FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, January 18, 2013

ኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ ህብረትን ፕሮቶኮል ጥሳለች ተባለ

ጥር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም


ኢሳት ዜና:-በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ በሚካሄደው 50ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ኢትዮጵያ የሊቀ-መንበርነቱን ቦታ እንደምትረከብ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጠው መግለጫ በህብረቱ አገራት ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ ተዘገበ።
የደቡብ አፍሪካ የውጪ ፖሊሲ ኢኒሺየቲቭ (ሳፍፒ) እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበርነቱን ቦታ ከቤኒን እንደሚረከቡ በኢትዮጵያ የተሰጠው መግለጫ የህብረቱን ፕሮቶኮል የጣሰ እና ጊዜውን ያልጠበቀ በመሆኑ አባል አገራቱን አስገርሟል።


ኢትዮጵያ የሊቀ-መንበርነቱን ቦታ ለመውሰድ የፈለገችው ተራዋ ሆኖ ሳይሆን ፤ወቅቱ የህብረቱ 50ኛ ዓመት ኢዩቤልዩ የሚከበርበት በመሆኑ በዚህ ታሪካዊ በዓል ሊቀመንበርነቱን ለመውሰድ ከመሻት ነው የሚል ትችትም ተሰንዝሯል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን አቶ ሀይለማርያምን በሊቀመንበርነቱ ቦታ መምረጥ- ከህብረቱ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ጋር እንዲያያዝ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።


አምባሳደሩ ይህን ቢሉም የሊቀመንበርነቱ ምርጫ የሚደረገው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የፊታችን ጃንዋሪ 27 በሆነበት ሁኔታ-ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ሊቀመንበርነቱ የሷ እንደሆነ የሰጠችው መግለጫ የህብረቱን ፐሮቶኮል ጥሷል ተብሏል።
ቃል አቀባዩ ዲና ሙፍቲ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የህብረቱ ሊቀመንበር ለመሆን ተራው የምስራቅ አፍሪቃ መሆኑን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ቦታውን ከቤኒን ለመረከብ ቅድመ-ዝግጅት አጠናቃለች ማለታቸው ይታወሳል።


በኢትዮጵያ አቋም ተቃውሞ ያሰሙት የህብረቱ አገራት እነማን እንደሆኑ በግልጽ ባይመለከትም አምባሳደር ዲና ሙፍቱ ፦”አቶ ሀይለማርያም የሊቀመንበርነቱን ስፍራ ሲረከቡ ዋነኛና ቀዳሚ ተግባራቸው በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲመሰረት እና ለአዲሱ የሶማሊያ መንግስት ጠንካራ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ነው”ማለታቸው፤ምናልባት ተቃውሞው ከምሥራቅ አፍሪካ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ ያጭራል።


ጃንዋሪ 27 ቀን የህብረቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በሚካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ እንዳለችው የሊቀመንበርነቱን ቦታ ታገኝ ይሆን ወይስ ሌላ ውዝግብ ሊነሳ ይችላል? የሚለው ከወዲሁ ማነጋገር ጀምሯል።

No comments:

Post a Comment