንደ አባት የሚከባከቡ ብዙ አጎቶች ግን አሉን፤ ውጤት ማምጣት ያለብን ስንሟላ ብቻ ነው እንዴ?
የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ‹ጎደሎ እንደሆንን አናስብ፡፡ በቤታችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በቢሯችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በትዳራችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በንግዳችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በሀገራችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በትምህርታችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በጤናችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በአካላችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ በፍላጎታችን ያልተሟላ ነገር አለ፡፡ ግን ለምን ጉድለታችንን ብቻ እናስበዋለን፡፡ ለምንስ መጉደላችንን ብቻ እየሰብን እንብሰከሰካለን፡፡ ለምንስ የወደፊቱን ላለፈው ነገር ስንል እንሠዋለን፡፡ ለምንስ ነገን በትናንት ምክንያት እናበላሸዋለን፡፡
ተጨዋቾቹ ምንድን ነው ያደረጉት? አንድ ተጨዋች ጎድሎብናል፡፡ አዎ፡፡ ልንተካው እንችላለንን? አንችልም፡፡ ታድያ ምን እናድርግ? ጎደሎውን በሌላ ነገር እናሟላው፤ በምን? ባለን ነገር ጎደሎውን እንሙላ፡፡ ምን አለን? ተናብቦ፣ ተገናዝቦ፣ ተሳስቦና ተረባርቦ የመጨዋት ችሎታ አለን፡፡ ሀገራዊ ወኔና፣ ኢትዮጵያዊ የማሸነፍ መንፈስ አለን፤ ስለዚህም ይህ ችሎታችን አሥራ አንደኛ ተጨዋች ሆኖ ይጫወታል፡፡ የጎደለን ነገር የለም፡፡ እኛ ሙሉ ነን፡፡ ጎደሎ አይደለንም፡፡ ይህ ነበር ውሳኔው፡፡ ይህ ነበር መርሑ፡፡
ጎደሎውን ባልጎደለው ነገር መሙላት እንጂ ጎደሎውን እኝኝ እያሉ ማሰብ ጉድለትን አያስቀረውም፡፡ የአንዳንዱ ጉድለት የሚታይ ነው፡፡ የሌላው ጉድለት ግን የማይታይ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሙሉ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን አንድ ተጨዋች ቢጎድለውም የዛምቢያ ቡድን ደግሞ ብዙ ነገር ይጎድለው ነበር፡፡ በአንድ ተጨዋች የማይሟላ ብዙ ጉድለት ነበረበት፡፡ እንዲያውም ትናንት ፍጹም ቅጣት ምቱ ባይሳት ኖሮ የዛምቢያ ቡድን ተሸናፊ ነበር፡፡ ለምን? ቢባል ከአንድ ተጨዋች የሚበልጥ ብዙ ጉድለት ነበረበት፡፡ የእነርሱ ጉድለት እንደኛ ስላልታየ፤ ስላልተቆጠረና በዳኛ ውሳኔ የተፈጸመ ስላልሆነ ነበር ልዩነቱ፡፡
በትናንትናው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያመጣንበት ትልቅ ድል ቢኖር ‹‹ጎደሎ ነን ብሎ በማሰብና በመጨነቅ›› ላይ የተቆጠረው ሦስት ነጥብ ነው፡፡ እንደዚያ የምንወዳቸውና የምንንሰፈሰፍላቸው ወላጆቻችን እንኳን ስንት ጉድለት አለባቸው፡፡ እንዲያ ነፍሳችንን የምንሰጥላቸው የአብራካችን ክፋይ፣ የማኅፀናችን ፍሬ የሆኑ ልጆቻችን እንኳን ስንት ጉድለት አለባቸው፡፡ እኛ ራሳችን ስንት ፈልገን ያላገኘነው፤ ጥረን ያልደረስንበት፣ አስበን ያልሆንነው፤ ታግለን ያልጨበጥነው ስንት ጉድለት አለብን፡፡ ግን ጎደሎነታችንን አናስብ፡፡ ያጣነውን ትተን ያገኘነውን እናስብ፤ የሌለንን ትተን ባለን እንጠቀም፤ ያልሆንነውን ትተን በሆንነው እንሥራበት፤ ያልደረስንበትን ትተን በደረስንበት እናፍራበት፡፡ የማይጎድል የለምና፡፡ የዚህ ዓለም ጉዞ አንዱን ጎደሎ እየሞሉ ሌላ ጎደሎ መፍጠር ነው፡፡
ደረጃችን የሚመጥን ጨዋታ ተጫውታችኋል፡፡ አንገታችን ቀና አድርገን እንድንሄድ አድርጋችኋል፡፡ ብዙ ነጥብ አስቆጥራችኋል፡፡ ስለ እናንተ በኩራት እንዲወራ አድርጋችኋል፡፡ ሌሎች ቡድኖች በአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች የሚጫወቱ ተጨዋቾች ይዘዋል፤ እናንተ የላችሁም፡፡ ግን ጎደሎአችሁን አታስቡ፡፡ ሌሎች ቡድኖች ብዙ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈዋል፤ እናንተ ከሠላሳ ዓመት በኋላ መጥታችኋል፤ ይህንን እንደ ጉድለት አታስቡት፤ ስለ ሌሎቹ ብዙ ይነገር ይሆናል፤ ይህንን እንደ ጉድለት አታስቡ፡፡ ሌሎች የሌላቸው፣ እናንተ ብቻ ያላችሁ ብዙ ነገር አለና ያንን አስቡት፡፡ ለጎደላችሁ ሳይሆን ላላችሁ ነገር ቦታ ስጡት፡፡ ደግሞም ይህ የአድዋ ጦርነት አይደለም፡፡ እግር ኳስ መሆኑንም አትርሱት፡፡ አንችልም፣ አይታሰብም የሚለውን ቡድን አሸንፋችሁ ‹‹የይቻላል ዋንጫ›› ካመጣችሁ እኛ በኩራት ጉሮ ወሸባዬ እያልን እንቀበላችኋለን፡፡ ‹ካፍ› ያልሰጣችሁን ዋንጫም እንሰጣችኋለን፡፡
መልካም ዕድል፡፡
No comments:
Post a Comment