ጥር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የአገሪቱን ኢኮኖሚና የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተነ የሚገኘውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ከእንግዲህ ከአገር ውስጥ አንበደርም ሲል የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ዘንድሮ ያጋጠመውን የበጀት ጉድለት መሸፈን ባለመቻሉ ከአገር ውስጥ ባንኮች ሊበደር እንደሆነ ሪፖርተር ዘገበ።
ለኑሮ ውድነቱ ጣራ መንካት አንዱና ዋነኛው ምክንያት መንግስት ከአገር ውስጥ መበደሩና ይህንንም ብድር ለማሟላት ብር እንዲታተም ማድረጉ ነው በማለት የቀረበባቸውን ትችት ከብዙ ማንገራገር በሁዋላ የተቀበሉት ሟቹ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ፤ “ከ እንግዲህ ግን መንግስት ፈጽሞ ከአገር ውስጥ ባንኮች አይበደርም” ማለታቸው ይታወሳል።
ይሁንና የዘንድሮን 26.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ለመሸፈን መንግስት ከአገር ውስጥ እንደሚበደር አስታውቋል።
መንግስት ብድሩን ለማግኘት ሲል እንዲታተም የሚያደርገው ብር እንደማይኖር ቢናገርም፤ባንኮች የማበደር አቅማቸው እጅግ የተዳከመ በመሆኑ ገንዘብ ወደ ማተሙ ማምራቱ አይቀሬ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ጋዜጣው የጠቀሳቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ፦”የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀዛቀዙ እና ከአገር ውስጥ ምንጮች ብድር ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መንግሥት ብር ማተም ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ “ ያስጠነቅቃሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የ2005 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት 137 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህንን በጀት ለመሸፈን ከታክስና የተለያዩ ገቢዎች 111 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ቀሪው 26 ቢሊዮን ብር ግን በበጀት ጉድለትነት ተይዞ በተለያዩ አማራጮች ለመሸፈን መታቀዱን ያስረዳል፡፡
ከእነዚህም መካከል 7.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ከውጭ አገሮች ከሚገኝ የፕሮጀክት ብድር፣ 5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን በዓለም ባንክ በኩል ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ከሚገኝ ብድር፣ እንዲሁም 169 ሚሊዮን የሚሆነውን ብር በእዳ ስረዛ ከሚገኝ ለመሸፈን መታቀዱን ይተነትናል፡፡
በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩት አማራጮች ከአጠቃላይ የበጀት ጉድለቱ 13 ቢሊዮን ብር ያህሉን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ቀሪውን 13 ቢሊዮን ብር ግን ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን ያብራራል፡፡
መንግሥት ከአገር ውስጥ ምን ያህል ሊበደር እንደሚችል የተጠየቁት የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ ሐጂ ኢብሳ ፣ “አሁን ላይ ሆነን መንግሥት ምን ያህል ሊበደር ይችላል የሚለውን መገመት አዳጋች ነው” ብለዋል፡፡
ነገር ግን ከብሔራዊ ባንክ የመበደር ዕቅድ በጭራሽ አለመኖሩን፣ ብድሩን በኢኮኖሚው ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኝ ገንዘብ ለመሸፈን መታቀዱንና እየተረጋጋ የመጣውን የዋጋ ንረት በማይጎዳ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡
በኢኮኖሚ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኝ ገንዘብ ማለት ከሌሎች የመንግሥት አበዳሪ ባንኮች እንደ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ እንደሆነ ጋዜጣው ያነጋገራቸው ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ተንታኞች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከመቀዛቀዝ ባለፈ ችግር ውስጥ ስላለ የባንኮች የማበደር አቅም የሳሳ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ብር የማተም ግዳጅ ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ ፍርኃታቸውን ይገልጻሉ፡፡
No comments:
Post a Comment