በአሸናፊ ደምሴ
አቃቤ ህግ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ አስበው ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሲል ከሰየመውና መንግስት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ቡድን ጋር በማበር የኦሮሚያን ክልል ፌዴሬሽኑ ለመገንጠል ሲንቀሳቀሱ ነበር ባላቸው አምስት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ትናንት የጥፋተኝነት ብይን ሰጠ።
ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀበት 2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በበደሌ፣ በጊንጪ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞንና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለኦነግ አባል ሆነው አባል መልምለው የፖለቲካ ስልጠና ወስደው ሲንቀሳቀሱ ነበር የሚለው የአቃቤ ህግ ክስ፤ ተከሳሾቹ የኦሮሚያን ክልል ከፌዴሬሽኑ በሃይል ለመገንጠል ከሚንቀሳቀሰው ኦነግ ድርጅት ውስጥ ይህንኑ አላማ ለማስፈፀም የተንቀሳቀሱ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የአገሪቱን የግዛት አንድነት መንካት ወንጀል ተከሰዋል ይላል።
ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን ክደው የተከራከሩት ተከሳሾች 1ኛ ለገሰ ታደሰ፤ 2ኛ አለማየሁ ቶሎሳ፣ 3ኛ ሀብታሙ ከበደ፣ 5ኛ አብዲ አያና እና 6ኛ አድሬ ኡርጌሳ ሲሆኑ፤ የአቃቤ ህግን የክስ መዝገብ በአግባቡ አላስተባበሉም ያለው ፍርድ ቤቱ በትናንት ውሎው ጥፋተኛ ናችሁ ብሏቸዋል።
በአራተኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ማስረጃ የተሟላ ባለመሆኑ በብይን ወቅት በነፃ የተሰናበተ ሲሆን፤ አምስቱ ተከሳሾች ላይ ግን እንዲከላከሉ ዕድሉ ቢሰጣቸውም የአቃቤ ህግን ክስ ጥርጣሬ መጣል ሳይችሉ ቀርተዋል።
የጥፋተኝነት ብይኑን ተከትሎ አቃቤ ህግ የቅጣት ደረጃው ከፍ ብሎ እንዲያዝለትና ማስተማሪያ እንዲሆንለት ሲጠይቅ፤ የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ወጣቶቹ ገና በትምህርት ላይ ያሉና ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን ከመጥቀሳቸው ባሻገር 2ኛ ተከሳሽ የኦብኮ አባል ነኝ ሲል ያቀረበው መረጃም እንደማቅለያ እንዲያዝለት የጠየቁት ተከላካይ ጠበቃው፤ ለሁሉም ተከሳሾች ቅጣቱ በገደብ እንዲያዝላቸው ሲሉ አመልክተዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎትም የግራ ቀኙን ሀሳብ መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 7 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ሰንደቅ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment