FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, January 26, 2013

ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው ለብሔራዊ ቡድናችን ፣ለአሰልጣኞች እና ለደጋፊዎች ሁሉ


ለናይጄርያው ግጥሚያ ዝግጅት ላይ
ትናንት አርብ ጥር 17/ 2005 ዓም በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ከደቡብ አፍሪካ የተላለፈው የኢትዮጵያ እና ቡኪናፋሶ የእግር ኳስ ውድድር የኳስን መሰረታዊ ባህሪ በያዘ መልኩ ማለትም ማሸነፍ ወይንም መሸነፍ አንዱን መርጦ አብቅቷል። አዎን በኢትዮጵያ በኩል አራት ጎሎች ተቆጥረዋል። ጫወታው እንዳበቃ በመጀመርያ በጣም ተናደድኩ ትንሽ ቆይቼ ነገሩ አለመሞቱ ግን የቡድኑ ሞራል ምን ያህል ይሆን? የሚለው ብቻ አሳሰበኝ። ዛሬ ቅዳሜ ጫወታውን ደግሜ አየሁት። በእውነት ትናንት ያልታዩኝ የተጫዋቾቻችን ድንቅ ጥበብ ታየኝ። ሰው አንድን ነገር ለመመልከት የረጋ ልቦና ይሻል የሚባለው ልክ ነው። ዛሬ ከስሜት ውጭ ሆኘ ስመከት ቡድናችንን የሚያስደንቁ ጥበቦቹ ታዩኝ። እናም የሚከበር ቡድን ግን አኛ ተመልካቾች ልናከብረው እና ልናደንቀው የሚገባ ነው ብዬ አሰብኩ።
በአንድ ወቅት ከአስራዎች አመታት በፊት ግብፅ ውስጥ የብሔራዊ ቡድናችን (ለማጣርያ ይመስለኛል) ሲጫወት ቡድኑን ለማዋከብ የነበረው የተመልካች ዘዴ በጣም መጮህ እና ከእዚህ በፊት በ ሰማንያ እና ዘጠና ሺ ሕዝብ የተሞላ ስታድዮም ውስጥ ተጫውቶ የማያውቀውን ተጫዋች ማዋከብ ነበር። በወቅቱ ቡድናችን የአለም አቀፍ ጫወታ ተሞክሮ ስሌለው እና የሰላሳ ሺ ሕዝብ የሚይዝ የአዲስ አበባውን ስታድዮም ብቻ ስለሚያውቅ ትልቅ ችግር ፈጥሮ ነበር። አሁን ያ አቅም ተፈጥሮ የጫወታው ቴክኒክ ሁሉ ጥሮ መስመር ላይ ነው ያለው። የተሞከሩት የጎል ሙከራዎች የዕድል ጉዳይ እንጂ ምርጥ ተጫዋቾች እንዳሉን ለመረዳት አይናችንን የሚከፍቱ ናቸው። አሁን የቀረን አንዲት ነገር ነች። ጀግንነት፣እራስን ማወቅ፣ካለምንም ጉራ ታላቅ ተጫዋቾች እንዳሉን ማወቅ፣ይህንንም ለቡድኑ መንገር። ሽንፈት የሚጀምረው እራስን ዝቅ አድርጎ ማየት ሲጀመር ነው። ቡርኪናፋሶች የጎል ዕድል ቢያገኙም፣በጫወታ ቢገዳደሩንም፣ አሁንም የማሸነፍ እድላችን እጃችን ውስጥ መሆኗን ማወቅ አለብን። መሸነፍ፣ፈተና፣ተስፋ መቁረጥ አንዳንዴ ተደጋግመው የተጫኑ የሚመስሉበት ጊዜ አለ። እዚህ ላይ ነው ጀግና የሚያስፈልገው። ”ቁርጥ ቀን ባይመጣ ሁሉም ጀግና ነበር” የሚባለው የእዚህ ቀን ነው። ቡድናችን አሰልጣኞቻችን ሁሉ በአንድ መንፈስ ቀጣዩን ጫወታ እንደሚያሸንፉ በሙሉ ልብ እራሳቸውን ከማወቅ እና ከማክበር ጋር ይጫወቱ ይመኑ ታምር ይሰራሉ።
እዚህ ላይ በቡድናችን የሞራል መጠበቅ ላይ እክል ፈጥረዋል የተባሉ ወደፊት ጥብቅ ምርመራ የሚፈልጉ እና በቀላሉ
የማይታዩ ጉዳዮች እንደነበሩ ይወራሉ። ይህንን በተለይ አስልጣኝ ሰውነትም ሆኑ ምክትላቸው ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰሩ ለፖለቲካው አካላትም ሆነ ለሕዝቡ በድፍረት እንዲነግሩልን እንጠብቃለን። በእዚህ ዘመን ”የተሰወረ የማይታይ ያልታወቅ የማይገልጥ” የለምና። ለሁሉም ግን አሁን መደረግ ያለበት ቢያንስ ቀጣዩ ጫወታዎች እስከሚጠናቀቁ በትዕግስት የቡድኑንም ሆነ የደጋፊውን ህብረት እንዲጠበቅ ማድረግ ይመስለኛል።
ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው። ጀግናን ጀግና የሚያሰኘው ፈፅሞ የማይሸነፍ ምትሃታዊ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም በዕድል ወይንም በትንሽ ስህተት አልያም ችላ ብሎት ጀግና የመጀመርያ ሽንፈት ይሸነፋል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ግን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያርበደብድ ይሆናል። የዓለማችን ጀግኖች ተሸነፉ ሲባሉ እንደገና ተነስተው ስለሚያሸንፉ ያለፈውን ሽንፈታቸው ከቶ ማን ሊያስበው ይቻላል? እንግሊዝን እስኪ በአለም ዋንጫ ላይ የሚደርስባትን እንመልከት። እንዲያ ድንቅ ክለቦች ያላት ሀገር በዓለም ዋንጫ ላይ ግማሽ መድረስ ሲያቅታት ለእንግሊዝ ሕዝብ እና መንግስት ሰቀቀን የማይሆን ይመስለናል ? ግን እንግሊዞች ኳስ ስለማይችሉ ነው የተሸነፉት? አይደለም። ኳስ እንዲህ ስለሆነች ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጫወታ ዛሬ አለፍ አለፍ እያልኩ ከቡርኪናፋሶ ጋር ያደረገውን ጫወታ ስመለከት እጅግ ድንቅ ተጫዋቾች እንዳሉን ግን እኛ ልናከብራቸው፣ልናደንቃቸው፣ ታላቅ ችሎታ እንዳላቸው አንዳንድ ቴክኒካዊ ስራዎችን እያስተካከሉ እንዲሄዱ እራሳቸውን ዝቅ እንዳያደርጉ መንገር በባለዑያዎች ብቻ እንደሚገባ አመንኩ። ይህ ደግሞ ለሽንገላ ሳይሆን ቀድሞ የነበረው ”እኛ ኳስ አይሆንልንም” የሚባልበት ጊዜ ላይ ላለመሆናችን ችሎታቸውን በልዩ አቀራረብ ያሳዩን ተጫዋቾች ምስክር ናቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ደረጃዋ ለአለም አይደለም ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም ያስደነቀን ጉዳይ ነው። ወደ ኋላ ፈፅሞ መመለስ የለም!
በመጪው ማክሰኞ ከናይጄርያ ጋር በሚኖረው ውድድር ተአምር የመስራት ብቃቱም ሆነ አቅሙ አላችሁ። በአንድ በኩል ናይጀርያ በትናንትናው ከቡርኪናፋሶ ጋር በተደረገው ጫወታ ቡድናችንን ዝቅ አድርጎ የማየት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል። ይህ ጥሩ ዕድል ነው።
በእርግጥም ከቡክናፋሶ ጋር የሆነ አምላክ ከእኛ ጋርም አለ። ከናይጄርያ ጋር ያለ አምላክ ከእኛ ጋርም አለ። ቀጣዩን ከናይጄርያ ጋርም ሆነ ቀጥለው በሚከፈቱት ዕድሎች ቡድናችን እንዲያሸንፍ እኛ ተመልካቾች የምናደርገው ሁለት ነገር ነው። አንድ በስታድዮም ተገኝቶ መደገፍ ሁለተኛው እና ዋናው ማንም ችላ ሊለው ወይንም ሊረሳው የማይገባው ከልብ የሆነ ቢያንስ የጥቂት ደቂቃዎች ልመና ወደ እግዚአብሔር ማቅረብን ነው። ያኔ ሁሉም ግዴታውን ተወጣ ማለት ይቻላል።የኢትዮጵያን ቡድን ያወደሱ ብእሮች እንደገና ይቀረፃሉ። ዋልያዎች በርቱ!
ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው። ጀግናን ጀግና የሚያሰኘው ፈፅሞ የማይሸነፍ ምትሃታዊ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም በዕድል ወይንም በትንሽ ስህተት አልያም ችላ ብሎት ጀግና የመጀመርያ ሽንፈት ይሸነፋል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ግን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያርበደብድ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ጌታቸው
ኦስሎ

No comments:

Post a Comment