FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, January 24, 2013

የዋልድባ መነኮሳት አቤቱታቸውን ለክልሉ መንግሥት አቀረቡ


ጥር ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ቤተ-ሚናስ ማኅበረ መነኮሳት አቤቱታቸውን ለአማራ  ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አቀረቡ።
የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ በደብዳቤ የዘረዘሩት መነኮሳቱ ፤መንግሥት በሰላማውያን መነኮሳት ላይ የሚደርሰውን እንግልት እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
የታሰሩ፣ የተንገላቱ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን መነኮሳትንም ዝርዝር አቅርበዋል።
"መብታችን እየተጣሰ ስለሆነ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድልን ስለመጠየቅ"በሚል ርዕስ ለክልሉ መንግስት ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጻፉት ሰፊ ደብዳቤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋልድባ የሚለውን ስም መጥራት ሁሉ የተለየ ይዘት እየተሰጠው  ይህን ስም የሚጠሩ መነኮሳት ሁሉ እየታሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
መንፈሳዊ ቦታ ማንም ያለ ዘር መድሎ የሚገለገልበት መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው ያሉት መነኮሳቱ፤ በቤተክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻህፍት የተፃፉትን ለጊዜው ትተን የሀራችንን ሕገ-መንግሥትና ሌሎች የመንግሥት ሕግጋትን ብንመለከት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት የሀገሪቱ አካባቢ የመኖርና መብቱ እንዲጠበቅለት የመጠየቅ ሰብዓዊ መብት እንዳለው ተደንግጓል ብለዋል።
ይሁንና የፀለምት ወረዳ አስተዳደርን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ለዘመናት አንድነቱ ተከብሮና የዘር መድልዎ ሳይደረግበት ማንኛውም መናኝ በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ብቻ ተመርምሮ ይኖርበት በነበረው ቦታ ግልጽ በሆነ መልኩ" የትግራይ ክልል ተወላጅ ካልሆናችሁ በዚህ ገዳም መኖር አትችሉም" በማለት በልዩ ልዩ መልክ ማኅበረ-መነኮሳቱን መከፋፈል ጀምረዋል ሲሉ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
ሹመኞቹ  ለዚህ ዓላማም በጣት የሚቆጠሩ መነኮሳትን፣ የአካባቢውን ታጣቂና የሚሊሻ ኃይል በመጠቀም ማኅበረ-መነኮሳቱን ለከባድ እንግልትና የመብት ጥሰት እየዳረጉን ይገኛሉ ያሉት መነኮሳቱ ደረሱብን ያሏቸውን የመብት ጥሰቶች በስፋት ዘርዝረዋል።
ተፈፅመውብናል ካሏቸው በደሎች መካከል የዘር መድሎ፣እስራትና ድብደባ እንደሚገኙበት ያመለከቱት መነኮሳቱ በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው ባለስጣናትና ታጣቂዎች የተደበደቡትን እና የታሰሩትን  መነኮሳት ከነተደበደቡበት እና ከነታሰሩበት  ቀን በዝርዝር አስፍረዋል።
ድብደባና የመብት ጥሰት ከደረሰባቸው ገዳማውያን መካከልም፦ አባ ገብረ ስላሴ ዋለልኝን፣አባ ወልደጊዮርጊስ ኃይለ ማርያም ፣ አባ ገ/ማርያም ገ/ዮሐንስ ፣መናኝ ክንፈገብርኤል ወልደሳሙኤል፣  አባ ገ/ስላሴ ገ/እግዚአብሔር ፣መናኝ ወልደሩፋኤል ወልደሳሙኤል፣አባ ወ/ገብርኤል ገ/ስላሴ፣አባ ገ/ህይወት ተ/ማርያም፣  አባ ኃ/ማርያም ገ/ስላሴ ፣እንዲሁም  የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አለምሸት ሙሉ፣ አቶ ተክሌ ገ/ኪዳን፣ አቶ አምባቸው ጥላሁንና አለቃ መሀቤ ገ/መስቀል ይገኙበታል።
"በተጨማሪም ከገዳሙ ለመውጣትም ሆነ ወደ ገዳሙ ለመግባት በምንንቀሳቀስበት ጊዜም የትግራይ ክልል ነዋሪ መሆናችሁን የሚያሳይ የቀበሌ መታዎቂያ ካላመጣችሁ እያሉ ያስገድዱናል፡፡ የገዳሙ ማኅተም ያለበት መታዎቂያ ስናሳይ ተቀባይነት የለውም እየተባልን መንቀሳቀስ እንዳንችል ተደርገናል፡፡ "ይላሉ መነኮሳቱ።
አክለውም "…  አሁን ወደ ጎንደር  ለማመልከት ስንመጣም ያስሩናል ብለን በትክክለኛው መንገድ መውጣት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም ተጨማሪ የሁለት ቀን የእግር መንገድ በርሃ ለበርሃ ተጉዘን ጎንደር ገባን፡፡ በዋናው መንገድ ለመምጣት የሞከሩት ታስረዋል፡፡ ማኅበረ-መነኮሳቱን በዘረኝነት ስለበተኑን 31 ያህል መነኮሳት ይህን ማመልከቻ ስናቀርብ ሌሎች ብዙዎች ገዳም ቀይረው ሄደዋል፡፡" ሲሉ የደረሰባቸውን እንግልት ዘርዝረዋል።
ሹመኞቹ  እነሱን ከገዳሙ  ካስወጡ በኋላ ከወረዳ አስተዳደር የተላኩ ሚሊሻዎችን ይዘው  በመሄድ መምህር፣ አቃቤትና ሌሎች ሰራተኞችን እንደ አዲስ  በመመደብ  ገዳሙን  በአዲስ መልክ  እንዳዋቀሩም በደብዳቤያቸው አመልክተዋል።
"ይህም ግልጽ የሆነ ጣልቃገብነት ነው፡፡ የገዳሙንም ስርዓት ያልጠበቀ ነው፡፡"ይህ ሁሉ የመብት ጥሰት የሚደርስብን ምንም ጥፋት ተገኝቶብን አይደለም ብለዋል።
ደብዳቤያቸውን ሲያጠቃልሉም፦"በተደጋጋሚ ያለአግባብ እየታሰርን፣ እየተደበደብን፣ የመንቀሳቀስ ነፃነታችን ተገድቦ፣ የግድያ ማስፈራሪያ በመንግሥት ባለስልጣን እየደረሰን በገዳማችን ለመኖር አልቻልንም፡፡ ዋስትናም አጥተናል፡፡ የሌላ ሀገር ዜጋ የሆንን ይመስል ያለጥፋት በመንፈሳዊ በዓታችን እንዳንኖር የማናውቀውን ፖለቲካ ተገን ባደረገ ዘረኛ አስተሳሰብ በገዳማችን የመቀጠል መብታችንና  ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በገዳሙ መነኮሳት ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በእኛ ብቻ ሊያቆም የሚችል ሳይሆን ውሎ አድሮ መጥፎ ጠባሳ የሚተው ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሙሉ መፍትሄ እንዲሰጡን እንጠይቃለን፡፡"ብለዋል።

No comments:

Post a Comment