ጥር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሁኑ የቻይና አምባሳደር ስዩም መስፍን ከሲሲቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ቻይና በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ማእድናትን በምታወጣበት ጊዜ የአካባቢ ውድመት ታደርሳለች እየተባለ በአፍሪካውያንና በምእራባዊያን ዜጎች የሚደርስባትን ወቀሳ መከላከል አያስፈልጋትም ብለዋል።
አምባሳደሩ ይህን መልስ የሰጡት የሲሲቲቪ ጋዜጠኛ ” ብዙውን ጊዜ አገራችን በሌሎች አገሮች ማእድናትን ስታወጣ የአካባቢውን ህዝቦች ታፈናቅላለች፣ በአካባቢውም ላይ ውድመት ታደርሳለች እየተባለች ትወቀሳለች፣ ይህ ችግር በኢትዮጵያም ውስጥ አለ?’ የሚል ጥያቄ ካቀረበላቸው በሁዋላ ነው።
አምባሳደር ስዩም መስፍን ሲመልሱ ” ቻይና የአፍሪካን ማእድን ለማልማት እዚህና እዛ ለሚቀርብባት ወቀሳ ራሱዋን መከላከል አያስፈልጋትም፣ የእኛ ነባር ወዳጆች እኮ ይህንኑ ለዘመናት ሲያካሂዱ ነበር” ብለዋል።
“የምእራባዊያን ኩባንያዎች ማእድናትን በአፍሪካ ውስጥ አውጥተው በተወሰነ ደረጃ ቀይረው ወደ አውሮፓ ሲልኩ ቀረጥ ይከፍላሉ፣ ማእድናትን እንዳለ ሲልኩ ግን ቀረጥ አይከፍሉም ይህ በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ እንዱስትሪ ላይ እድገት እንዳይኖር አድርጓል” የሚሉት አምባሳደር ስዩም ቻይና ይህንን እስካልኮረጀች ድረስ በአካባቢ ውድመት ዙሪያ ለሚደርስባት ክስ ትኩረት መስጠት እንደማይገባት መክረዋል።
ጋዜጠኛው ” ቻይናዎች ጥሩ ምክር ከእውነተኛ ወዳጅ ይገኛል ይላሉ” በማለት በአምባሳደር ስዩም መስፍን መልስ መርካቱን ገልጿል።
ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ማእድናትን ፍለጋ በምታካሂደው እንቅስቃሴ በአካባቢ ላይ ጉዳት ታዳረስላች ለህዝብ መፈናቀልና ችግር ትኩረት አትሰጥም በማለት ወቀሳ እንደሚቀርብባት ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment