ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በታኅሳስ ወር/2004፣ በአወሊያ ትምህርት ቤት የጀመሩት ‹‹አል አሕባሽ›› የተሰኘ አስተምህሮት እየተጫነብን ነው ሮሮ – ቀጥሎም ‹መምህራኖቻችን አይባረሩ› እንቅስቃሴ… መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በመምረጥ፣ መጅሊሱ ይቀየርና ሕገ መንግሥቱ ይከበር እስከማለት ዘልቋል፡፡ ይሄው ጥያቄ የተመለሰበት መንገድ የመጅሊሱ አባላት በቀበሌ እንዲመረጡ ማድረግና ያንን የተቃወሙትን የኮሚቴ አባላት እና ሌሎችንም ማሰር እና በሽብርተኝነት መክሰስ ሲሆን… ይህ የመንግሥት እርምጃ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በማስቆጣት ተቃውሞዋቸውን በየሣምንቱ አርብ ከጸሎት በኋላ እየገለጹ ዓመት እንዲደፍኑ አድርጓቸዋል፡፡
በተቃራኒው በየከተማው እነዚህን ብሶተኞች የሚቃወሙ ሙስሊም ሰልፈኞችን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደጋግሞ አሳየ፡፡ ብዙዎች ሰልፈኞቹን መንግሥት ያስተባበራቸው እንደሆኑ መገመት አልቸገራቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰልፈኞች በሰልፉ ብዙም አልዘለቁበትም፤ በሌላ በኩል ከታሪክ እንደምንረዳው በደርግ ዘመን ‹‹የሃይማኖት መሪዎች የኢምፔሪያሊስቶችን አብዮት የሚያደናቅፍ ሴራ አወገዙ›› የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው እንደነበሩ ሁሉ አሁንም ‹‹የእንትን መስኪድ ኢማሞች ‹አንዳንድ› ድብቅ ሴራ አጀንዳቸውን በሙስሊሙ ዘንድ ለማራመድ የሚፈልጉ … አወገዙ፡፡›› የሚለውን ዜና ከፕሮፓጋንዳ ለይቶ ማይት ስለማይቻል ነው፡፡
መንግሥት የሙስሊሞቹን ጥያቄ በአጭሩ መልስ የማይሰጠው እንደሚናገረው ‹‹አክራሪነትን›› ለመከላከል ብቻ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ይልቁንም የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንም የውስጥ ለውስጥ አጀንዳ በመሆኑ (‹‹የቀድሞውን ጳጳስ የሕወሓት አባል/ደጋፊ ናቸው›› እስከማለት ድረስ) የሙስሊሞቹን ጥያቄ መመለስ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችንና ምናልባትም ሌሎችንም ፊት እንደመስጠት ይሆንብኛል ብሎ ሳይጠረጥር አይቀርም፡፡
የሆነ ሆኖ ምንም እንኳን መንግሥት የሃይማኖተኞችን ጥያቄዎች በጉልበት ቢደፈጥጥም (‹‹ምርጫውን በቀበሌ በማካሄድ››) ወይም የየሳምንቱን ጥያቄ እንዳልሰማ በማለፍ ‹‹ሰልችቷቸው እንዲተዉት›› ለማድረግ ቢሞክርም፤ እስካሁን ከተለመከትነው መገመት እንደምንችለው… እነዚህ ሰዎች ስትራቴጂያቸውን እየቀያየሩ ያላቸውን ሁሉ አማራጭ ወደመጠቀም አያመሩም ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡
በቅርቡ እንኳን ያሳዩት የቢጫ ካርድ ተቃውሞ ከእግርኳስ ጨዋታ ሕግ የተወረሰ ሲሆን እንደማስጠንቀቂያ ታይቷል፡፡ ቀጣዩ ቀይ (የማሰናበቻ) ካርድ እንደሚሆን ቢገመትም መቼ እና እንዴት ለሚለው ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ሙስሊሞቹ የቀይ ካርድ እርምጃቸውን ከጀመሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከመስኪድና ከጸሎት ስብሰባ ውጪ ሊጠሩ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እርምጃ (ከመንግሥት ተገማች ምላሽ ጋር ተደማምሮ) አገሪቱን ወደአብዮት ሊመራት ይችላል ብሎ መጠርጠር ከባድ አይመስለኝም፡፡
ነገር ግን እንደምናስበው ይህ ዓይነቱ አብዮት በሒደቱም ሆነ በውጤቱ ቀላል አይሆንም፡፡ የሙስሊሞቹ አደባባይ መውጣት ጥያቄያቸውን ከሃይማኖታዊው ይልቅ ፖለቲካዊው ትርጉሙ ስለሚያመዝን (የመንግሥት አይቀሬ ሥልጣን ፈልገው ነው ፕሮፓጋንዳ ታክሎበት) ሙስሊም ላልሆነው የኅብረተሰብ አካል የጥርጣሬ መንፈስ ሊፈጥር እና አንዱ በሌላው ላይ የመቃወም አቋም ሊያስይዝና ለፖለቲካውም ለማኅበረሰቡም የማይበጅ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡
እንደመደምደሚያ
ሃይማኖቶች ለአብዮት የሚያበረክቱት እና ማበርከት የሚችሉት ሚና አለ የሚባል ባይሆንም፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አብዮታዊ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ከታሰበ የአገሪቱን ብዝኃ ሃይማኖትነት ማገናዘብ የሚችል ገለልተኛ/ሴኩላር ለውጥ ቢመጣ እመርጣለሁ፡፡ የሃይማኖተኞች ወይም ሃይማኖትን ግብ ያደረጉ አብዮተኞች ሚናም ሃይማታዊ/አምልኮአዊ ጣልቃ ገብነት ከመቃወም ወይም የማምለክ/አለማምለክ ነጻነትን (ማለትም በጠቅላላው ሥርዐት ውስጥ የእምነት ነጻነት ሥርዐቱን ለይቶ /ምን ያህል ነጥሎ ማየት ይቻላል የሚለውን ለውይይት በመተው/ ለማስተካከል) ከመሻት በላይ የተሻገረ መሆን የለበትም፡፡ በጥቅሉ ግን ሃይማኖተኞች እንደዜግነታቸው የሥርዐት ለውጥን መሻት ብቻ ሳይሆን የለውጡ ዋነኛ ተዋናይ የመሆን መብቱም ግዴታውም አለባቸው፡፡
No comments:
Post a Comment