ጥር ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እየተካሄደ ባለው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ነገ ከናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል።
ዋልያዎቹ እና ንስሮቹ የሚያደርጉት የነገው ጨዋታ በከፍተኛ ደረጃ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት ስቧል።
ምድቡን ቡርኪናፋሶ በ4 ነጥብ ስትመራ ዛምቢያና ናይጀሪያ በ2 ነጥብ ይከተላሉ።
ዋልያዎች በ 1 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም በነገው ጨዋታ ዛምቢያ እና ቡርኪናፋሶ አቻ ከተለያዩ፤ወይም ዛምቢያ በቡርኪናፋሶ ከተሸነፈ-ዋልያዎች ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ንስሮቹን በ 1 ጎል ልዩነት ማሸነፍ ይበቃቸዋል።
በነገው ጨዋታ ዛምቢያ አሸንፎ- ናይጀሪያ ዋልያዎችን ካሸነፈ ሁለቱ ቡድኖች ተያይዘው ሊያልፉ ስለሚችሉ ቡርኪናፋሶዎች ለራሳቸው ማለፍ ሲሉ ማሸነፍ ያ ካልተሳካ እኩል መውጣት ግዴታቸው ነው።
ከዚህ አንፃር ቡርኪናፋሶዎች ጠንክረው ስለሚጫዎቱ ቢያንስ እኩል መውጣት አይቸገሩም ያሉ የስፖርት ተንታኞች፤ዋልያዎች በስሜት፣ በእልክና በተረጋጋ መንፈስ ጠንክረው በመጫዎት ናይጀሪያዎችን ካሸነፉ ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፍ ታሪክ ሊሰሩ እንደሚችሉ መክረዋል።
የኢሳት ቤተሰቦች በሙሉ ብሔራዊ ቡድናችን ድል እንዲቀዳጅ ልባዊ ምኞታቸውን ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment